1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ኤኮኖሚ በተፈፀመው ጎርጎራዊ ዓመት ፪ሺ፬ እንዴት ነበር?(፩)

ሐሙስ፣ ጥር 5 1997

የዓለም ኤኮኖሚ መነቃቃት ተስኖት የቆየባቸው ዓመታት አብቅተው፣ አሁን በአዲስ የዕድገት ዘመን መተካታቸው ይሆን? የትኛው የዓለም አካባቢ ነው እጅግ ጠንካራው ዕድገት የሚንፀባረቅበት? የትኞቹስ ድርጊቶች ነበሩ ለዓለም ኤኮኖሚ የተለየ ትርጓሜ የነበራቸው? ለእጅግ ምቹው የኤኮኖሚ መፋፊያ ቦታ በሚደረገው ውድድር ረገድ አንድ አማራጭ አለን?

https://p.dw.com/p/E0f4

በዛሬው ዝግጅታችን፥ እንደ ጎርጎራዊው አቆጣጠር የተፈፀመውን ዓመት ፪ሺ፬ መለስ ብለን በመመልከት፣ ለእነዚሁ ጥያቄዎች ትኩረት እንሰጣለን፤ ዛሬ የምናቀርበው፥ የዚሁኑ ሐተታ መጀመሪያ ከፊል ሲሆን፣ ሁለተኛው ከፊል በሚቀጥለው ሣምንት ይለጥቃል።

የዓለም ኤኮኖሚ ሦሥት ዓመታት ሙሉ በብዛት ጨጋጋ ሁኔታ ሲታይበት ከቆየ በኋላ፣ አሁን በተፈፀመው ዓመት ፪ሺ፬(እጎአ) ነው የተሻሻለ ሁኔታ ሊንፀባረቅ የበቃው። በዚህ አኳኋን፣ በተባ መ የንድግድና የልማት ድርጅት(ኡንክታድ)፣ እንዲሁም በዓለምአቀፉ ገንዘብ-መርሕ ተቋም(ኣይኤምኤፍ) ጠበብት ግምገማ መሠረት፣ የዓለም ኤኮኖሚ በ፪ሺ፬ ሂደት ያገኘው ዕድገት ተጠቃልሎ ሲታይ በአራት እና በአምስት በመቶ መካከል ነው የሚሆነው። እጅግ ጠንካራ ዕድገት የሚንፀባረቅበት የደቡብና የምሥራቅ እስያ ሀገሮች ኤኮኖሚ በአማካይ ኣሃዝ ሰባት በመቶ የዳበረ ሆኖ ነው የሚታየው። ከእነዚሁ የእስያ ሀገሮች መካከል በተለይም ግዙፊቱ ቻይና ናት በገበያው ጥቅም ረገድ ዛሬ እጅግ የምታስጎመዥ ሀገር ለመሆን የበቃችው። ዛሬ ከየዘርፉ ብዙ እንዱስትረኞች ናቸው የደሞዙ ደረጃ ርካሽ የሆነበትን ግዙፉን የቻይና ገበያ የሚያልሙት። በተለይም ቻይና ከሦሥት ዓመታት በፊት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከሆነች ወዲህ ነው እጅግ የሚያስጎመዠው ግዙፉ ገበያዋ የበለጠውን ትርጓሜ ያገኘው። በዚህም ምክንያት ነው፥ ለምሳሌ የጀርመን መራሔመንግሥት ጌርሃርት ሽረደር፣ ከቅርብ ጊዜ በፊት ቻይናን በጎበኙበት ወቅት ለጀርመን እንዱስትሪ-ኩባንያዎች የግዙፍ ጥቅሙን ጎዳና በማለስለስ በብዙ የኤኮኖሚ ልዑካን እንዲታጀቡ ያደረጉት። ለኤኮኖሚያዊ ደኅንነቷ በኤክስፖርቱ ገበያ ላይ ለምትመረኮዝ፣ ጀርመንን ለመሰለች እንዱስትሪ-ሀገር ግዙፉ የቻይና ገበያ ትልቅ መስሕብ ሆኖ ነው የሚታየው።

የቻይና መሪዎች እንደሚያስረዱት፥ በ፪ሺ፬ ዓ.ም. መጀመሪያዎቹ ፲ ወራት ውስጥ የቻይናና የጀርመን ንግድ ልውውጥ ይዘት ፵፫-ነጥብ-፮ ሚሊያርድ ዶላር ደርሶ ሲገኝ፣ ይህም ከሃች ዓምናው በ፴ በመቶ የላቀ ነው። በቻይናና በአውሮጳው ኅብረት መካከል ከተደረገው ጠቅላላ የንግድ ልውውጥ፥ የጀርመኑ ድርሻ ወደ አንድ-ሦሥተኛ የተጠጋ ነበር። ከታላላቆቹ የጀርመን እንዱስትሪ-ኩባንያዎች መካከል ዛሬ በተለይ አውቶሞቢል-ፋብሪካዎች ፎልክስቫገን፣ ቤኤምቬ እና ዳይምለር-ክራይስለር፣ እንዲሁም የንጥረነገር እንዱስትሪው ቤኣኤስኤፍ እና ኤሌክትሮኒኩ እንዱስትሪኩባንያ ዚመንስ ናቸው ቻይና ውስጥ ቅርንጫፎችን ከፍተው ጠንካራ የገበያ ተሳትፎ የሚያደርጉት።

በሌላው በኩል ደግሞ፥ ቻይና ውስጥ ገስጋሹ የኤኮኖሚ ተሐድሶ ለውጥ ራሱ ከሚደቅነው ወፍራም ጥቅም ጎን ብዙ እክሎችንም የሚያስከትል መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ርግጥ፥ ቻይና ውስጥ በጠቅላላው ሲታይ የተድላው ኑሮ ከፍ ነው ያለው፣ ግን በሐብታምና በድሃ መካከል ያለው ክፍተት ይብሱን እየገዘፈ ነው የተገኘው። ይኸው ሁኔታ በ፪ሺ፬ ሂደት ብሶትን ቀስቅሶ፥ የሥራ ማቆምን አድማ፣ ማኅበራዊ ውዝግብን እና የሠራተኞች መነሳሳትን ነበር ያስከተለው። ባለፈው ዘመን ለማኅበራዊው ፍትሐዊ ኑሮ ራሱን አርአያ አድርጎ ሲመለከት የነበረው የቻይና መንግሥት አሁን ራሱን ከዚሁ ኃላፊነት የሚያርቅበት ሁኔታ ነው የሚታየው። ለምሳሌ አንዱ ቻይናዊ የሥነኅብረተሰብእ መምህር እንደሚሉት፥ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ የተካሄዱት የተሐድሶ ለውጦች ያስገኙት ተድላ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው ስርጭት አለቅጥ የተዘናነፈ ነው፣ ከዚህም የተነሳ በኑሮው ጠርዝ ላይ የሚገኙትን ችግረኞች ለመደገፍ የየቦታው ባለሥልጣናት ግዙፍ ወጭ ነው የሚከሰክሱት፣ ይህም በበኩሉ የየአስተዳደር አካባቢውን የእዳ ተራራ አለቅጥ ነው የሚያገዝፈው፤ የኋላ ኋላም የሕዝብ ብሶትና ተቃውሞ ነው የሚቀሰቀሰው፤ ለማኅበራዊ ኑሮው ዝንፈት በፍጥነት ሰላማዊው መፍትሄ ካልተገኘ ሰላማዊ የነበረው ተቃውሞ በአመጽና በኃይል ተግባር የሚተካ ነው የሚሆነው።

የቻይናው ኤኮኖሚ በተፈፀመው ዓመት ፪ሺ፬ ዘጠኝ በመቶ ነበር ያደገው። ከዚህ ጋር ሲነፃፀር፥ ዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት/ኣይኤምኤፍ ለአውሮጳ ያሰላው ፪ በመቶ ዕድገት ኢምንት ሆኖ ነው የሚታየው። ሆኖም፣ መነቃቃት ተስኖት የቆየው ኤኮኖሚያቸው አሁን እንዳንሰራራ የሚገነዘቡት አውሮጳውያን ለዚሁ ለ፪ በመቶው ዕድገት ከፍተኛ ትርጓሜ ነው የሚሰጡት።

