1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የኤድስ ጉባኤ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 17 2004

ላለፉት ሰላሳ ዓመታት HIV/AIDS በዓለማችን ከ30 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ፈጅቷል። ዓለም ዓቀፍ የኤድስ ጉዳኤ በዩናይትድ ስቴትስዋ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከእሁድ ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ ጉባኤ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በዚችዉ

https://p.dw.com/p/15e8e
ምስል picture alliance/dpa

 ምድር ከተካሄደ ወዲህ አነሰም በዛም ወሳኝ የተባሉ ሂደቶች ታልፈዉ፤ ተዛማቹ በሽታ ወትሮ የነበረዉ የመተላለፍ ፍጥነት እንቅፋት እንዲጋረጥበት ያደረጉ ጥረቶችም ዉጤት አሳይተዋል። እሁድ እለት ዋሽንግተን ላይ የተከፈተዉ ዓለም ዓቀፍ የኤድስ ጉባኤ ደግሞ የተጀመረዉ ተስፋ ሰንቆ መሆኑ ነዉ የተነገረለት።  መድሃኒት አልባ ሲባል የነበረዉ በሽታ ካለፉት ዓመታት ወዲህ አንዴ ክትባት ሌላ ጊዜ አብነት እንደተገኘለት ሲነገር ተደምጧል።

ከየሀገራቱ የመጡ 20 ሺህ ተመራማሪዎች፤ ዶክተሮች እና HIV ቫይረስ በደማቸዉ የሚገኝ ተሳታፊዎች የተገኙበት የዋሽንግተኑ የAIDS ጉባኤ በተስፋና ከየአቅጣጫዉ የተደረጉ ጥረቶች ያስከተሉትን ዉጤት በመዘርዘርም ስኬትን አሰባስቦ በቋመጠ መንፈስ ነዉ የተጀመረዉ። ይህ የሆነበት ምክንያት ይላሉ የዓለም ዓቀፉ የኤድስ ጉባኤ ሊቀመንበር ዶክተር ዲያነ ሃቭሊር፤

« ይህ የሆነበት ምክንያት በተከታታይ የተደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ላለፉት ሶስት ዓመታት በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር ትርጉም ባለዉ መልኩ እንዲቀንስ ስልት ስለፈጠሩልን ነዉ።»

Wachsamkeit gegen AIDS schwindet
ምስል picture-alliance/dpa/dpaweb

የጀርመን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዳንኤል ባር ለጉባኤዉ ይፋ ያደረጉትም እሳቸዉ ያሉትን እዉነታ ያጠናክራል፤

«ጀርመን ዉስጥ በHIV ቫይረስ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር በመቀነሱ እንኮራለን። ያም ማለት በአንድ ዓመት በቫይረሱ አዲስ የሚያዙት 2,700 መሆኑ በግልፅ ታይቷል።  ያም ቢሆን 2,700 በጣም ብዙ ነዉ፤ ይህ ገና አጠንክረን መዉሰድ የሚገባን ቀጣይ ርምጃ እንዳለ ያሳያል።»

የጉባኤዉ ተሳታፊዎች በመክፈቻዉ ወቅት የሰነዘሯቸዉ አስተያየቶች እና አጋጣሚዉ ጉባኤዉ በተስፋ ሰጪ ግኝቶች ከመታጀቡ ጋ የተገኘ አስመስሏል። ባለፉት ዓመታት የHIV ቫይረስን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ መድሃኒቶች መገኘታቸዉ ተሰምቷል። በተለይ በክትባት መልክ እንደሚሰጥ የተወራለት የእስያዉ ግኝት በርካቶችን አጓጉቶ እንደነበር አይዘነጋም። ለ16 ሺህ ሰዎች ታይላንድ ዉስጥ የተሰጠዉ ክትባት፤ በHIV ቫይረስ የመያዝን እድል በሶስት እጅ ይቀንሳል ተብሎለታል። ምርምሩ ለሰባት ዓመታት በዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይልና የታይላንድ መንግስት ትብብር መካሄዱ በወቅቱ ተገልጿል። ክትባቱ የተቀመመዉ ቀደም ሲል ከተገኙ ሁለት የተለያዩ ክትባቶችን በማቀናጀት ነበር።

የHIV ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል በተደረጉ ጥረቶች  ዉጤቶች መገኘታቸዉን ነው ዘገባዎች የሚያመለክቱት። በዉጤቱም ለወትሮዉ የሰዉነትን በሽታ የመከላከል አቅም አዳክሞ ቫይረሱ ሰዎችን ለሞት የሚጣድፍበትን አቅም መቀነስ መቻሉ፤ የቫይረሱንም የስርጭት ፍጥነት ለመግታት መሞከሩ ታይቷል። ይህንንም መንግስታት ከየሀገራቸዉ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ቁጥሮችን በማሳየት ገልፀዉታል። ተመራማሪዎች ደጋግመዉ እንዳመለከቱት በአግባቡ የሚሰጣቸዉን መድሃኒት የተከታተሉ ቫይረሱ በደማቸዉ የሚገኝ ወገኖች በዚህ መዘዝ ብቻ ለህልፈተ ህይወት የሚያሰጋቸዉ ሁኔታ እንደሚቀንስ ይገልፃሉ። የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ቫይረሱ በደማቸዉ እንደሚገኝ በምርመራ የተረዱቱ ቲሎ ክሪስት የዚህ ምስክር ናቸዉ፤

