1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኃይልምንጭ-ውይይት መድረክ በቦን

ሐሙስ፣ ግንቦት 12 1996

በዓለም ውስጥ የታዳሽ ኃይል-ምንጮች ልማት እንዲነቃቃ ለማድረግ ይቻል ዘንድ፣ በሰኔ መጀመሪያ ላይ ቦን ውስጥ አንድ ዓለም-አቀፍ የውይይት መድረክ ይከፈታል።

https://p.dw.com/p/E0fi

አዘጋጁና ጋባዡ የጀርመን መንግሥት ነው። ይኸው ዓለም-አቀፍ የታዳሽ ኃይል-ምንጮች መድረክ ከመከፈቱ በፊት በጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ፣ “ኦይሮሶላር” የተሰኘው የአውሮጳው ተቋም ከግንቦት ፳፩ እስከ ግንቦት ፳፫ ለተመሳሳይ ውይይት ጥሪ አስተላልፏል። በዚሁ መድረክ ላይ ስለ ታዳሽ ኃይል-ምንጮች ልማት ከመላው አህጉራት የቀረቡት ሐሳቦች ናቸው ክርክር የሚደረግባቸው።

የዓለምን ኃይል-ምንጭ ይዞታ እና የተፈጥሮን ጥያቄ የሚመለከተው የሰሞኑ ዓለም-አቀፍ የውይይት መድረክ ከጥቂት የመንግሥት ወኪሎች በስተቀር በተለይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው የሚሳተፉበት። የእነርሱ የጋራ ግብ የፀሐይን ብርሃን እና የነፋስን ኃይል የመሳሰሉት፣ ለተፈጥሮ ጓዳ ጭነት የማይሆኑት ታዳሽ የኃይል ምንጮች በዓለም-አቀፍ ደረጃ በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውሉበት የአማራጩ ርምጃ ትግበራ ነው።

የዓለም ኃይልምንጭ ጉዳይ መማክርትና በአውሮጳ የታዳሽ ኃይልምንጮች ተመልካች ድርጅት ሊቀመንበር ኼርማን ሼር ስለግቡ ክትትል ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፥ “.........እኛ አሁን ግልጽ አድርገን ለማሳየት የምንፈልገው፥ የዓለም ሕዝብ የሚያስፈልገው መላው የኃይል ምንጭ አቅርቦት በታዳሽ የኃይል ምንጮች ሊሸፈን የሚችል መሆኑን፣ ይኸው የታዳሽ ኃይልምንጮች ግብዓት ለመላው የዓለም ኤኮኖሚ ዕድገት ጠቀሜታን እንደሚያመጣ፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮች በዛሬው የአቶም ኃይልና ከሰልን በመሳሰሉት የተፈጥሮ ቅሪቶች አገልግሎት ቦታ ለመተካት ብቃት የላቸውም የሚለው አነጋገር ትክክለኛ አለመሆኑን ነው። የዚህ ዓይነቱ ያጋደለ አስተሳሰብ ሥልጣኔ ያመጣው ውሸት ነው።

ባሁኑ ጊዜ ንግዳዊው የኃይል ምንጭ አቅርቦት ከ፺ በመቶ በበለጠ ደረጃ በተፈጥሮ ቅሪቶች ወይም በአቶም ኃይል ነው የሚሸፈነው። የምድር ጋዝን፣ የምድር ዘይትን እና ከሰልን የመሳሰሉት የተፈጥሮ ቅሪቶች የሆኑት የኃይል ምንጮች ከእለታት አንድ ቀን ተሟጥጠው የሚያልቁ እንደመሆናቸው መጠን አሁን አማራጩ መነቃቃትና መጠናከር አለበት። ከዚህም በላይ እነዚሁ የተፈጥሮ ቅሪቶች በኮሬንቲ ብርሃን ወይም በሙቀት መልክ ወደኃይል-ምንጭነት እንዲለወጡ የሚደረግበት ርምጃ ብዙ የተን ብክለትን ያስከትላል። እነዚሁ ሁለት እክሎች ለታዳሾቹ እና ለንፁሆቹ የኃይል ምንጮች አማራጭነት ዓይነተኛውን ትርጓሜ ነው የሚሰጡት። ፀሃይ፣ ነፋስ፣ እፀዋት፣ እና ውሃ በመሠረቱ ተሟጥጠው የሚያልቁ አይደሉም፣ የሚያስከትሉት ሥጋት የለም፣ የጎን ጉዳት አያደርሱም።

ዓለምአቀፉ የኃይል ምንጭ ውይይት መድረክ አማራጩን ብቻ ሳይሆን፣ ተጨባጭ የርምጃ እርከኖችንም ለማሳየት ነው የሚሻው። መድረኩ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚዘረጋው መርሐግብር፥ የሰው ልጅ የኃይምንጭ ችግሩን በተቻለ ፍጥነት ሊወጣው የሚችልበትን መንገድ ያሳያል ነው የሚባለው።

ወደፊት ለአውቶሞቢሎች አስፈላጊ የሚሆነውም ማሽከርከሪያ ኃይል ጭምር ነው አሁን የውይይት ክብደት የሚያገኘው። በቤንዚንና በናፍጣ የሚንቀሳቁት ተሽከርካሪዎች በሚሊዮን ቶን የሚታሰብ የተን ብክለት ነው ወደ አየር የሚረጩት። የድፍድፍ ዘይቱ ንጣፍ በየጊዜው እያነሰ በሚሄድበት ወቅት በተለይም ወደ እንዱስትሪያዊው ዕድገት በተቃረቡት የእስያ ሀገራት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ነው መጀመሪያውን አውቶሞቢል ለማሽከርከር የሚጣደፈው። በዚህ አኳኋን፣ ወደፊት የኃይል ምንጭ ፍላጎትና ፍጆታ እየገዘፈ የሚገኝ መሆኑ ነው። ጥያቄው ታዲያ፥ የወደፊቱ የኃይል ምንጭ ይዘት እንዴት ሊሆን ነው? የሚል መሆን አለበት።

ለተታዳሽ የኃይል ምንጮች ከፍተኛውን ትርጓሜ የሚሰጡት ጠበብት እንደሚሉት፣ የታዳሾቹ የኃይል ምንጮች አገልግሎት እንዲነቃቃ የሚያደርጉ ዓለምአቀፍ ተቋማትን መመሥረት አንድ ርምጃ ሲሆን፣ ሌላው ርምጃ ደግሞ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሥነተፈጥሮአዊ ቀውሶች የሚወገዱበትን ሁኔታ የሚመለከት ነው። አሁን ሰሞኑን ቦን ውስጥ የሚካሄደው የታዳሽ ኃይልምንጮች ውይይት መድረክ ኅብረተሰቡ ይህንኑ ዓቢይ ጥሪ ለመቀበል ምን ያህል ዝግጁነት እንዳለው የሚያሳይ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው።