1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ቅርሶች በኢትዮጵያ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 16 2007

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል /UNESCO/ መዝገብ ላይ የሰፈሩ እና በዓለም ቅርስነት እውቅና ለማግኘት የሚጠባበቁ ቅርሶች አሏት።

https://p.dw.com/p/1G3LV
Bet Giyorgi Felsenkirche von Lalibela in Äthiopien
ምስል picture alliance/Robert Harding World Imagery

እነዚህን ቅርሶቿን ጠብቆ የቆየው ማህበረሰብ ለዚህ ትልቅ ሚና መጫወቱ ይነገራል።ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ኢትዮጵያ በጎርጎሮሲያው 2015 ከዓለም ምርጥ የአገር ጎብኚዎች መዳረሻ ተብላ በአውሮፓ የቱሪዝም እና የንግድ ምክር ቤት እውቅና ተሰጥቶታል። ይህም ምክር ቤቱ ባወጣው ዘገባ መሰረት ኢትዮጵያን ምርጥ ተሸላሚ እንድትሆን ካበቋት ምክንያቶች መካከል፤ እንደ አክሱም፤ ላሊበላ፤ የሀረሩ ጀጎል፣ የመሣሰሉት ቅርሶች ይገኙበታል። እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ስፍራዎች ደግሞ በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣የትምህርትና ባህል ማዕከል/UNESCO/መዝገብ ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ናቸው።

ፓሪስ ፈረንሳይ በሚገኘው በዩኔስኮ በሚኒስትር ካውንስል ማዕረግ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተጠሪ ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይሌ፤ ዩኔስኮ አንድን ቅርስ እንዴት የዓለም ቅርስ ብሎ እንደሚሰይም ገልፀውልናል። ይህንንም የሚወስነው በየዓመቱ የሚገናኘው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ነው። የዘንድሮው 39ኛው የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ስብሰባ ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ዶይቸ ቬለ በሚገኝበት ቦን ከተማ ከሰኔ 21 እስከ ሐምሌ 2 2007 ዓም ተካሂዷል።

Bildergalerie Axum
ምስል DW/G. Tedla

ዘንድሮ ዮኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘግባቸው ከኢትዮጵያ የቀረቡ ቅርሶች ባይኖሩም፤ በጎርጎሮሲያዊው 2016 ዓም የሚቀርቡ የተወሰኑ ቅርሶች አሉ። ከነዚህም መካከል የኦሮሞ ህዝብ የገዳ ስርዓት አስተዳደር አንዱ ነው። ላለፉት አራት አመታት በኢትዮጵያ የቱሪዝም እና ባህል ሚኒስቴር በቱሪዝም ባለሙያነት ያገለገሉት ሚርከና አብደታ፤ በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ ተራ ስለሚጠብቀው ስለዚሁ ቅርስ ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ ከገዳ ስርዓት አስተዳደር ባሻገር እንደ ፍቼ ጨምባላላ የደቡብ ህዝቦች የዓመት መለወጫ፤ የባሌ ብሄራዊ ፓርክ፣የመሳሰሉት በቅርስነት በዩኔስኮ እውቅና ለማግኘት እየተጠባበቁ የሚገኙ ናቸው።በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ለማግኘት ከሚጠባበቁ ቅርሶች መካከል የገዳ አስተዳደር ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ የሚሉት በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተጠሪ ፕሮፌሰር ምትኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና በማህበረሰቡ ዘንድ ያልተመዘገቡ ቅርሶች እንዳሉም ጠቁመዋል።አንድ ሀገር በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የምታስመዘግባቸው ቅርሶች በጨመሩ ቁጥር ከዚህ የምታገኘው፤ ትርፍ ይጨምራል።

UNESCO United Nations Educational, Scientific and Cultural Organization Logo

የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ ቀጣይ ስብሰባ የሚቀጥለው ዓመት ነው። በዚህም ጉባኤ ላይ ቢያንስ አንዱ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርስ የማዕከሉ መዘርዝር ውስጥ እንደሚገባ የቀድሞው የባህል እና ቱሪዚም ሚኒስቴር ባልደረባ አቶ ሚርከና አብደታ እርግጠኛ ናቸው።

በዓለም ቅርስነት እውቅና ያገኙ እና ለማግኘት በሚጠባበቁ የኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ያደረግነውን የባህል መድረክ ዝግጅት በድምፅም ያገኙታል።

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