1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚና የምንዛሪው ተቁዋም ሚና

ረቡዕ፣ መጋቢት 9 2001

የቡድን-ሃያ የፊናንስ ተጠሪዎች ባለፈው ሰንበት ተገናኝተው በቅርቡ ለንደን ላይ በመሪዎች ደረጃ ለሚካሄደው የዓለም የፊናንስ ጉባዔ የዝግጅት ስብሰባ አድርገው ነበር።

https://p.dw.com/p/HEuv
የእንግሊዝና የአሜሪካ ፊናንስ ሚኒስትሮች
የእንግሊዝና የአሜሪካ ፊናንስ ሚኒስትሮችምስል AP

በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉትን ቀደምት መንግሥታትና በተፋጠነ ዕድገት ላይ ያሉ ሃገራትን የጠቀለለው የቡድን-ሃያ የፊናንስ ተጠሪዎች ባለፈው ሰንበት ተገናኝተው በቅርቡ ለንደን ላይ በመሪዎች ደረጃ ለሚካሄደው የዓለም የፊናንስ ጉባዔ የዝግጅት ስብሰባ አድርገው ነበር። በስብሰባው የዓለምን ኤኮኖሚ መልሶ በዕድገት አቅጣጫ ለማራመድ አስፈላጊው ጥረት ሁሉ እንደሚደረግ ቃል ተገብቷል። የወቅቱን የኤኮኖሚ ቀውስ በጋራ በተመታገሉ ረገድ የዓለምአቀፉን የምንዛሪ ተቁዋም ሚና ለማጠናከር መታሰቡም ነው የተነገረው። ይሁንና ችግሩን ለማሽነፍ የተቻለው ጥረት ሁሉ እንደማይጓደል ቃል ቢገባም በሌላ በኩል ቻይና መጪው ጉባዔ ፍሬ መስጠቱን አጠያያቂ ማድረጓ አልቀረም። በምንዛሪው ተቁዋምም ሆነ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ስርዓት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል ባይ ናት። ግን ይህ በወቅቱ ገቢር ከመሆን የራቀ ጉዳይ ነው የሚመስለው።

የቡድን-ሃያ መንግሥታት የፊናንስ ሚኒስትሮች የዓለም ኤኮኖሚን እንደገና በዕድገት አቅጣጫ ለማራመድ፣ የፊናንስ ገበዮችን ጠበቅ ባለ መልክ ለመቆጣጠርና የተሽመደመደውን የባንኮች የብድር ተግባርም ለማነቃቃት ከጋራ ስምምነት መድረሳቸውን ተናግረዋል። ባለፈው ታሕሣስ ዋሺንግተን ላይ የተጀመረው የዓለም የፊናንስ ጉባዔ አሁን በተከታዩ ስብሰባው ለዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ጭብጥ ምላሽ ለመስጠት ከሚችልበት ደረጃ እንደሚደርስ ነው የሚታመነው። የብሪታኒይ የፊናንስ ሚኒስትር አሊስቴር ዳርሊንግ ስብሰባው እንዳበቃ በሰጡት መግለጫ የውሣኔውን ይዘት እንዲህ ነበር የዘረዘሩት።

“በርካታ የፊናንስ ሚኒስሮችና የማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪዎች በፊታችን መጋቢት 24 ቀን ለንደን ላይ ለሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ዝግጅት ለማድረግ ባለፈው ምሽትና በዛሬው ዕለት ሂደት ተሰብስበው ነበር። በዚሁ ስብሰባ ዓለምአቀፉን የፊናንስ ስርዓት ለመጠገንና ለማጠናከር ተስማምተናል። በተጨባጭ ቀውሱ እንዳይደገም ማድረጉን በተመለከተ አጣዳፊ ዕርምጃ እንደሚያስፈልግ የሁላችንም ዕምነት ነው። ከመግለጫችን መረዳት እንደሚቻለው የሥራ ቦታዎችን ለማስፋፋት ወሣኝና መሠረታዊ ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ። በአጠቃላይ ዕድገት መልሶ እንዲሰፍን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን”