«ቫይረሱ በደሜ እንደሚገኝ ያመላከተኝን የምርመራ ዉጤት ስመለከት በቃ ግፋ ቢል ሁለት ሶስት ዓመት በህይወት ብኖር ነዉ ብዬ ነበር ያሰብኩት። ስለዚህ ላደርግ ካቀድኳቸዉ ጥቂት ነገሮችን ለማከናወን ወሰንኩ፤ እነዚህን ነገሮች አሁንም በድጋሚ በምንም መልኩ ቢሆን ማድረግ ይኖርብኛል። አዎ፤ እናም ቀስ በቀስ ነገሮቹ ተለወጡ፤ አሁን ይገባኛል፤ በሚገባ የእድሜ ባለፀጋ ሆኛለሁ።»

ባለፉት በርካታ ዓመት በምርምር የተገኙ  ከ20 በላይ የሚሆኑ ለበሽታዉ መከላከያ እንዲዉሉ የተቀመሙ መድሃኒቶች አሉ። ተመራማሪዎች ከእነዚህ  መድሃኒቶች ፍቱን የሆኑት የሶስቱ ድብልቅ HIV ቫይረስ በደማቸዉ ለሚገኝ ቢሰጥ፤ ቫይረሱ ወደሌሎች የመተላለፍ ኃይሉ ይዳከማል፤ በታማሚዎቹ ሰዉነት ላይም የሚደርሰዉ ጉዳት የመቀነስ እድል ይኖረዋል። በቦን ዩኒቨርሲቲ ሥር ምርምር የሚያካሂደዉ ክሊኒክ ባልደረባ ዩርገን ሮክሽትሮህ አስፈላጊዉን የመድሃኒቶቹን ንጥረ ነገሮች ያካተተ አንድ ክኒን ብቻ ቢገኝ አወሳሰዱን ለታማሚዎቹ እንደሚያቀለዉ ያምናሉ። እንዲህ ያለዉን መድሃኒት የሃኪም ትዕዛዝን ሳያዛቡ፤ ከተገቢዉ የግል ጥንቃቄዎች ጋ መዉሰድንም ይመክራሉ።

«ያለፉት ዓመታት ጥረቶች ትርጉም ያላቸዉ ናቸዉ። ለዚህ ነዉ የHIV  መድሃኒቶች ሥራ እየሠሩ ነዉ የምንለዉ። ሆኖም ግን ህመምተኞች በቀላሉ ሊወስዷቸዉ የሚችሉ እና የተሻለ ዉጤት የሚያስገኙ መድሃኒቶች አሁንም ያስፈልጉናል።»

Eine HIV - Infizierte und ihr täglicher Pillen - Cocktail
የሚወሰዱ የመድሃኒቶች ስብስቦችምስል picture-alliance / dpa

  እስካሁን ቫይረሱን ሊያጠፋ የሚችል መድሃኒትም ሆነ ክትባት እንዳልተገኘ በሚገለፅበት በዚህ ወቅት ተመራማሪዎች የተለየ ስልት ማግኘት ችለናል ማለታቸዉ ነዉ በዚህ ጉባኤ የተሰማዉ። ይህ የሚባለዉ አዲስ ስልት ምን ይሆን? በ UNAIDS የመረጃ፤ የፖሊሲና ዉጤት ዘርፍ ዳይሬክተር በርንሃርድ ሽቫርትላንደር፤

«በርግጥ ጉባኤዉ የተጀመረዉ በአዎንታዊ ስሜት ነዉ፤ በመሠረቱ ሳይንቲስቶች የHIVን ስርጭት ለመግታት የሚችል ያሉት አንድ ስልት ብቻ አይደለም። እስካሁን ለመከላከል ሲረዱ የቆዩ ህክምናዎችን በማጣመር፤ ቫይረሱ ለሌለባቸዉ ሆኖም ለችግሩ ሊጋለጡ ለሚችሉ ሰዎች ሳይቀር ሊጠቅም እንደሚችል ነዉ የጠቆሙት።»

