1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክና የታዳጊ አገሮች የልማት ችግር

ሐሙስ፣ ሰኔ 2 1997
https://p.dw.com/p/E0ec

አያሌ የምዕራቡ ዓለም የኤኮኖሚ ሥርዓት ተቃዋሚዎች ለአዲሱ ባለሥልጣን በላኩት ግልጽ ደብዳቤ የዓለም ባንክ በታዳጊ አገሮች ጥቅም ላይ ይበልጥ ያተኮረ ሆኖ እንዲጠገን ጠይቀዋል። ቮልፎቪትስ የዓለም ባንክ አስተዳዳሪ እንዲሆኑ በፕሬዚደንት ቡሽ መታጨታቸው በጅምሩ በምዕራባውያን አገሮች ሣይቀር በዓለም ዙሪያ ነበር ተቃውሞ የገጠመው።

ለዚሁም ምክንያቱ የቀድሞው ምክትል መከላከያ ሚኒስትር የኢራቅን ወረራ በግንባር-ቀደምነት ከቀየሱት ቀደምት የአሜሪካ ባለሥልጣናት አንዱና በፖለቲካ አመለካከታቸውም ሲበዛ ወግ-አጥባቂ መሆናቸው ነው። ቮልፎቪትስ የባንኩ ዓባል ሃገራት የኋላ ኋላ ለዋሺንግተን ግፊት ባይንበረከኩ ኖሮ በሙሉ ድምጽ ተቀባይነት አግኝተው ሊሾሙ ባልበቁም ነበር።

የሆነው ሆኗል፤ ዓለም፤ በተለይም ታዳጊው ዓለም በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ሃቁን ተቀብሎ መግፋቱ ግድ ነው የሆነበት። ፓውል ዎልፎቪትስ በበኩላቸው ለዓለም ባንኩ አስተዳደር ሥልጣን ከታጩ ወዲህ ባለፉት ወራት ዝናቸውን ለማደስና የሙያውን መስክ አዋቂዎች ለማድመጥ ሲጥሩ መቆየታቸው ነው የሚነገረው። ከተለያዩ የባንኩ አስተዳደር ባለሥልጣናትና የልማት አዋቂዎች በመምከር የተጣለብኝን ሃላፊነት ለመወጣት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጌያለሁ ነው የሚሉት።

ዎልፎቪትስ የቀደምታቸውን የጀምስ ቮልፈንሰንን ውርስ ተቀብሎ ለማሳደግ እንደሚፈልጉም ቃል ገብተዋል። “የልማት ዕርድታ ሁላችንን የሚያስተሳስር የጋራ ዓላማ ነው። ሕዝቦች ድህነትን መታገል ያለውን ዓቢይ ትርጉም ያውቁታል። በመሆኑም በዓለም ላይ ያለውን ድህነት ለማለዘብ አስተዋጽኦ ማድረግ መቻሉ በዕውነት በጣም ነው የሚያስደስተኝ።” ሲሉ ተናግረዋል።

ፓውል ዎልፎቪትስ በቅርቡ የአፍሪቃን ክፍለ ዓለም እንደሚጎበኙና በሚቀጥለው ወር ስኮትላንድ-ግሌንኢግል ላይ በሚካሄደው የሥምንቱ ሃያላን መንግሥታት የ G-8 መሪዎች ጉባዔ የአፍሪቃ የልማት ዕርዳታ ጉዳይ ከዓበይቱ የአጀንዳ አርዕስት አንዱ እንደሚሆን አስታውሰዋል። “ይበልጡን ተሥፋ የማደርገው ከአምሥት ዓመታት በኋላ መለስ ብለን ስናስተውል ይህ ለአፍሪቃ የለውጥ ወቅት እንደነበር፣ በርካታ የአፍሪቃ አገሮች ዘላቂ የልማት አቅጣጫ ይዘዋል፤ አንዳንዶች ወደኋላ ቀረት ያሉትም መከተል ችለዋል ብለን ለመናገር እንበቃለን ብዬ ነው።”