አጽናፋዊው ትሥሥር እየጎላ በሚሄድበት ባሁኑ ዘመን የሽያጭ ገበያው ውድድር በጣም ጥጥር ነው የሆነው። ስለዚህ፥ በዚሁ ጥጥር ውድድር አንፃር ምንድን ነው መደረግ ያለበት? መልሱ ግልጽ ነው፥ የደሞዝን ወጭ መቀነስ፣ የማኅበራዊ ኑሮ መደጎሚያውንም ወጭ መቀነስ፥ ይኸው ርምጃ በበኩሉ የበለጠ ተሐድሶ ለውጥ እንዲካሄድ ግዴታ ያደርጋል። ራሳቸው የዓለምአቀፉ ገንዘብመርሕ ድርጅት/ኣይኤምኤፍ የቀድሞ ሥራአስኪያጅ እና ያሁኑ የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ከለር፣ እንዲሁም መራሔመንግሥት ጌርሃርት ሽረደር እንደሚያስገነዝቡት፣ ከማስተካከያው የተሐድሶ ለውጥ በስተቀር ሌላ የሚያዋጣ አማራጭ የለም።

ይኸው አማራጭ የለውም የሚባለው የውድድር ጥያቄ፥ ሰፊ የማኅበራዊ አገልግሎት መረብ የዘረጉትን አውሮጳውያኑን ብቻ አይደለም አሁን የሚያስጨንቀው፣ ራሳቸው በገበያ ላይ ከፍተኛውን ትኩረት የሚያደርጉት ዩኤስ-አሜሪካውያንም ናቸው በአዲሱ ዓለምአቀፍ የገበያ ውድድር ረገድ መራራውን ተሞክሮ እንዲቀምሱት ግዴታ የሆነባቸው። አሁን በሚቀርበው ግምት መሠረት፥ በገበያ እቃዎች ማደራጃው እንዱስትሪ በኩል ዩኤስ-አሜሪካ ውስጥ ብቻ ፫ ሚሊዮን የሥራ ቦታዎች ናቸው የተደመሰሱት፣ ከእነዚሁ መካከል ለአንድ-ሦሥተኛው ድምሰሳ ከቻይና የተሸጋገሩት ርካሽ ሸቀጦች ናቸው ተጠያቂ ሆነው የሚታዩት። በተለይ ያሜሪካው ጨርቃጨርቅ እንዱስትሪ ነው ከቻይና የማይበገር ውድድር የመጣበት፥ በቻይና አንድ የፋብሪካ ሠራተኛ በወር ቢበዛ መቶ ዶላር ብቻ ሲያገኝ፣ ዩኤስ-አሜሪካ ውስጥ አንዱ የፋብሪካ ሙያተኛ በአንድ ሰዓት ብቻ ፲፪ ዶላር ነው የሚከፈለው፤ አሜሪካውያኑ ይህንኑ ውድድር ሊበግሩት አይችሉም፤ በርካሹ የደሞዝ ወጭ ምክንያት ርካሽ የሚሆነው ዕቃ መሆኑ ነው ቻይና በዓለም ገበያ ላይ ጠንካራ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችላት።

ሌላው የገበያ ጥያቄ፥ በእንዱስትሪ-ሀገሮች ውስጥ ለግብርናው ዘርፍ በሚሰጠው በግዙፉ ድጎማ አንፃር ነው የሚታየው። ከዓመታት በፊት ጀምሮ በግልጽ እንደሚታየው፥ እንዱስትሪ-ሀገሮች ገበያዎች ክፍት እንዲሆኑና የንግድ መሰናክሎች እንዲወገዱ ለሚያቀርቡት ጥያቄ ሁሉ ትርጓሜ የሚሰጡት፥ እነርሱኑ የሚጠቅም ከሆነ ብቻ ነው። ግን የተፈፀመው ዓመት ፪ሺ፬ በዚህ ረገድ አንድ የለውጥ ምልክት ያሳየ ነው የሚመስለው፥ የተባ መ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ባለፈው ጥር ዳቮስ/ስዊስ ውስጥ በተካሄደው የዓለም ኤኮኖሚ መወያያ መድረክ ላይ ተገኝተው ያሰሙት ንግግር፥ እንዱስትሪ-ሀገሮች ለግብርናው ዘርፋቸው ግዙፍ የወጭ ድጎማ እየሰጡ ገበያን የሚያቃውሱበት አድራጎት እንዲያበቃ በጥብቅ ነበር ያስገነዘበው። እርሳቸው እንደሚሉት፥ የግብርናው ዘርፍ ድጎማ የገበያ ኃይሎችን ይሰብራል፣ የተፈጥሮን ጓዳ ያጎሳቁላል፤ የድሆቹ ሀገሮች ሸቀጦች የገበያ ዕድል እንዳያገኙ ያደርጋል፣ በዚህም አኳኋን የድሆቹን ሀገሮች ገቢ ያጓድላል። ግና ገበያው በእውነት ነፃና ክፍት ቢሆን ኖሮ፣ እነዚያው ደሆቹ ሀገሮች በራሳቸው የንግድ ገቢ እየተማመኑ ከውጭው ርዳታ ጥገኝነት በተላቀቁም ነበር። ስለዚህ፥ ዋና ፀሐፊ አናን አጥበቀው እንደሚያስገነዝቡት፥ ለመላው የዓለም ኅብረተእሰብእ ደኅንነት እና ለነፃው የኤኮኖሚ ሥርዓት ተዓማኒነትም ሲባል፥ እንዱስትሪ-ሀገሮች የሚሰጡት የግብርናው ድጎማ መወገድ ይኖርበታል።

