1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የነፋስ ኃይል ማኅበርና ታዳሽ የኃይል ምንጭ ፣

ረቡዕ፣ ግንቦት 14 2005

እ ጎ አ በ 2001 ዓ ም፤ የተቋቋመውና ዋና ማዕከሉን ቦን ጀርመን ውስጥ ያደረገው የዓለም የነፋስ ኃይል ምንጭ ማኅበር ፤ በአሁኑ ጊዜ 250 ያህል ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፣ 65 ያህል በነፋስ ኃይል የሚጠቀሙ ብሔራዊ ማኅበራት እንዲሁም 50 ገደማ

https://p.dw.com/p/18cKZ
ምስል picture-alliance/dpa

ሳይንሳዊ የምርምር ተቋማትና ከ 120 የማያንሱ ከነፋስ የኃይል ምንጭ ጋር ግንኙነት ያላቸው ኩባንያዎች በአባልነት የሚሳተፉበት ነው። ይኸው ማኅበር ባለፈው ሳምንት ባቀረበው ዓመታዊ ዘገባ ምንም እንኳ ላቅ ያለ ትኩረት የተሰጠው በተወሰኑ አገሮች ቢሆንም፣ የዚህ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ተፈላጊነት የቱን ያህል ከፍ ያለ መሆኑን ነው ያስረዳው።

ከከርሠ ምድር በሚብላላ የእሳተ ገሞራ ኃይል፤ እንፋሎትም ሆነ የፈላ ውሃን ፣ በማጥመድ እንዲሁም በውኃ ኃይል ኤሌክትሪክ በማመንጨት፤ መቶ በመቶ በታዳሽ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ የሆነችውን ሀገር ፣ አይስላንድን ጨምሮ፤ በአጠቃላይ 100 የተለያዩ ሃገራትና አካባቢዎች፤ ናቸው በአሁኑ ጊዜ ከነፋስ በሚገኝ የኃይል ምንጭ በመጠቀም የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙት። የዓለም የነፋስ ምንጭ ማኅበር እንዳብራራው ባለፈው 2012 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት በአጠቃላይ 45 ጊጋ ዋት የሚያመነጩ አዳዲስ አውታሮች ተክለዋል። ሃቻምና መጠኑ 40 ጊጋ ዋት ነበረ ። እናም ባጠቃላይ አምና ከነፋስ ኃይል የተገኘው የኃይል ምንጭ መጠን 282 ጊጋዋት መድረሱ ነው የተመለከተው።

Neubukow in Mecklenburg-Vorpommern
ምስል DW/L.Knüppel

አዳዲስ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ አውታሮችን በመትከል ረገድ፤ በክፍለ-ዓለም ደረጃ ሲታይ፣ እስያ 36,3፣ ሰሜን አሜሪካ 31,3፣ አውሮፓ 27,5 ፣ ላቲን አሜሪካ 3,9፣ ፤ ኦሽኒያ 0,8፣ አፍሪቃ ደግሞ 0,2 ከመቶ ብቻ ነው ያከናወነው።

ቻይናና ዩናይትድ እስቴትስ፣ በ 2012 (እ ጎ አ) እያንዳንዳቸው በአጠቃላይ 13 ጊጋዋት የኃይል መጠን ያላቸው አውታሮች የተከሉ ሲሆን፤ ጀርመን ፤ ዘንድሮ 3 በመጪው ዓመት ደግሞ 4,5 ጊጋዋት ከነፋስ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ሰፊ እቅድ አላት። በምሥራቅ አውሮፓ፣ በሩሜንያ፤ ዩክሬይን፤ ፖላንድ ኢስቶኒያ፣ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር ብራዚልና በሰሜን አሜሪካዊቷ ሜክሲኮ፣ ባጠቃላይ 40 ከመቶ ነው ፣የነፋስ ኃይል ምንጭ ከፍ እንዲል የተደረገው።

በሚመጡት 20 ዓመታት ፣ በዓለም ዙሪያ፣ የነፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ አሁን ካለው በ 10 እጥፍ ከፍ እንደሚል ይታሰባል። ላቲን አሜሪካና ምሥራቃዊው አውሮፓ በነፋስ ኃይል ለመጠቀም ከፍተኛ ተናሳሽነት ሲያሳዩ፣ አፍሪቃ ባለህበት ሂድ! የሚል መስሏል። የቦኑ ዓመታዊ መግለጫ እንደሚያስረዳው፣ ከአፍሪቃ ቱኒሲያና ኢትዮጵያ ብቻ ናቸው አዳዲስ በነፋስ ኃይል የሚሠሩ ኤሌክትሪክ አመንጪ አውታሮችን መትከላቸው የተነገረላቸው።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