አሜሪካዊው ባለሥልጣን አምነውበትም ሆነ ከያቅጣጫው የሚሰነዘረባቸውን ጥርጣሬ ለማለዘብ ያልታሰበ የአቋም ተሃድሶን ነው ያንጸባረቁት። ሆኖም በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለም የኤኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ተቃውሞ ባላቸው የደቡቡ ዓለም ጥቅም ተሟጋቾች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘታቸው ሲበዛ ያጠራጥራል።

ዎልፎቪትስ የሥራ ዘመናቸውን በይፋ በጀመሩበት ዕለት በባንኩ ፊት ለፊት የተሰለፉ የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ሥርዓት ተቃዋሚዎች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከሶሥት መቶ የሚበልጡ ድርጅቶች የፈረሙበትን አንድ ደብዳቤ ለባለሥልጣኑ አቅርበዋል። ደብዳቤው የዓለም ባንኩ የበላይ አስተዳዳሪ ድርጅቱን እንዲከፍቱና ለታዳጊ አገሮች አጠቃላይ የዕዳ ምሕረት እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው።
“Alliance for Social Justice” “የማሕበራዊ ፍትህ ሕብረት” እንደተሰኘው ድርጅት ባልደረባ እንደ ሶረን አምብሮስ ዕምንት በዎልፎቪትስ የሥልጣን ዘመን የረባ ለውጥ የሚጠብቅ ማንም የለም። “ሚስተር ዎልፎቪትስ ለዓለማችን ድሆች ከቀደምታቸው ከጀምስ ቮልፈንሶን የተሻለ ይሆናሉ የሚል ዕምነት የለንም። ይልቁንም ሁኔታው የባሰ ይሆናል ብለን ነው የምንጠረጥረው።”

የዓለም ባንክ ለታዳጊ አገሮች በያመቱ የሚሰጠው ብድር ሃያ ሚሊያርድ ዶላር ገደማ ይጠጋል። የብድር አሰጣጡ ሁኔታና ከዚሁ ጋር የተያያዙት ግዴታዎች ባንኩ በተቀባዮቹ አገሮች ላይ የፖለቲካ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ በግልጽ ያሣያሉ። ተቀባዮቹ ሃገራት የልማት መርሃቸውን ከባንኩ ፖሊሲዎች ለማጣጣም ብዙ ጊዜ በብሄራዊ ደረጃ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ ፕሮዤዎችን መተው፣ የምንዛሪያቸውን የለውጥ ዋጋ ያለውዴታ ዝቅ ማድረግና የበጀት ፖሊሲያቸው’ን መቀየር እንደሚገደዱ በየአገሩ የታየ ጉዳይ ነው።
ማሕበራዊ ዋስትና በሚገባ ባልተረጋገጠባቸው በነዚሁ ድሆች አገሮች እዚህ ግባ የማይባለው መንግሥታዊ ድጎማ መሰረዙም ይበልጥ ለድህነት መስፋፋት ምክንያት መሆኑም እንግዳ ነገር አይደለም። በዚሁ የተነሣ ባንኩ በኢንዱስትሪ ልማት የተራመዱት መንግሥታት ጥቅም ጠባቂ፣ ወይም መሣሪያ ነው የሚሉት ተቺዎቹ ጥቂቶች አይደሉም። ሁኔታው ይህን በሚመስልበት ወቅት ነው እንግዲህ አሁን የተሃድሶው ጥሪ አይሎ የሚገኘው።