በዚሁ የግብርናው ድጎማ እንዲወገድ በሚቀርበው አቤቱታ ረገድ የሚደረጁት ሀገሮች በ፪ሺ፬ ሂደት መጀመሪያውን ስኬት ለማስመዝገብ በቅተዋል። ይኸውም፥ ስለዚሁ የግብርና ድጎማ ጥያቄ በተፈጠረው ንትርክ አንፃር የዓለም ንግድ ድርጅት በደረሰው ውሳኔ፥ ዩኤስ-አሜሪካ ለጥጥ ተካዮቿ የምትሰጠው ግዙፉ የወጭ ድጎማ የዓለም ንግድን ሕግጋት እንደሚቃረን ማረጋገጡና ማስገንዘቡ ነው። ግዙፍ የመንግሥት ድጎማ የሚታከልላቸው የግብርና ምርቶች የዓለም ገበያን ዋጋ እየተጫኑ፣ እነዚሁኑ የግብርና ውጤቶች በጣም ርካሽ በሆነ ወጭ የሚያመርቱት አዳጊዎቹ ሀገሮች ርትአዊ የገበያ ውድድር አቅምና ዕድል እንዳያገኙ ያደርጓቸዋል።

በዚያው በተፈፀመው ዓመት ፪ሺ፬ በዓለም ድርጅት ዘንድ ለግብርና ምርቶች ኤክስፖርት ስለሚሰጠው ድጎማ ሁለተኛውም ዓቢይ ውሳኔ ነበር የተላለፈው። ፩፻፵፯ቱ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል-መንግሥታት ዠኔቭ ውስጥ ካካሄዱት በጣም የጠጠረ ድርድር በኋላ የደረሱት አዲስ ስምምነት፥ አውሮጳውያኑና ዩኤስ-አሜሪካውያኑ ለግብርና ምርቶቻቸው ኤክስፖርት የሚሰጡት ድጎማ ሙሉ በሙሉ የሚወገድበትን ርምጃ የሚመለከት ነው። በዓለም ንግድ ድርጅት አመለካከት መሠረት፥ ውሳኔው እንደ አንድ ትልቅ እመርታ ነው የሚታየው። የዓለም ንግድ ድርጅት ኣባላት እውነተኛ ጥረት ካደረጉ፥ እያንዳንዱን የንግድ እንቅፋት ሊያስወግዱት እንደሚችሉ የዠኔቩ ጉባኤ ግልጽ አድርጎታል ነበር የተባለው። ግን የኤክስፖርቱ ድጎማ ብቻ አይደለም ችግሩ፤ ይኸው የኤክስፖርት ድጎማ ለግብርናው ዘርፍ ከሚሰጠው ጠቅላላው ርዳታ አንዱን ንኡስ ከፊል ብቻ ነው የሚይዘው። ሰለዚህ፥ የሚደረጁት ሀገራት ስለ ዕድል እኩልነት ለመናገር እስኪችሉ ድረስ ገና ረዥም መንገድ መሄድ አለባቸው።