በሚኒስትሮቹ ዕምነት ዓለምአቀፉ የምንዛሪ ተቁዋም IMF በገንዘብ ችግር ላይ የሚወድቁ ሃገራትን ፈጣንና ፍቱን በሆነ መንገድ እንዲደግፍ ብቃት ይኖረው ዘንድ የፊናንስ አቅሙን ከፍ ማድረጉ አስፈላጊ ነው። ቀውሱን ለመታገል ወደፊት በሚፈሰው የኤኮኖሚ ማነቃቂያ በጀት ዕቅድ ላይ የተፈጠረው አለመግባባትም ከሞላ-ጎደል በሰፊው በረድ ማለቱ ይታመናል። ከዚሁ በተጨማሪ ማንኛውንም የብሄራዊ ገበያ እገዳ በሁሉም መልኩ ለመታገል፣ የመዋዕለ-ነዋይ ፍሰትን ለማጠናከርና ንግድንም ወደፊት ለማራመድ ከስምምነት ተደርሷል። አሊስቴይር ዳርሊንግ ቀጠል አድርገው ያስረዱት ቡድኑ ከተፈለገ የበለጠ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም ነው።

“በተለያዩ አገሮች ከአሁኑ የተወሰዱ ጠቃሚ ዕርምጃዎች አሉ። ሆኖም ከተፈለገ የበለጠ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን ግልጽ አድርገናል። አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው የባንኮችንና የሌሎች መሰል የፊናንስ ተቁዋማትን የማበደር አቅም መልሶ ማስፈንና ኪሣራን መሽፈን በሚያስችል ዕርዳታ ለማገዝ በጋራ አስፈላጊ የሆኑትን ዕርምጃዎች መውሰድ ነው”

የቡድን-ሃያ የፊናንስ ሚኒስትሮች የጋራ መግለጫ ከሁለት ሣምንታት ገደማ በኋላ ለንደን ላይ በሚካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ከምን ዓይነት አስታራቂ ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚችል ቢቀር በአዝማሚያ ደረጃ የሚጠቁም ነው። የኤኮኖሚው ዘርፍ በቂ ብድር እንዲያገኝና ባንኮችም ወደፊት በመረዳት በመቀጠላቸው ጉዳይ የመግባባት ሁኔታ ነው የሚታየው። በሌላ አነጋገር የወለድ ቅነሣ፣ መንግሥታዊ የብድር ዋስትናና ምናልባትም መንግሥት ኪሣራ ባሰጋቸው የግል ባንኮች ውስጥ እነዚሁኑ ከውድቀት ለማትረፍ ድርሻ የመያዙ ዕርምጃ ቀጣይነት ይኖራቸዋል።
ይህ ሁሉ የሚታሰበው እርግጥ ጀርመንንና ፈረንሣይን የመሳሰሉት መንግሥታት የኤኮኖሚውን ዘርፍና ባንኮችን ሕዝብ በሚከፍለው ግብር በመደጎም ለመቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው ማስረገጥ በያዙበት ወቅት ነው። ይህም የጋራ ዕርምጃ የመውሰድ ብቃት መኖሩን ጥቂትም ቢሆን አጠያያቂ ያደርገዋል። ለምሳሌ ያህል የጀርመኑ የፊናንስ ሚኒስትር ፔር ሽታይንብሩክ ተጨማሪ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ በጀት የማፍሰስ ፍላጎት እንደሌላቸው በሰንበቱ ስብሰባ እንደገና አስረግጠዋል። ከዚህ አንጻር ተቃራኒውን ዕርምጃ ከሚሹ ሃገራት ጋር ምናልባት ሊኖር የሚችለው አስታራቂ ሃሣብ መንግሥት ለባንኮች የሚሰጠውን የፊናንስ ድጋፍ በቅድመ-ግዴታዎችና በጊዜ ገደብ የሚወስን ነው የሚሆነው።

