1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ባንክና የአፍሪቃ የልማት ችግር

ሐሙስ፣ ጥቅምት 17 1998
https://p.dw.com/p/E0eE

የአፍሪቃን ድህነትና ኋላ ቀርነት መታገሉ ለተቋማቸው ዋነኛው ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የተናገሩት የዓለም ባንክ አስተዳዳሪ ፓውል ቮልፎቪትስ ከሣሃራ በስተደቡብ ያለው የውቅቱ ሁኔታ ማንም ሊቀበለው የማይገባ መሆኑን አስገንዝበዋል። ሆኖም በርሳቸው አባባል የዓለም ባንክና የበለጸጉት መንግሥታት የሚያደርጉት ጥረት አፋጣኝ ስኬት እንዲያገኝ ከተፈለገ የአፍሪቃ መሪዎች ዕርምጃም እንዲሁ የሚያጅበው ሊሆን ይገባል። ድህነትን የመቀነሱን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ አፍሪቃውያን መሪዎች በቆራጥነት መነሣት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው።

የቀድሞው የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣን ዎልፎቪትስ ከ 110 የሚበልጡ መንግሥታትን ለሚወክሉት መማክርት እንዳስረዱት የዓለም ባንክ በመጪዎቹ ዓመታት ለአፍሪቃ አገሮች የአካባቢ ኤኮኖሚ ትስስር ሁኔታዎችን በሚያመቻች የመዋቅር ግንባታ ላይ በሰፊው ያተኩራል። ለሬፑብሊክ ኮንጎ፣ ለማላዊ፣ ለደቡብ አፍሪቃና ለዚምባብዌ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያቀርብ አንድ የሃይል ማመንጫ ፕሮዤ ግንቢያን በደቡባዊው አፍሪቃ ማገዙ አንዱ ዕቅዱ ነው።
የዓለም ባንክ ከሕንድ ውቂያኖስ እስከ አትላንቲክ አፍሪቃን ለሚያቋርጥ አውራ ጎዳና ግንቢያም ገንዘብ ለማቅረብ ያስባል። ቀደምት ከሆኑ የነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች ጋር በመተባበር በምዕራባዊው አፍሪቃ የጋዝ ማስተላለፊያ ባምቧ መዘርጋቱም ዎልፎቪትስ እንዳስረዱት ሌላው ዕቅዱ ነው። ይህ በወቅቱ የተፈጥሮ እንክብካቤ ተሟጋቾች የሚቃወሙት ፕሮዤ ቢጠናቀቅ የተፈጥሮ ጋዝን ከናይጄሪያ ወደ ቤኒን፣ ቶጎና ጋና ማስተላለፍ የሚችል ይሆናል።

እርግጥ ባንኩ በነዚህ መዋቅራዊ ግንባታዎች ማተኮሩ በአፍሪቃ የጤና ጥበቃና የትምሕርት ይዞታዎችን ለማሻሻል ሲያራምድ የቆየውን ተግባር ይተዋል ማለት አይደለም። ፓውል ቮልፎቪትስ በዚሁ አጋጣሚ የበለጸጉት መንግሥታትም የልማት ዕርዳታን ለማሳደግና ለድሆች አገሮች ዕዳን ለመሰረዝ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ አሳስበዋል። የዕርዳታ ተግባራቸውን በተሻለ ሁኔታ ማቀናበር ይኖርባቸዋል ባይም ናቸው።

የዓለም ባንኩ አስተዳዳሪ አያይዘው እንዳስረዱት ከበለጸጉት መንግሥታት ከሁሉም በላይ ይበልጥ የሚጠበቀው ደግሞ ዶሃ ላይ የተጀመረውን የንግድ ድርድር ወደተሳካ ፍጻሜ ማድረሳቸው ነው። የዚህ ድርድር መሳካት በዓለም ዙሪያ ከአንዲት ዶላር ባነሰች የዕለት ገቢ ኑሮውን ለሚገፋው 1,2 ቢሊዮን ሕዝብ ሁኔታ መሻሻል ወሣኝ ነው ተብሏል። በካታር ርዕሰ-ከተማ ስም የሚጠራው ይህ ድርድር የተከፈተው ከአራት ዓመታት ገደማ በፊት ነበር።

