1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ም/ቤት

ረቡዕ፣ መስከረም 22 2006

በአዲሱ የጥናት ውጤት መሠረት ፣ የየብስ የመሬትና የከባቢ አየር ሙቀት መጠን ፣ ከተተነበየው በላቀ ሁኔታ በሲሦ ይጨምራል ነው የተባለው። እ ጎ አ እስከ 2100 ዓ ም፤ ውቅያኖሶች፤ ከባህር ልክ በላይ ከ 26 -82 ሴንቲሜትር ከፍታ ይኖራቸዋል ማለት ነው።

https://p.dw.com/p/19szM
ምስል Reuters

ከዚህ ቀደም ከተተነበየው ይበልጥ በሚያስደነግጥ ሁኔታ የፕላኔታችን የአየር ለውጥ እሳሳቢ መሆኑን ባለፈው ዓርብ ፣ እስቶክሆልም ፤ እስዊድን ላይ ባወጣው 5ኛ ዘገባ ላይ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
በአዲሱ የጥናት ውጤት መሠረት ፣ የየብስ የመሬትና የከባቢ አየር ሙቀት መጠን ፣ ከተተነበየው በላቀ ሁኔታ በሲሦ ይጨምራል ነው የተባለው። እ ጎ አ እስከ 2100 ዓ ም፤ ውቅያኖሶች፤ ከባህር ልክ በላይ ከ 26 -82 ሴንቲሜትር ከፍታ ይኖራቸዋል ማለት ነው። IPCC ከዚህ ቀደም እ ጎ አ በ 2007 ዓ ም ባወጣው የጥናት ውጤት ፤ ወቅያኖሶቹ ከየብስ ጋር ከሚያዋስናቸው ጠርዝ ያኔ ይገኙበት ከነበረው መሥመር በ 18 እና 59 ሴንቲሜትር መካከል ከፍ ሊሉ እንደሚችሉ ነበረ ያስታወቀው ። ይህ፣ 90 ከመቶ የተረጋገጠ ነው ሲል ያኔ ያቀረበው መረጃ፣ አሁን 95 ከመቶ የማያወላዳ መሆኑን ነው ያስገነዘበው። መቶ በመቶ ሊባል ምንም ያህል አልቀረውም። IPCC ፣ በቢል ክሊንተን የአስተዳደር ዘመን ፣ የዩናይትድ እስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት በኋላም ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው ከነበሩት፣ አልበርት አርኖልድ ጎር (ጄ አር)ባጭሩ ከአል ጎር ጋር እ ጎ አ በ 2007 ዓ ም የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘቱ አይዘነጋም። ም/ቤቱ ፣ የአየር ንብረት ፣ በሰዎች ግድየለሽ እርምጃ የቱን ያህል እንደሚዛባ ግንዛቤ በማስጨበጡና ሊወሰዱ የሚገባቸውን የመፍትኄ ሐሳቦች በማመላከቱም ነው ለሽልማት የበቃው።

