1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐባይ ግድብ ፣ የኢትዮጵያ ፓርላማና ተቃዋሚዎች

ሐሙስ፣ ሰኔ 6 2005

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአባይ ተፋሰስ ሃገራትን የትብብር ስምምነት ዛሬ አፀደቀ ። በ547 ቱ የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምፅ የፀደቀው ይኽው ስምምነት የአባይ ወንዝ ውሐ ዋነኛ ተጠቃሚ ለሆኑት ለግብፅና ለሱዳን የላቀ መብት የሚሰጠውን የቀደመውን የቅኝ ግዛት ዘመን ውል የሚተካ አዲስ ስምምነት ነው ።

https://p.dw.com/p/18p1V
ምስል picture-alliance / dpa

ስምምነቱን ከዚህ ቀደም ሌሎች 5 የተፋሰሱ ሃገራት ፈርመዋል ። ስምምነቱን ከተቀበሉት ሃገራት አብዛኛዎቹ ውሉን በፓርላማቸው አፅድቀዋል ። የኢትዮጵያ ፓርላማ እስካሁን ስምምነቱን ሳያፀድቅ የቆየው በግብፅ በይፋ በምርጫ የተቋቋመ መንግሥት እስኪመሰረት ሲጠበቅ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ በረከት ስምዖንን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል ። የኢትዮጵያ ፓርላማ ግብፅ አዲስ መንግሥት እስክትመሰርት ድረስ ስምምነቱን ሳያጸድቅ በአባይ ወንዝ ላይ የሚያስገነባው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግብፅና ኢትዮጵያ ማወዛገቡን እንደቀጠለ ነው ።ግብፅ ኢትዮጵያ የምትሰራው ግድብ ወደ ሃገርዋ የሚገባውን የአባይ ውሐ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል ብላ ትሠጋለች ። የግብጽ ባለሥልጣናት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሙርሲን ጨምሮወደ ግብፅ የሚፈሰውን የውሐ መጠን የሚቀንስ ፕሮጀክትን ለመቋቋም ሁሉንም አማራጮች እንደሚወስዱ አስጠንቅቀው ነበር ። ይሁንና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የግድቡ ግንባታ በማንም ሆነ በምንም ምክንያት አይቆምም ሲሉ አስታውቀዋል ። የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሐመድ ከማል አምር ስለ ግድቡ ለመነጋገር የፊታችን እሁድ ወደ አዲስ አበባ ይሄዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ዘግቧል ። የኢትዮጵያ ፓርላማ ፤ የዐባይን የትብብር ስምምነት ማጽደቁ ግብጽ በቅርቡ ከቆሰቆሰችው እሰጥ አገባ አኳያ የኢትዮጵያን ጠንካራ አቋም የሚያንጸባርቅ ሳይሆን እንዳልቀረ ተመልክቷል። ዛሬ ፓርላማው የደረሰበትን ውሳኔ መንስዔ በማድረግ ፤ ከአዲስ አበባው ዘጋቢአችንን ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ ግር ቃለ ምልልስ አድርገናል ። በተያያዘ ዜና በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉት ፣ ከኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፤ አንድነት ለዴሞክራሲና ፍትኅ ፤ አንድነት፤ ገዥው ፓርቲ የዐባይን ግድብ ጉዳይ ፣ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ እያዋለው ነው ሲል ወቀሰ። የአንድነት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፤ ግብጻውያን የኢትዮጵያን የተቃውሞ ወገኖች በመርዳት ግድቡን ማሰናከል ነው የሚል ቃል መሠንዘራቸው፣ «የጠላቴ ጠላት » በሚል ፈሊጥ በሃጋራችን ጥቅም ላይ ፈጽሞ የማንደራደር መሆናችንን ሊረዱልን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር ዝርዝር ዘገባ አለው ።

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