በዚህ ጉዳይ በአንድ በኩል በአውሮፓ አገሮች መካከል በሌላ በኩልም በአውሮፓና በአሜሪካ መካከል የአመለካከት ልዩነት አለ። በፊናንስ ሚኒስትሮቹ ስብሰባ አኳያ ለንደን ላይ ተገናኝተው የተነጋገሩት የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ አንጌላ ሜርክልና የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጎርደን ብራውንም ይሁንኑ በማጤን ሙሉ ስምምነት ይገኛል ለማለት አልደፈሩም። በርከት ባሉ ነጥቦች ላይ አስታራቂ ስምምነት እንደሚኖር ነው ዕምነታቸውን የገለጹት።
መለስ ብሎ ለማስታወስ ያህል የአሜሪካ ባለሥልጣናት በብሪታኒያና በጃፓን በመደገፍ ይበልጡን በመንግሥት የተደገፈ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ዕርምጃን ሲከተሉ ቆይተዋል። አውሮፓውያን አገሮች በአንጻሩ ከዚህ መሰሉ ዕርምጃ ይልቅ የበለጠ ደምብና ቁጥጥርን ይመርጣሉ። ጎርደን ብራውን በመጪው የመሪዎች ጉባዔ ምን ያህል የአውሮፓውያኑን ሃሣብ እንደሚቃረቡ በወቅቱ ግልጽ አይደለም። የሆነው ሆኖ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ባለፈው ታሕሣስ ዋሺንግተን ላይ ተካሂዶ እንደነበረው የመጀመሪያው የዓለም የፊናንስ ጉባዔ መጪው የለንደን ጉባዔ በበጎ ፍላጎት መግለጫ ተወስኖ እንደማይቀር ዕምነታቸው የጠነከረ ነው።

“የአሁኑ ጉባዔ ዓላማ ፍሬ ማግኘት፤ ውጤት ላይ መድረስ ይሆናል። እና በበኩሌ አሁን ተሥፋዬ የላቀ ነው። ከተደረገው ዝግጅት አንጻር አግባብ ባለው ደምብና ክትትል ይህን መሰሉ ቀውስ እንዳይደገም ለማድረግ ከአሜሪካ፤ ቻይናንና ሕንድን ከመሳሰሉት ሃገራት ጋር ከአንድ ውጤት እንደምንደርስ ጽኑ ዕምነቴ ነው”

በሰንበቱ የቡድን-ሃያ የሚኒስትሮች ስብሰባ ምናልባት በአውሮፓና በአሜሪካ መካከል የሃሣብ መቀራረብ አዝማሚያ ታይቶ ይሆናል። ግን ይህ ስልታዊ ለሆነ የጋራ ስምምነት መብቃቱ ገና በገቢር መታየት የሚኖርበት ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ዕድገትን መልሶ በማስፈኑ ረገድ በአሜሪካና በአውሮፓ መካከል ያለውን ልዩነት ቻይና በመጪው ጉባዔ ለፊናንስ ስርዓት ለውጥ አጀንዳዋ ልትጠቀምበት ትችላለች። ሕዝባዊት ቻይና ለነገሩም ከመጪው የለንደን የቡድን-ሃያ የመሪዎች ጉባዔ የምትጠብቀው ውጤት ዝቅተኛ ነው። የቀድሞው የቻይና ሕዝባዊ ባንክ ምክትል አስተዳዳሪ ዉ ቺያዎሊንግ ባለፈው ሰንበት ሻንግሃይ ላይ በተካሄደ የፊናንስ ጉባዔ ላይ ጉባዔው ፍሬ መስጠቱ አጠያያቂ ነው ነበር ያሉት።