Symbolbild Klimawandel
ምስል picture-alliance/dpa


የአየር ንብረት ለውጥ ነክ ም/ቤት ያቀረበው አዲሱ ዘገባ፤ ለጀርመንም ሆነ ለሰሜን አውሮፓ እስከምን ድረስ አሥጊ ነው?
በሰሜናዊው ጀርመን በ ኪል ከተማ በሚገኘው የሄልምሆርስት የውቅያኖስ ምርምር ማዕከል ባልደረባ ሞጂብ ላቲፍ እንዲህ ይላሉ።«በመሠረቱ፣ በዓለም ዙሪያ የሚታየው አዝማሚያ፣ የፕላኔታችን ሙቀት መጨመር፣ የባህር ልክ ከፍ ማለት ፤ ለጀርመንም በአየር ንብረት ረገድ ብርቱ ፍተና የሚያስከትል ነው። ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ውጤት ጋር ሲመዘን የጀርመን አማካይ ላይ ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ፤ በኛ ሀገር፤ ምሥራቁ ባህር፣ እ ጎ አ ከ 1900 ዓ ምወዲህ የባህሩ ልክ መጠን በ 20 ሴንቲሜትር ከፍ ማለቱ እሙን ነው። የምድራችን ሙቀት ጨመረ ሲባል ፤ እዚህ በጀርመንም በአንድ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ ጨምሯል ማለት ነው። »የባህር ልክ መጠን ከፍ እያለ መኼድ ምንድን ነው የሚያስከትለው?
«ከሚመጣው ጣጣ ጋር መጋፈጥ ግድ የሚል ነው ። ሁለት ጠረፎች እንዳሉን የታወቀ ነው። አንደኛው የሰሜን ባህር ጠረፍ ሲሆን ሁለተኛው የምስራቅ ባህር ጠረፍ ነው። የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ም/ቤት እንዳለው ፤ እስከያዝነው ምዕተ ዓመት ፍጻሜ ፤ የፕላኔታችን ውቅያኖሶች ከፍታ እስከ 80 ሴንቲሜትር ድረስ ሊዘልቅ ይችላል። ግን በትክክል ይህ ነው ብሎ መቶ በመቶ ማረጋገጥ አዳጋች ነው። ትንሽ ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል። ምክንያቱም፤ በአርክቲክ ወቅያኖስ የግሪንላንድ ደሴት የበረዶ ክምር በሚመጡት ዐሠርተ-ዓመታት ምን እንደሚያጋጥመው በትክክል ካሁን መናገር አያቻልምና!እዚህ ላይ በተጨማሪ መዘንጋት የሌለብን፣ ባንግላዴሽ፣ እንዲሁም በሰላማዊው ውቅያኖስ የሚገኙ ደሴቶች ዕጣ -ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ነው፤ የውቅያኖሱ ጠርዝ ትንሽ እንኳ ከፍ ማለት የቱን ያህል የጥፋት አደጋ እንደሚደቅን መገመት የሚያዳግት አይደለም። »

Fabrikschornsteine
ምስል picture-alliance/chromorange


በእስቶክሆልም ይፋ የተደረገው 5ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በይነ-መግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ነክ ም/ቤት (IPCC )ዘገባ ፣የፕላኔታችን የሙቀት መጠን ቀስ እያለ እንደሚጨምር መግለጡ፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ባለሥልጣናት በጊዜ ተገቢውን እርምጃ እንዳይወስዱ ሰብብ አይሆንም ወይ ለሚለው ጥያቄ፤ የአየር ንብረት ምርምር ነኩ ሊቅ ሞጂብ ላቲፍ እንዲህ ነበረ መልሳቸው---«እንደሚመስለኝ፤ ፖለቲከኞች ምንጊዜም፤ ግፊት ሲያይልባቸው ፣ ማለት አንድ የሆነ ችግር ካጋጠመ በኋላ ነው እርምጃ ለመውሰድ ደፋ ቀና የሚሉት። ዓይተናል --አማራጭ የኅይል ምንጭን በተመለከተ ስለቀረበው ውሳኔ--፣ በፉኩሺማ የአቶም አውታር አደጋ ከደረሰ በኋላ ነበረ ወዲያው አማራጭ የኃይል ምንጭ አቅርቦትን የሚመለከት ውሳኔ ላይ የተደረሰው። ለነገሩ ለዐሠርተ-ዓመታት ከአየር ንብረት ይዞታ ጋራ በተያያዘ ጉዳይ በሚነሱ ጥያቄዎች፤ የአማራጭ የኃይል ምንጭን አስፈላጊነት ከመጠቆም የቦዘንንበት ሁኔታ አልነበረም። ታዲያ፣ እስከተወሰነ ጊዜ ሙቀት ቀስ ብሎ ይጨምራል በሚለው አባባል ፋታ ይሰጣል ብሎ ችላ ማለት ስህተት ነው የሚሆነው። ጥልቁ ባህር፣ ወይም ጥልቁ ውቅያኖስ እጅግም አይሞቅም ብሎ መዘናጋት ፤ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙቀቱን መጨመር አይገታውም፤ እናም ጠቃሚ ጊዜ ይሆናል በከንቱ የምናባክነው።»ፕላኔታችን፣ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እየጋለች እንደምትሄድ ፣ ይህም ፤ ድንጋይ ከሰል፤ ነዳጅ ዘይትና ጋዝ በመጠቀም በዚሁ ሳቢያ በሚያጋጥም የተቃጠለ አየር (CO2)ልቀት መሆኑን እ ጎ አ ከ 1950 ዓ ም አንስቶ ዘገባዎች ይቀርቡ ነበር።

