1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር

ሰኞ፣ ሰኔ 28 2002

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በሚካሄደው የዓለም አግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ተራ በተራ የወደቀው እየወደቀ አሁን አራት ቡድኖች ብቻ ከዋንጫ ባለቤትነት ተሥፋ ጋር ቀጥለዋል።

https://p.dw.com/p/OB1r
የስፓኝ ተጫዋቾች ፌስታምስል AP

በዘንድሮው ውድድር የእስካሁን ሂደት የአፍሪቃ ለግማሽ ፍጻሜ ዙር የመብቃት ሕልም መልሶ ቅዥት ሲሆን የብራዚልና የአርጄንቲና በሩብ ፍጻሜ መሰናበትም የተጠበቀ አልነበረም። ለግማሽ ፍጻሜው ከደረሱት አራት አገሮች ሶሥቱ አውሮፓውያን ሲሆኑ የላቲን አሜሪካ ብቸኛ ተጠሪ፤ ማን አሰበው? ኡሩጉዋይ ሆናለች።

በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ኳስ ድቡልቡል ናትና ያልተጠበቀ ውጤት ደግሞ ደጋግሞ የታየና የተለመደ ቢሆንም እንደ ዘንድሮው የደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ ውድድር ታላላቅ የሚባሉ ቡድኖች ገና ከጅምሩ በብዛት ተፈረካክሰው የወደቁበት ጊዜ ግን ሊያስታውሱት ያዳግታል። ፈረንሣይና ኢጣሊያ ገና በመጀመሪያው የምድብ ዙር ደብዛቸው ጠፍቶ ሲሰናበቱ እንግሊዝም ቢሆን ከአንዲት ዕርምጃ በላይ አላለፈችም። በሩብ ፍጻሜው ዋዜማ በጀርመን 4-1 ተቀጥታ ስትሰናበት ቡድኑ ያ የቀድሞ ግርማ ሞገስና ሃያል የትግል መንፈስ የከዳው ነበር።

ወደ ሩብ ፍጻሜው ሻገር እንበልና የአፍሪቃ የመጨረሻ ተሥፋ ጋና ከኡሩጉዋይ ጋር ባካሄደችው ግጥሚያ በፍጹም ቅጣት ምት 5-3 ተረትታ በአሳዛኝ ሁኔታ ስትሰናበት አፍሪቃ በአፍሪቃ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው ውድድር ለግማሽ ፍጻሜ ለመብቃት እንዳሁኑ የተቃረበችበት ጊዜ አልነበረም። አሳሞዋህ ጂያን ጨዋታው ከተራዘመ በኋላ በ 120ኛዋ ደቂቃ ላይ የሳታት ፍጹም ቅጣት ምት የጋናን ብቻ ሣይሆን የመላውን አፍሪቃ ሕልም ወደ ቅዠት ስትለውጥ ለ 24 ዓመቱ ወጣት ግሩም ተጫዋች ውድድሩ የሰቀቀን መሆኑም አልቀረም። የሆነው ሆኖ የጋና ብሄራዊ ቡድን ያደረገው ትግል የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም።

የሁለት ጊዜዋ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ኡሩጉዋይ በዚህ ሁኔታ ከዕድል ጋር ወደ ግማሽ ፍጻሜው ስታልፍ ሌላዋ የላቲን አሜሪካ ተወካይ ብራዚል ደግሞ በኔዘርላንድ 2-1 ተሸንፋ መሰናበቷ እስካሁን ማስገረሙን የቀጠለ ጉዳይ ነው። የብራዚል ቡድን ለዚያውም ቀድሞ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ብቃቱን ለምን ሊጠቀም እንዳልቻለ እንቆቅልሽ የሆነባቸው ብዙዎች ናቸው። ምክንያቱ ከኔዘርላንድ ልዕልና ይልቅ ከራሱ ከብራዚል ቡድን የመንፈስ ዝግጅትና የወኔ ጉድለት ጋር የተያያዘ ነው የሚመስለው።

ለማንኛውም የብራዚል በአጭሩ መቀጨት የተቀሩትን ቡድኖች የዋንጫ ባለቤትነት ተሥፋ ይበልጥ ነው ከፍ ያደረገው። ጀርመን በፍጹም ልዕልና አርጄንቲናን 4-0በመቅጣት ለግማሽ ፍጻሜው ስትደርስ ዋንጫውን እንደምትወስድ ከወዲሁ ብዙዎች እየተነበዩ ነው። እርግጥ በመጀመሪያ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዋ የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነችውን ስፓኝን ማሽነፍ ይኖርባታል። የጀርመን ቡድን አጥቂ ሚሮስላቭ ክሎዘ እንደሚለው ከሆነ ቡድኑ ስፓኝንም እንደ አርጄንቲና ለማሰናበት ቆርጦ የተነሣ ነው የሚመስለው።

“ስፓኞችም ቢሆኑ የማይረቱ አይደሉም። ልናሸንፋቸው እንችላለን። ቡድኑን በሚገባ አጥንተን ድክመቱን ለመለየትና ይህንኑም ለመጠቀም ነው የምንሞክረው”

በነገራችን ላይ ስፓኝ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰችው በመከላከል ጥበብ የሰከነውን የፓራጉዋይን ቡድን በከባድ ትግል 1-0 በማሽነፍ ነው። በከዋክብት የተመላው የስፓኝ ቡድን ከጀርመን ጋር በሚያደርገው ግጥሚያ የእንግሊዝ ወይም የአርጄንቲና ዕጣ እንዳይገጥመው ከወዲሁ መላ መምታት ይኖርበታል። በተረፈ በግማሽ ፍጻሜው ዙር ነገ ኡሩጉዋይና ኔዘርላንድ የሚጋጠሙ ሲሆን ስፓኝና ጀርመን የሚገናኙት ደግሞ በማግሥቱ ረቡዕ ምሽት ነው።

በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫና በአፍሪቃ እግር ኳስ ይዞታ ላይ ኢጣሊያ ውስጥ የሚኖረውን የቀድሞውን የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ኮከብ ሉቺያኖ ቫሳሎንም አነጋግረናል።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