በዓለም ንግድ ድርጅት ሥር የሚካሄደው የዶሃ የልማት ድርድር ዙር ዓላማም የዓለምን ኤኮኖሚ በማዳበር በብዙ ሚሊዮን የሚቀጠር ሕዝብን ከድህነት ማላቀቅ ነው። ለድርድሩ መጓተት ዓቢይ ምክንያት ሆኖ የሚገኘው የበለጸጉት መንግሥታት አሜሪካን ጨምሮ ለገበሬዎቻቸው የሚሰጡትን ድጎማ ለመቁረጥ ፈቃደኝነት አለማሳየታቸው መሆኑ ይታወቃል። ታዳጊ አገሮች በበኩላቸው ይሄው ሁኔታ የእርሻ ምርታችንን ዋጋ እያዋደቀ ነው ሲሉ ያማርራሉ። ቮልፎቪትስ እንደሚሉት ለበለጸጉት መንግሥታት ድጎማውን መቁረጡ ምናልባት አመቺ ላይሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ምቾት ለጊዜው መጓደሉ ከድሆች አገሮች ዕለታዊ ችግርና ድህነት አንጻር ሲታይ ብብደቱ ኢምንት ነው።

የፊንላንዱ የመማክርት ስብሰባ መድረክ የዓለም ባንኩ አስተዳዳሪ ፓውል ዎልፎቪትስ በዚህ ሥልጣን ሲሾሙ ተስፋፍቶ የነበረውን በልማት ጉዳይ ላይ በቂ ልምድ የላቸውም የሚል አስተሳሰብ ለማስተባበል ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ባንኩን የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ፖሊሲ መሣሪያ ያደርጋሉ ብለው የፈሩት ታዛቢዎችም ጥቂት አልነበሩም። ይሁንና አስተዳደሩን በያዙበት ከመንፈቅ ያነሰ ጊዜ እስካሁን ያሳዩት አቀራረብ የቀደምታቸውን የጀምስ ዎልፈንሰንን ቢቀር በዚህ በኢንዱስትሪ ልማት በበለጸገው ዓለም በጎ የተሰኘ አርአያ ተከትለው ለመራመድ መቁረጣቸውን የሚያመለክት ነው።

ዎልፈንሰን በ 2001 ዓ.ም. ሄልሢንኪን በጎበኙበት ጊዜ አንድ የዓለምአቀፉ ኤኮኖሚ ስርዓት ተቃዋሚ ፊታቸው ላይ የፍራፍሬ ክሬም ወርውሮባቸው እንደነበር ይታወሳል። ባለፈው ሰንበት ዎልፎቪስ ይህ ዕጣ አልገጠማቸውም። ምናልባት ምክንያቱ የጸጥታ ጥበቃው መጠናከር ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም 300 ገደማ የሚጠጉ ሰዎች አሁንም ዝናብ ሳይበግራቸው ከፊንላንድ ም/ቤት ፊትለፊት በመሰለፍ በዎልፎቪትስና በባንካቸው ላይ ተቃውሞ ማሰማታቸው አልቀረም። ተቃዋሚዎቹ ካነገቧቸው መፈክሮች መካከል በአሜሪካ የኢራቅ ወረራ ወቅት የባለሥልጣኑን ሚና በማስመልከት “ፓውል ዎልፎቪትስ በሕዝብ ፍጅት የሚፈለጉ” የሚል ይገኝበት ነበር።

በጉባዔው አዳራሽ ውስጥ የታየው ሁኔታ ግን ከዚህ ለየት ያለ ነው። የስዊድኑ እንደራሴ ካይ ኖርድኩዊስት ለምሳሌ ዎልፎቪትስ እንዳሉት የሚራመዱ ከሆነ ጥሩ ስራ እንደሚሰሩ ተሥፋን የሚያጠናክር ነው ሲሉ ቁጥብነት በተመላው መልክ ቢሆንም ተናግረዋል። እርግጥ የዓለም ባንክ በቀድሞ ፖሊሲው በአፍሪቃ ስሕተት መፈጸሙን ዎልፎቪትስ ተረድተዋል ያሉ አንዳንድ ወገኖች ባይታጡም ጥርጣሬያቸውን የሚገልጹትም ገና ብዙዎች ናቸው።