Ausgetrocknete Erde
ምስል picture-alliance/chromorange


አሁንም ዓለም በመላ፤ ከፋብሪካዎች፣ ከአውቶሞቢሎች፤ ከአኤሮፕላኖችና ከመርከቦች ከከባቢ አየር ጋር እንዲቀላቀል የሚደረግ የተቃጠለ አየር ልቀት፤ በሰፊው እንዲገታ ካልተደረገ ፤ (ይህን ደግሞ መንግሥታት ያከናውናሉ ብለው ሳይንቲስቶች አያምኑም)ዓለማችን ባለንበት ምዕተ ዓመት የ 1,1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት ጭማሪ እንደሚያጋጥማት ነው የተገለጠው። ወደ 2 ዲግሪ ጠርዝ ፣ ከፍ ካለም ብርቱ አደጋ አይቀሬ ነው። በተለይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባልበቁ አዳጊ አገሮች የሚያስከትለው ጥፋት በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። ህዝብ በባህር ልክ ከፍታ ሳቢያ ከጠረፍ ከተሞች እየለቀቀ መሰደዱ የማይቀር ነው። በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እንደሚታየው የባህር ማዕበል እያየለ ነው የመጣው። በቅርቡ በሜክሲኮ የደረሰውን ያስታውሷል።
ከዚህ ቀደም በዚህ ክፍለ ጊዜ እንዳወሳነው፣ በምድር ሰቅ ዙሪያ በሙቀት ሳቢያ የሚተን ውሃ፣ ከቀዝቃዛ አየር ጋር ተጋጭቶ የሚፈጥረው አውሎ ነፋስና ውህ ጭኖ የሚከንፍ ማዕበል ፤ በዓለም ዙሪያ በየጊዜው የሚያደርሰው አደጋ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም የሚሄደው። የተቀጠለ አየር (CO2) ልቀት እየጨመረ መሄድ የተለያዩ ፣ የኦክስጂን ጋዝ ክምችት(ኦዞን) ፀር የሆኑ ጋዞችም መታከል፣ ከአካባቢ ብክለት ባሻገር የፕላኔታችን ሙቀት እየጨመረ እንዲሄድ በማድረግ ሊያስከትል ስለሚችለው ጥፋት በየጊዜው ነው የሚነገረው። ሙቀት እየጨመረ በመምጣቱ ፣ የአርክቲክና የአንታርክቲክ የበረዶ ተራሮች እየቀለጡ፤ በመናድ ላይ መሆናቸው እሙን ነው። የሙቀት መጨመር ፣ ለባህር አውሎ ነፋስና ማዕበል መበራከት አስተዋጽዖ ማድረጉም አልቀረም።

Symbolbild Klimawandel
ምስል picture-alliance/dpa


ታዲያ ከባህር የሚቀሰቀስ ውሃ ተሸክሞ በሚነፍስ አውሎ ነፋስ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ አስቀድሞ ከመነሻው ከሥር ከመሠረቱ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ቅድመ -ጥንቃቄ ያደረግ ዘንድ መረጃ በማቅረብ ለማስጠንቀቅ ፣ የዩናይትድ እስቴትስ ብሔራዊ የበራራና የኅዋ ነክ መስተዳድር (NASA) በምድር ሰቅ አካባቢ በሞቃት አየር የሚፈጠሩ ማዕበሎችንና በአውሎ ነፋስ ውሃ ቀላቅሎ የሚከንፍ ማዕበልን (ሃሪኬን) እንቅሥቃሴ የሚከታተሉ ጥቂት ለየት ያሉ አብራሪ የለሽ አኤሮፕላኖችን አሠማርቷል። እነዚህ አብራሪ የለሽ አኤሮፕላኖች፤ ከህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላኖች የበረራ መሥመር እጥፍ መጥቀው
21,000 ሜትር(21 ኪሎሜትር ) ከፍታ ላይ መብረር የሚችሉ ናቸው።
የዚህ ጥናት ዓላማ፤ ወቅታዊ የባህር አውሎ ነፋስንና ማዕበልን እንቅሥቃሴ ለማወቅ ብቻ ሳይሆን፤ በቀጣይነት ለፕላኔታችን የአየር ንብረት ለውጥ ሂደትም ላይ ጠቀሚነት እንደሚኖረው ነው የሚታሰበው። በ 5ኛው የ IPCC ዘገባ ፤ በአርክቲክና ፣ አንታርክቲክ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በባህር ወይም በውቅያኖስ ጠረፎች ስለሚያጋጥመው ችግር ፣ ስለድርቅና ስለጎርፍ ጠንቀኝነት ሠፍሯልና ፣ ሃገራት በየበኩላቸው ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? በመጪው ሳምንት እንደምንመለስበት ተስፋ አለን።

ተክሌ የኋላ
ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