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ሰባት ቀደምት መንግሥታትና ሩሢያ በፊታችን ወር በስኮትላንድ-ግሌንኢግል በሚያካሂዱት የመሪዎች ጉባዔ የአፍሪቃ ጉዳይ ዓቢይ ትኩረት እንደሚሰጠው መወራቱ ሰሞኑን ያለማቋረጥ መነገር ይዞ የሚገኘው ዜና ነው። ሆኖም ዓለምአቀፉ የልማት ዕርዳታ በያመቱ በ 25 ሚሊያርድ ዶላር ከፍ እንዲል፣ ለ 38 ድሆች ተብለው ለተመደቡ አገሮች ሙሉ የዕዳ ምሕረት እንዲደረግና ሌሎች ድህነትን የሚያለዝቡ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ በብሪታኒያ መንግሥት የልማት ኮሚሢዮን የተንቀሳቀሰው ሃሣብ አሁንም የጋራ ሆኖ መታቀፉን የሚያመለክት ሁኔታ የለም።

ሃሣቡን ቢቀር አሜሪካ ከአሁኑ እንዳልተቀበለችው ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ላይ የደቡብ አፍሪቃን መሪ ታቦ እምቤኪን ተቀብለው ያነጋገሩት ፕሬዚደንት ቡሽ በማያሻማ ሁኔታ አስገንዝበዋል። ጉዳዩ ባለፉት ዓመታት እንደታየው ሁሉ የበለጸጉት መንግሥታት መሪዎች በተሰበሰቡበት ሁሉ ከመነሣቱ በስተቀር ሰባት መቶ ሚሊዮን ለሚሆነው ከሣሃራ በስተደቡብ ለሚገኘው የአፍሪቃ ሕዝብ የተሥፋ ጭላንጭል ማሣየቱ አሁንም ሲበዛ ያጠራጥራል።

በርካታ የበለጸጉ መንግሥታት ለአፍሪቃ ልማት ከዓመታዊ አጠቃላይ የሕብረተሰብ ምርታቸው 0.7 በመቶ የምትሆነዋን ድርሻ ለመለገስ ከ 35 ዓመታት ገደማ በፊት የገቡትን ቃል እስከዛሬ ዕውን ያደረጉት አራት የአውሮፓ አገሮች ብቻ ናቸው። አሜሪካ እንዲያውም 0.2 ከመቶ እንኳ በማትሞላ ድርሻ የመጨረሻውን ቦታ ይዛ ነው የምትገኘው። ይህ ደግሞ አፍሪቃ ዛሬ ከመቼውም ይልቅ በረሃብ፣ በበሽታና ባለመረጋጋት በመወጠር በሞት-ሽረት ሁኔታ ላይ በምትገኝበት ጊዜ እጅግ የሚያሳዝን፤ የሚያሳፍርም ነው።
ሃያሏ መንግሥት ዩ.ኤስ.አሜሪካ ለኢራቅ ወረራና ከዚያም ወዲህ ያፈሰሰችውና የምታፈሰው መዓት ገንዘብ ሲታሰብ ለዓለምአቀፉ ልማት ዕርዳታ የምታቀርበው 16 ሚሊያርድ ዶላር ዓመታዊ የልማት ዕርዳታ ኢምንት ሊባል ይችላል። አሜሪካ በዓለም ላይ ግማሽ ገደማ የሚጠጋውን የጦር መሣሪያ የምታመርተው አገር መሆኗም ሌላው ሃቅ ነው። ዋሺንግተን አሁን ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ያቀረበችው የ 500 ሚሊዮን ኤውሮ የረሃብ ዕርዳታም ከበጎ ፈቃድ መግለጫ ያለፈ ሆኖ ሊታይ የሚገባው አይሆንም።

አፍሪቃ ዛሬ መንታ መንገድ ላይ ደርሳ ነው የምትገኘው። በአንድ በኩል የውጩ ዕርዳታ የግድ ያስፈልጋታል። አለበለዚያ ችግሩን ለብቻዋ ልትወጣው አትችልም። በሌላ በኩል አዲሱ የአፍሪቃ የልማት ሽርክና በአሕጽሮት ኔፓድ በመባል የሚታወቀው ዕቅድ ክፍለ-ዓለሚቱን በተለይ በራስ አቅም ላይ ተመሥርቶ በተሃድሶ አቅጣጫ ለማራመድ ከተጸነሰ ወዲህ ብዙዎች ተሥፋ ማቀንቀናቸው አልቀረም።