እሳቸዉ እንደሚሉት በሳይንሱ እስካሁን የተገኙ የመከላከያ ስልቶች በተለያዩ ሀገሮች ያስገኙት ዉጤት ነዉ ጉባኤዉን ከመነሻዉ በተስፋ ያጀበዉ። የHIV ስርጭት ለመግታት ቫይረሱ በደማቸዉ የሚገኝ ብቻ ሳይሆኑ፤ ጤናማዎቹም መድሃኒቱን የሚወስዱበት ሁኔታ መኖሩንም ነዉ ያመለከቱት፤

Welt-Aids-Tag 2009
ምስል picture-alliance/dpa

«ባለፉት ዓመታት፤ ባለፉት 18 ወራት በተለይ ቫይረሱን ለመከላከል በርካታ ተጨማሪ ስልቶች ተገኝተዋል። ይህም በቫይረሱ ምክንያት የታመሙትን በማከም፤ አቅማቸዉ ተገንብቶ፤ በህይወት ሰንብተዉ ምርታማ እንዲሆኑ ማድረግ ብቻ ሳይሆን አሁን እነዚህ ህክምናዎች የቫይረሱን ስርጭት እንዴት ሊገቱ እንደሚችሉ ብዙ አዉቀናል። አንደኛ ህክምናዉ የቫይረሱን ስርጭት ከመግታት አንፃር፤ አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰዉ ወደሌላ እንዳያስተላልፍ የቫይረሱን አቅም ከማድከም አኳያ ዉጤት አሳይቷል፤ ሌላዉ በቅርቡ የደረስንበት ደግሞ PRAP የሚባለዉ ማለትም ለቫይረሱ ከመጋለጥ አስቀድሞ የሚደረግ ለጤናማ ሰዎች የሚሰጥ ህክምናን ይመለከታል።»

ለዚህ በሽታ በሚል በምርምሩ የተገኙ መድሃኒቶች ቫይረሱ በደማቸዉ ዉስጥ የሌለ ጤናማ ሰዎች ቢወስዷቸዉ በHIV ከመያዝ እንደሚከላከሉላቸዉ ነዉ ተመራማሪዎች ደረስንበት ያሉትን ግኝት የUNAIDS የመረጃ፤ የፖሊሲና ዉጤት ዘርፍ ዳይሬክተር በርንሃርድ ሽቫርትላንደር፤ ያብራሩት። በተለይ ለዚህ ይዉላል በሚል የሚጠቀሰዉ ትሩቫዳ የተሰኘዉ መድሃኒት ቢሆንም ጉዳዩ ግን አሁንም በርካታ ተመራማሪዎችን ማነጋገሩ አልቀረም። ለመሆኑ መድሃኒቱ ይረዳል ይባልና ሰዎች ይጠቀሙበት ቢባል ሊወሰድ የሚገባዉ እንዴት ነዉ፤ በየዕለቱ ወይስ አንድ ሰዉ ወሲብ ለመፈፀም ሲዘጋጅ? HIV ላይ ምርምር የሚያካሂደዉ የጀርመን ኤሰን ከተማ ዩኒቨርሲቲ ክሊኒክ ባልደረባ ሽቴፋን ኤሰር ዋናዉ ሊያነጋግር የሚገባዉ ጉዳይ ይህ ነዉ ሲሉ ይሞግታሉ።

«ይህ በፍፁም አይሠራም፤ ምክንያቱም ሰዎች መቼ ለወሲብ ሊነሳሱ እንደሚችሉ ሁሌም ሊያዉቁ አይችሉም፤ ስለዚህ ይህ የሚያመጣው ዉጤት አይኖርም። በርግጥ ሰዎች መቼ ለወሲብ ሊነሳሱ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ጥናቶች ተደርገዋል። ያ ግን ከመድሃኒቶችና ከመድሃኒት ምርምሮች ጋ የሚሄድ ነገር አይደለም። ያም ማለት ወሲብ ከመፈፀሜ ሁለት ደቂቃ በፊት መድሃኒቱን ብወስድ ራሴን በቫይረሱ ከመያዝ አዳንኩ ማለት አይደለም። የሚሆን ከሆነ ቢያንስ ከቀናት በፊት መድሃኒቱን መዉሰድ ይኖርብኛል። ለመሆኑ ከቀናት አስቀድሞ ያ ሰዉ መቼ ወሲብ ለመፈፀም ሊነሳሳ እንደሚችል ያዉቃል ማለት ነዉ?»

የባለሙያዉ ክርክር እንዲሁ የተነሳ አይደለም፤ ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ ሊያደርጉ ይገባል የሚባሉት የሶስቱ መ-ዎች መመሪያነት አሁንም አማራጭ እንደሌለዉ የሚያመለክት እንጂ። እነሱም በአንድ መወሰን፤ መታቀብና መከላከያ መጠቀም ሲሆኑ፤ ዛሬ ዛሬ እንደዉም ከመወሰንና ከመታቀብ የተለየ አማራጭ ማቅረብ ሰዎችን ለአደጋ መጋበዝ ነዉ የሚሉ ሞልተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