1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የወጣቶች ቀን

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 14 2003

ካቶሊካዊያን የዓለም የወጣቶች ቀን ለ 26ኛ ጊዜ እዚህ አውሮጳ ውስጥ እየተከበረ ይገኛል። የካቶሊካዊት ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛን በወጣቶቹ ቀን ላይ የመገኘት ዕቅድ በመቃወም ረቡዕ ለት በማድሪድ ረብሻ መቀስቀሱ ተነግሯል። በረብሻው ቢያንስ 11 ሰዎች መቁሰላቸውም ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/Rgll
የዓለም ወጣቶች ቀን ማድሪድ ከተማምስል picture alliance / dpa
በዚህ የዓለም የወጣቶች ቀን ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንም መገኘታቸው ታውቋል። የዛሬው የወጣቶች መድረክ ዝግጅታችን የሚያተኩረው በዚሁ ዓለም አቀፋዊ ዝግጅት ላይ ነው። ካቶሊካዊያን የዓለም የወጣቶች ቀን ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2003 ዓ. ም. ነበር ስፔን ማድሪድ ከተማ ውስጥ በይፋ የተከፈተው። ከቤተ ክርስቲያን በወጡ ዘገባዎች መሰረት ከ400 ሺህ በላይ ወጣቶች ማድሪድ ከተማ ለመገኘት እንደተመዘገቡም ታውቋል። የማድሪድ ከተማ ነዋሪዎች ከመላው ዓለም የመጡ ወጣቶችን የተቀበሉት በዝማሬ፣ በጭፈራ እና በዳንስ ነበር። ለቀናት በዘለቀው በዚህ የዓለም የወጣቶቹ ቀን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ሊገኙ እንደሚችሉም ተገምቷል። ማክሰኞ ዕለት የወጣቶቹ ቀን በይፋ የከፈቱት የማድሪዱ አቡን ሩኮ ቫሬላ ነበሩ፥ «በዚህ 26ኛው የዓለም ወጣቶች ቀን ከሶስት ዓመታት በፊት ሲድኒ ላይ ወደተጋበዙት ወደ ብፁዕ አባታችን ቤኔዲክት 16ኛ ማድሪድ ከተማ ላይ እንኳን በደህና መጣችሁ።» በዚህ የካቶሊካውያን የዓለም የወጣቶች ቀን ላይ ለመሳተፍ የመጡ እንዳሉ ሁሉ ለተቃውሞ የተሰለፉም አልታጡም። ወጣቶቹ «አነስተኛ እምነት፤የዳበረ ትምህርት» ሲሉ ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። በሌላ ወገን ደግሞ ለተቃውሞ የወጡትን ወጣቶች የሚቃወሙ ሌሎች ወጣቶች የካቶሊካዊት ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛን ስም እያነሱ ሙጋሴያቸውን አሰምተዋል። ቤኔዲክቶ ቤኔዲክቶ፤ ረዥም ዕድሜ ለርዕሰ ሊቃነ-ጳጳሳቱ ሲሉም ተደምጠዋል።
NO FLASH Weltjugendtag Oviedo Flaggen
ወጣቶች ከመላው ዓለምምስል picture alliance / dpa
በተቃውሞና በድጋፍ የተዋጠው ትዕይንት ግን ባለበት አልዘለቀም። በተለይ ትናንት ተቃውሞው አይሎ ወደረብሻ መቀየሩ ተዘግቧል። ተቃውሞውን ተከትሎ በተነሳው ረብሻም ቢያንስ 11 ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል። ቩርስበርግ ከተባለው የጀርመን ግዛት ተነስታ ማድሪድ ከተማ የወጣቶቹ ቀን ላይ የተገኘችው ወጣቷ ካታሪና የተቃውሞ ሰልፉን እና አጠቃላዩን ሁኔታ በዚህ መልኩ ትገልፀዋለች፥ «በጣም የሚያስደስት ሁኔታ ነው እዚህ ያለው። ትልቅ የተቃውሞ ሰልፍም ነበር። በእርግጥ ማንም ባይጠብቀውም። እና እዚህ ስለምናደርገው በጣም በርካታ ትችቶች ነው የሚሰነዘረው። በእርግጥ ከመላው ማኅበረሰብ ጋር በጣም ደስ የሚል ሁኔታ ነው ያለው። በቀላል አነጋገር ቃላት ከሚገልፁት በላይ እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው።» እንደ ካታሪና ያሉ በርካታ ወጣቶች የወጣቶቹን