1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር መክፈቻ፣

ሐሙስ፣ ሰኔ 5 2006

የዘንድሮው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት እንሆ ከአንድ ሰዓት ተኩል ገደማ በኋላ በሳዖ ፓውሎ ስታዲየም በደመቀ ሥነ ሥርዓት ይከፈታል ተብሎ በመጠበቅ ላይ ነው። ከዚያም ሥነ ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ ከ 2 ሰዓት ገደማ በኋላ የመክፈቻው ግጥሚያ

https://p.dw.com/p/1CHXO
ምስል Getty Images/Mario Tama

በአስተናጋጅ ሀገር ብራዚልና ክሮኤሺያ መካከል ይካሄዳል። በሥራ ማቆም አድማ የተደናገጠቸው አስተናጋጅ ሀገር ሠራተኞች፤ ያቀረቡትን ጥያቄ ምንጊዜም እንደሚገፉበት ያስታወቁ ሲሆን፤ ዛሬ ግን መስተንግዶው ሳንክ እንዳያጋጥመው መተባበራቸው እንደማይቀር ነበረ ቀደም ሲል የተነገረው ፦ ይሁንና ፖሊስ በሚያስለቅስ ጋዝ እስኪበትናቸው ደረስ ዛሬም ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ እንደነበሩ ታውቋል።

Brasilien Präsidentin Dilma Rousseff mit WM-Pokal
ምስል imago/Xinhua

«ምን ቢሉ ምን ቢሉ ደረሰ አሉ ቀኑ!» እንደሚባለው ነው ፤ ከደቡብ አፍሪቃ ቀጥሎ የዓለምን የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የምታስተናግደው ሀገር ፤ 4 ዓመት ጠብቃ ፤ አይደርስ የለም፣ ቀኑ ደርሶ ፣ ዛሬ መስተንግዶዋን ትጀምራለች። የዓለም የእግር ኳስ ፌደሬሽን (FIFA) እንዳለው ፣ በዓለም ወደር የሌለው ይኸው ትርዒት፤ ከ 3,2 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ከቴሌቭዥን ፊት ዓይኑን እንዲተክል በውዴታ ግዴታ ማስኮልኮሉ አይቀሬ ነው።

የብራዚል ጎረቤት አርኼንቲና ተወላጅ የሆኑት የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በብራዚል ቴሌብዥን ባስተላለፉት ቡራኬ መሰል መልእክት፣

«አስደናቂው የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ፣ በትክክለኛ የወንድማማችነት መንፈስ እንዲከናወን ምኞቴ ነው ፤ እግር ኳስ የቡድን ሥራና በዓለም ሕዝብ መካከል፣ የትብብር መንፈስ የሚንጸባረቅበት እንጂ የዘረኝነትና የስግብግብነት ትርዒት የሚታይበት ሊሆን አይገባም» ማለታቸው ተጠቅሷል።

Deutsche Nationalelf bekommt Besuch beim Training
ምስል Getty Images

የተለያዩ አገሮች ብሔራዊ ቡድኖች ደጋፊዎች፣ የአስተናጋጅ ሀገር የብራዚል ጭምር በተለያዩ ከተሞች ተሠማርተው ፣ በእግር ኳስ ፍቅር ስሜት እየዘፈኑ ፣ እየዘመሩ ባሉበት በዛሬው ዕለት ፤ የመክፈቻው ሥነ ሥርዓትና የመጀመሪያው ግጥሚያ የሚካሄድበትን የኮሪንቲያንስ ክለብ ስታዲየም ለመውረርና ለማስተጓጎል ያሰቡ የተቃውሞ ሰልፈኞች በፖሊስ የሚያስለቅስ ጋዝ ተበትነዋል።

የተቃውሞ ሰልፈኞቹ አምና በዚህ ወር የ FIFA የኮንፈደሬሽን ዋንጫ ውድድር ከተካሄደበት ጊዜ አንስቶ ተቃውሞ ከማቅረብ አልቦዘኑም፤ እግር ኳስን ጠልተው ሳይሆን፤ ሥራ አጦች፣ መጠጊያ የሌላቸው ፣ የተሟላ የህክምና አገልግሎት የማያገኙ፤ በትምህርት ተቋማትም ብዙ ጉድለቶች መኖራቸው እየታወቀ ፤ መንግሥት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ ለምን 12 እስታዲየም ለማደስና አዳዲሶችም ለመሥራት ያውለዋል? ነው ቃውሞአቸው !

«ያለፍትሕና ርትእ የዓለም ዋንጫ ብሎ ነገር የለም»! የሚል መፈክር ያነገቡ እንደነበሩም ተገልጿል።

የማሕበራዊ ኑሮውን ችግር የብራዚል ሠርቶ አደር ሕዝብ ቢገነዘበውም ፣ የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ውድድር እስኪጠናቀቅ ትዕግሥት ማድረግና ከዚያ በኋላ እንደአስፈላጊነቱ መቀጠል በሚለው የተስማማ ይመስላል። የብራዚልን ሰንደቅ ዓላማ የሚያውለበልብ ፣ ዓርማ የያዘ ፤ 10 ቁጥር የተጻፈበት ሹራብ በብዛት የለበሰ ሰው በየጎዳናው ይታያል።

Straße in Brasilien dekoriert mit Nationalflaggen zur WM
ምስል picture-alliance/AP

የብራዚል ወጣት ኮከብ ተጫዋች፤ ኔይማር፤ 12ኛው ተጫዋች ወሳኝነት አለውን ይፈለጋል ባይ ነው። ብሔራዊው ቡድን ከሚያበረታታ ህዝብ ሰፊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆመው። ያም ሆነ ይህ አሁን ጭውውቱ ፤ ሁሉ ስለ እግር ኳስ ሆኗል።

ለዋንጫ ፍጻሜ የሚደርሱ እነማን ይሆናሉ? ተብለው የተጠየቁ ብራዚላውያን ይህን ነበረ ያሉት።

«ጋናና ብራዚል ናቸው ለፍጻሜ የሚደርሱ!»

«ብራዚል ዋንጫ ትወስዳለች።»

«ብራዚል አሸንፋ ዋንጫ ብትወስድ ደስ ይለኛል ፤ ምክንያቱም ብዙ ጥረት አድርገዋልና!»

«እንደሚመስለኝ ብራዚል በጣም ጥሩ ዕድል ይኖራታል፣ አጥቂውና ተከላካዩ ሁለቱም ጠንካሮች ናቸው»።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