በዓለም ባንክና በዓለምአቀፍ መማክርት መካከል የፖሊሲ ውይይት መድረክ የሆነው 800 እንደራሴዎችን ያቀፈ ነጻ ስብስብ ዓላማ ድህነትን መታገልና በዓለምአቀፉ ልማት ሂደት ግልጽነትና አስተማማኝነትን ማራመድ ነው። ያለፈው ሰንበት ውይይት ከያዝነው ዓመት ልማት ባሻገር የወደፊቱስ እንዴት? በሚል ጥያቄ ላይ ያተኮረ ነበር።

ተሰናባቹ የስብስቡ ሊቀ-መንበር የኔዘርላንዱ እንደራሴ በርት ኮንደርስ ይህን ሊገባደድ የተቃረበውን 2005 ዓ.ም. የቃል ኪዳን ዓመት ብለውታል። ሆኖም መማክርቱ ነቅተው ጉዳዩን ካልተከታተሉና በየመንግሥታቱ ላይ ግፊት ካላደረጉ ሁሉም ሳይሟላ የሚቀር ነገር ነው የሚሆነው። በርሳቸው አስተሳሰብ በልማቱ ክርክር ላይ የውሣኔ ድምጽ የሚሰጡት እንደራሴዎች ተሳትፎ ሊጓደል አይገባውም።

G-8 በመባል የሚጠሩት ቀደምት በኢንዱስትሪ ልማት የተራመዱ መንግሥታት መሪዎች ባለፈው ሐምሌ ወር በስኮትላንድ ግሌንኢግልስ በተባለች ስፍራ ለ 18 የድሃ-ድሃ ተብለው ለተመደቡ አገሮች በዓለም ባንክና በምንዛሪው ተቋም IMF ዘንድ ያለባቸውን ዕዳ ሙሉ በሙሉ ለመሰረዝ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም። ከነዚህም አብዛኞቹ፤ ማለት 14ቱ የአፍሪቃ አገሮች ናቸው። ግን እስካሁን ቃሉ ከቃል አልፎ በተግባር አልተተረጎመም።
አንድ በፊንላንዱ ጉባዔ የተሳተፉ የኡጋንዳ እንደራሴ “የዕዳ ስረዛ የፒንግ-ፖንግን ጨዋታ ያህል ሆኗል” ሲሉ ነው ባዶ ቃል ሆኖ መቀጠሉን በትዝብት የተናገሩት። ከአፍሪቃ እስከ አውሮፓ ለዕዳ ምሕረት የሚቀሰቅሱ የተግባር ቡድኖችም አንዳንድ ሃብታም አገሮች፣ የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቋም በወቅቱ ማን ምን ያህል እንደሚከፍልና በአፈጻጸሙ ሂደት በመወዛገብ፤ እንዲሁም የዕዳ ምሕረት ይደረግላችኋል በተባሉት አገሮች ላይ ተጨማሪ ግዴታዎችን በመጫን ቃሉን እያጠፉ ነው ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪ የዶሃው የንግድ ድርድር ዙር ንግግርም የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ የእርሻ ድጎማን በመቀነሱ አኳያ ባለቸው ልዩነት ፈሩን እንዳይለቅ ማሳሰቡ አልቀረም። የዓለም ንግድ ድርጅት ጠቅላይ አስተዳዳሪ ፓስካል ላሚይ ከጀኔቫ በቪዲዮ ግንኙነት ለጉባዔው ባስተላለፉት መልዕክት ለታዳጊ አገሮች የእርሻ ምርቶች ገበዮችን በመክፈቱ በኩል የአሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት የመደራደሪያ አቋሞች አሁንም በጣሙን ይለያያሉ።

ከዚህ አንጻር የዶሃው የልማት ንግግር ከተሳካ ፍጻሜ መድረሱ ሲበዛ የሚያጠያይቅ ነው። በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት በዚህ ገበዮችን ለታዳጊ አገሮች በመክፈቱ ጉዳይ ለአያሌ ዓመታት ግትር አቋም ይዘው ነው የቆዩት።