ቀን ደግፈው በቦታው ሰገኙ ሌሎች የተለያዩ በርካታ ማኅበራትና ተቋማት በበኩላቸው ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል። «አውሮፓ ላይቻ»የተሰኘው ስፔናዊ ማኅበር ሊቀ-መንበር ፍራንሲስኮ ዴልጋዶ እምነት ከአስተዳደር ሊነጠል ይገባል ሲሉ ተቃውሞዋቸውን ገልፀዋል። «የምንፈልገው ዓለማዊ መንግስት ነው። እምነት እና መንግስት በፍፁም መለያየት አለባቸው። እናም ወደ ስፔን የሚደረገው የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን እምነታዊ ጉዞ ቀስ በቀስ መጥፋት አለበት።» ለቀናት የዘለቀው ይህ የወጣቶች ቀን ቀጥሎ የሚጠናቀቀው የፊታችን እሁድ ነው። ትናንት ማድሪድ ከተማ ላይ የካቶሊካዊት ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳቱን ንግግር ለማድመጥ ጉዞ ያደርጉ ከነበሩት መካከል ገመቹ በቀለ ይገኝበታል። ወጣት ገመቹ በቀለ በዶቼ ቬሌ አካዳሚ እና በሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር በሚሰጠው ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ ጥናት ውስጥ የድህረ-ምረቃ ተማሪ ነው። ለአጭር ጊዜ ደግሞ ዶቼ ቬሌ የአማርኛው ክፍል ውስጥ በተግባራዊ ልምምድም ቆይቷል። ወደ ከተማው እምብርት ለመጓዝ የምድር ለምድር ፈጣን ባቡር እየጠበቀ ባለበት ቅፅበት ነበር የደወልኩት። ባቡሩ መሬት ለመሬት በሚጓዝበት ጉድጓድ ውስጥ ባቡሩ እስኪመጣ ከሚጠባበቁት በርካታ ወጣቶች መሀከል ሆኖ ሁኔታውን እንደሚከተለው ያብራራል፥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ከሚገኙ 190 ሀገራት የተሰባሰቡት እነዚህ ወጣቶች ማድሪድ ላይ በአንድነትም በተቃውሞም ተገናኝተዋል። የሁሉም ትኩረት ታዲያ ርዕሰ ሊቃነ-ጳጳሳቱ ነበሩ። የዓለም ወጣቶች ቀን የሚከበርባት ስፔን ከ10 ዓመታት በፊት ግብረ-ሰዶማዊነትን ማለትም በተመሳሳይ ፆታ የሚደረግን ጋብቻ በህጓ ፈቅዳ አርቅቃለች። ከዚያም ባሻገር ስፔን ግብረ-ሰዶማዊ አቻ ተጋቢዎች በማደጎ ህፃናትን ማሳደግ ይችላሉ ስትልም በህጓ አካታለች። በዚያም መሰል ሕግን በይፋ ካረቀቁ የዓለማችን ሀገራት ሶስተኛዋ ሆናለች።
NO FLASH Spanien-Besuch zum Weltjugendtag Papst Benedikt XVI. 2011
የካቶሊካዊት ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛምስል dapd
ርዕሰ ሊቃነ-ጳጳሳቱ ትናንት ስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ አየር ማረፊያ ሰደርሱ የስፔኑ ንጉስ ጁዋን ካርሎስ እና ንግስት ሶፊያ በተጨማሪም የስፔን ጠቅላይ ሚንስትር ሉዊስ ሮድሪጌዝ ሳፓቴሮ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቤኔዲክት 16ኛ የወጣቶች ቀን አስተናባሪዎችን ካመሰገኑ በኋላ አብይ ያሉትን የወጣቶች ችግር ነቅፈዋል። «ወጣቶች የፆታዊ ጉዳይ ወጥ እውነታን ስተው በታያታ፣ ሁሉን በመጠቀምና በዓለማዊ ፌሽታ ተውጠው ይስተዋላሉ። ይህ የህብረት መላላት እና የመበላሸት ውጤት ነው። እናም ይህን ከባድ ፈተና ተወጥተው ደስተኛ ህይወት ለመምራት ሀይላቸውን ሁሉ ቢያሟጡም ያለ እግዚአብሔር ርዳታ ግን ከባዱን ፈተና ሊያልፉት እንደማይችሉ ያውቁታል።» ካቶሊካውያን የዓለም ወጣቶች ቀን በማድሪድ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ኩታሮ ቪየንቶስ ውስጥ ነሐሴ 15 ቀን 2003 ዓ. ም. ይጠናቀቃል። እሁድ በማሳረጊያው ዕለት ሁለት ሚሊዮን ታዳሚያን እንደሚሰባሰቡም ይጠበቃል።