1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ መክሸፍ

ሰኞ፣ መስከረም 4 1996
https://p.dw.com/p/E0gK

በካንኩን፡ ሜክሲኮ ካለፈው ረቡዕ እስከ ትናንት ድረስ የተካሄደው አምስተኛው የዓለም ንግድ ድርጅት የሚንስትሮች ጉባዔ ካላንዳች ውጤት አበቃ። በኢንዱስትሪ መንግሥታትና በድሆቹ የዓለም ሀገሮች መካከል መፍትሔ ሊገኙላቸው ያልቻሉ በርካታ ንግድ ነክ ጉዳዮች፡ ለምሳሌ፡ ለግብርና ምርት የሚሰጠው ድጎማ እንዲቋረጥ፡ እንዲሁም የንግዱ ማከላከያ ገደቦች እንዲነሡ የቀረቡት መሰል ጥያቄዎች ለጉባዔው ክሽፈት ተጠያቂ ናቸው። ይህንኑ የከሸፈውን የሚንስትሮች ጉባዔ ቀደም ሲል ከተደረጉት ሌሎቹ የድርጅቱ ጉባዔዎች ልዩ ያደረገው ጉዳይ በመልማት ላይ ያሉት ሀገሮች ለመጀመሪዪዜ አንድ አቋም ይዘው በመቅረብ በአንድ ድምፅ የተደራደሩበት ሁኔታ ነው።

እርግጥ፡ የተለያየ የልማት ደረጃና የፖለቲካ ፖሊሲ ያላቸው አዳጊዎቹ ሀገሮች በካንኩን ጉባዔ ላይ ተሰሚነት ለማግኘት እና ተፅዕኖ ለማሳረፍ ከፈለጉ አንድ ሆነው የሚቀርቡበት ድርጊት ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው በመገንዘብ ነበር አንድ አቋም ይዘው የተደራደሩት። ይኸው አቋማቸው የበለፀጉት ኢንዱስትሪ መንግሥታቱ በጉባዔው ላይ ላሳርፉባቸው ግፊትና ድጋፋቸውን ለመሳብ ላደረጉት ማባበያ እንዳይንበረከኩ ኃይል ሰጥቷቸዋል። የጉባዔው ተሳታፊዎች በጠቅላላ በስብሰባው መጨረሻ ላይ ፍሬ አልባ የሆነ ስምምነት ከመድረስ ይልቅ ጉባዔው ቢከሽፍ እንደሚሻል ነበር በውሳኔአቸው ያጎሉት። አዳጊዎቹ ሀገሮች በዓለሙ ንግድ ሥርዓት ላይ ጠንካራ ድርሻ እና ተጨማሪ ትርፍ የማያስገኝላቸውን ስምምነት ለመድረስ ዝግጁ አለመሆናቸውን አረጋግጠዋል። የካንኩን ጉባዔ ካለውጤት የተበተነበት ድርጊት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኘውን የዓለም ኤኮኖሚ የበለጠ አደጋ ላይ እንዳይጥለው የኤኮኖሚ ጠብት ሠግተዋል።በኢንዱስትሪ ጎዳና በማኮብኮብ ላይ የሚገኙት ቻይናን፡ ሕንድን፡ ብራዚልንና ግብፅን የመሣሠሉት ሀገሮች በሜክሲኮ ጉባዔ ላይ አዳጊዎቹን ሀገሮች በወከለውና ራሱን ቡድን ሀያ አንድ ብሎ በጠራው ቡድን ውስጥ ተጠቃለዋል። ቦሊቪያ፡ ኩባ፡ ፔሩ እና ኤኳዶርን የመሣሠሉት ድሆቹ ሀገሮች፡ ኤኮኖሚያዊ ልማታቸው ከፍተኛ የሆኑት ቺሌና ታይላንድ፡ እንዲሁም፡ ከሌሎች አዳጊ ሀገሮች በጠቅላላ ባንድ በኩል አንዱ የሕዝቡዋ ከፊል በላቀው ብልፅግና፡ ሌላው ከፊል ደግሞ በከፍ ድህነት ውስጥ የሚኖርባት ደቡብ አፍሪቃም ጭምር የዚሁ ቡድን አባላት ናቸው። ይኸው ቡድን ከዓለም ሕዝብ መካከል ከግማሽ በላይ የሚበልጠውን ነው በካንኩን ስብሰባ ላይ የወከለው። የዓለም ንግድ ድርጅት የሚንስትሮች ጉባዔ የከሸፈበት ድርጊት ሁሉን ተሳታፊዎች፡ በተለይ ግን ተጠቃሚ ለመሆን የፈለጉትን ኢንዱስትሪ መንግሥታትን ጎድቶዋል። ወደፊት በዓለም ንግድ ፖለቲካ ላይ የመሻሻል ሂደት ለማስገኘት ከተፈለገ፡ ኢንዱስትሪ መንግሥታቱ አዳጊዎቹን ሀገሮች የሚያሳትፍና ሁነኛ ጥቅም የሚያስገኝላቸውን አንድ የውይይት ዙር መክፈት እንደሚኖርባቸው የካንኩን ጉባዔ ግልፅ እንዳደረገላቸው ጠብብት ገምተዋል።