እርግጥ ይህም ሰፊ የልማት ዕርዳታ ሳይታከልበት ዕውን ሊሆን እንደማይችል ዕቅዱ ይፋ ከሆነ ወዲህ ያለፉት አራት ዓመታት ሂደት በይበልጥ አሣይቷል። ከምዕራቡ ዓለም በኩል አስፈላጊውን ዕርዳታ ለመለገስ በጎ አስተዳደር፣ ፍትህና የሰብዓዊ መብት መከበር ቅድመ-ግዴታ ሆኖ መቅረቡ ባልከፋ ነበር። ችግሩ ማን ፍትህን እንደሚረግጥና ማን እንደሚያከብር በሃቅ ተለይቶ ጥርት ባለ መንገድ አለመቀመጡ ነው። አፍሪቃን በተመለከተ የምዕራቡ ዓለም ባለ-ሁለት መስፈርት የዴሞክራሲ ግንዛቤ ግራ ማጋባቱ ዛሬም አላበቃም።

የፈለጉትን ገዢ ቡድን የማወደሱና የጠሉትን የማግለሉ ዘይቤ፤ ዛሬም በመስፈርትነት የሚሰራበት ሆኖ እንደቀጠለ ነው። በተጨባጭ ማን የልማት ዕርዳታ ወይም የዕዳ ምሕረት ይገባዋል፤ አይገባውም የሚወስነው ዛሬም ቢሆን የአበዳሪዎች የራስ ጥቅምና የተለጋሹ መንግሥት ለነርሱ ፍላጎት ያደላ መሆን-አለመሆን ነው።

ተጨባጩ ሃቅ ይህ ሲሆን ብዙ እየተነገረለት ያለው የቅርቡ የስኮትላንድ የ G-8 ጉባዔ መፍትሄ ያመጣል ብሎ በተሥፋ መጠበቁ በጣሙን ያዳግታል። የሚቀረው ምርጫ አፍሪቃ ራሷ ባላት አቅም ላይ በማተኮር የተቻለውን ያህል ወደፊት ለመራመድ መሞከር ብቻ ነው። ለዚህም ኔፓድ የመንግሥታት ስብስብ ብቻ ሣይሆን የሕብረተሰብ ክፍላትን በሰፊው የጠቀለለ መሆን ይኖርበታል። ይህ የአፍሪቃን ኣብያተ-ክርስቲያን ጨምሮ የዕቅዱን ድክመት የሚተቹ የተለያዩ የሲቪል ማሕበራት ዕምነት ነው።

የዓለም ባንክ በበኩሉ ለአፍሪቃ መዋቅራዊ ግንባታ ተጨማሪ ገንዘብ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አስታውቋል። ለዚሁ ተግባር በ 2000 ዓ.ም. የቀረበው ብድር 600 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ይጠጋ ነበር። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባንኩ ባለሥልጣን ሚሼል ቮርምሰር እንደገለጹት ብድሩን በዚህ ዓመት ወደ 1.6 ቢሊዮን፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ወደ 2.6 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ተወጥኗል። ሌሎች አበዳሪ ሃገራትና የግል ባለሃብቶች በዚህ አኳያ የሚያቀርቡት ገንዘብ በጠቅላላው ተደምሮ ከአምሥት ቢሊዮን አይበልጥም። ግን ይህም ቢሆን ለተግባራዊነት እንዲበቃ በባንኩ ላይ ተጽዕኖ ያላቸው ሃብታም አገሮች ዝፍጁነት ወሣኝ ነው። የእስካሁኑ ሃቅ ተሥፋን የሚያዳብር አይሆንም።