ቺያዎሊንግ እንዳሉት በቡድን-ሃያ የመሪዎች ስብሰባ ጭብጥ ውጤት ማግኘቱ የማይቻል ነገር ነው። በመሆኑም ቻይና በዚሁ ላይ ተሥፋ ከመጣል ይልቅ የራሷን ድምጽ ማሰማት ይኖርባታል። ቻይና በእርግጥም የክብደቷን ያህል ተጽዕኖ ከማድረግ አልተቆጠበችም። በቡድን-ሃያ ጉባዔ የዝግጅት ሂደት እስካሁን ንቁ ተሳታፊ ሆና ነው የቆየችው። ግፊቷም መሠረታዊ በሆነ የፊናንስ ስርዓት ለውጥ ላይ ያለመ ነው። የአገሪቱ የፊናንስ ሚኒስትር ቺ-ቹዌሬን በሰንበቱ ስብሰባ ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብ የዓለም የፊናንስ ተቁዋማት ለውጡን እንዲያፋጥን፤ እንዲሁም ፍትሃዊ፣ አቅድ ያለውና ፍቱን አዲስ የፊናንስ ስርዓት እንዲያንጽ ነበር ጥሪ ያደረጉት።

ዉ ቺያዎሊንግም ከሻንግሃይ የሚኒስትሩን ሃሣብ በማጠናከር የበለጸጉት መንግሥታት የታዳጊ አገሮችን ጥቅም በመጠበቁ ረገድ የበለጠ ሃላፊነት መሽከምና ቻይናን ለመሳሰሉት ተራማጅ ሃገራት በዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቁዋም ውስጥ የበለጠ ሥልጣን መስጠት እንዳለባቸው አስረግጠዋል። በዉ አባባል IMF የተራማጆቹን አገሮች ድርሻ ማሳደግና ሁሉንም ዓባላቱን እኩል ማስተናገድ አለበት። ትኩረቱ በተለይ በሃያላን መንግሥታት ላይ ነው። ግን በሰንበቱ የቡድን-ሃያ ስብሰባ እንደታየው የወቅቱ አዝማሚያ በምንዛሪው ተቁዋም መጠናከር እንጂ ተሃድሶ ላይ አላተኮረም። ይህ ደግሞ መጪውን የመሪዎች የፊናንስ ጉባዔ ይብሱን ሊያከብድ የሚችል ነው።

ለግንዛቤ ያህል በአሕጽሮት BRIC በመባል የሚታወቁት አገሮች፤ ማለት የብራዚል፣ የሩሢያ፣ የሕንድና የቻይና የድምጽ መብት በ IMF ውስጥ ከጠቅላላው በ 9,6 ከመቶ ገደማ ብቻ የተወሰነ ነው። የሁሉም ድምጽ ተጣምሮ ደግሞ አሜሪካ ካላት ድምጽ ከግማሹ እንኳ አይበልጥም። በዚሁ የተነሣም አንዳንድ የቻይና የኤኮኖሚ ጠበብት አሜሪካ በተቁዋሙ ውስጥ ያላት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እስካልተነሣ አገሪቱ ለምንዛሪው ተቁዋም ገንዘብ እንዳታወጣ እስከማንስጠንቀቅ ነው የደረሱት።
በቻይና የማሕበራዊ ሣይንስ አካዳሚየ ዓለም ኤኮኖሚና ፖለቲካ ጥናት ዘርፍ ፕሬዚደንት ዩ ዮንግዲንግ እንዳስረዱት ቻይና ብዙ ገንዘብ ብታፈስ እንኳ በዓለምአቀፉ የፊናንስ ተቁዋማት ውስጥ የበለጠ ክብደት ልታገኝ አትችልም። ለዚሁም ምክንያቱ አሜሪካ በምንዛሪው ተቁዋም የውሣኔ አሰጣጥ ሂደት ቬቶ ስላላት ነው። የቻይና ፍላጎት ምንም ሆነ ምን ከፊናንስ እስከ ንግድ በዓለምአቀፉ ተቁዋማት ውስጥ ፍትሃዊ ለውጦች ካልሰፈኑ አሁን ዓለምን ያናጋው የኤኮኖሚ ቀውስ ወደፊት እንዳይደገም ማድረግ መቻሉ አጠራጣሪ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