1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጉባዔ በሲንጋፑር፧

ማክሰኞ፣ መስከረም 9 1999

ዓለም አቀፉ የገንዘብ መምሪያ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ ጉባዔ በያመቱ እንደሚደረገው ሁሉ፧ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ሲከፈት ውሳኔዎች ሁሉ ይተላለፋሉ፧ ወሳኙ ሂደት፧ ከጉባዔው በፊት የሚከሠት ነው። በሲንጋፑርም የሆነው ይኸው ነው።

https://p.dw.com/p/E0dU
የዓለም-አቀፉ የገንዘብ መምሪያ ተቋምና የዓለም ባንክ ጉባዔ፧ በሲንጋፑር፧
የዓለም-አቀፉ የገንዘብ መምሪያ ተቋምና የዓለም ባንክ ጉባዔ፧ በሲንጋፑር፧ምስል AP

በዓለም አቀፉ የገንዘብ መምሪያ ድርጅት ከፍተኛ አካል፧ ከአዳጊ አገሮች ላቅ ባለ ደረጃ ላይ የሚገኙት፧ በተጠቀሰው የተቋሙ ወሳኝ አካል፧ ውክልና እንዲኖራቸው አያሌ ወራት ድርድር ሲካሄድ መቆየቱ ታውቋል። የተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ Rodrigo de Rato በዛሬው ዕለት እንዳስታወቁት፧ ቻይና፧ ቱርክ፧ ደቡብ ኮሪያና ሜክሲኮ፧ ከፍ ያለ የመሠረታዊ ወረት(ካፒታል) ድርሻ ያገኛሉ። በተጨማሪም ከፍተኛ የድምጽ መብትና የገንዘብ ቀውስ በሚያጋጥምበት ጊዜ፧ ላቅ ያለ ብድር የማግኘት ዕድል ይሰጣቸዋል። ከሲንጋፑር፧ የዶይቸ ቨለ ባልደረባ Karl Zawadsky ለላካው ዘገባ፧ ተክሌ የኋላ.....

ለቻይና፧ ቱርክ፧ ደቡብ ኮሪያና ሜክሲኮ፧ ከፍ ያለ የድምፅ መብትና በዛ ያለ ብድርም የማግኘት ዕድል መሰጠቱ፧ 60 ዓመት በሆነው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ታሪክ እጅግ ዐቢይ የተሃድሶ ለውጥ ነው። ታላላቆቹ በኢንዱስትሪ የገሠገሡት አገሮች፧ ለምሳሌ ዩ ኤስ አሜሪካና ጀርመን የተጠቀሱትን በቂ ውክልና ሳያገኙ የቆዩ አገሮች እንዲሠምርላቸው መርዳታቸው አልቀረም። ዋና ሥራ አስኪያ ሮድሪጎ ደ ራቶ እንዳስታወቁት፧ ለሃድሶው ለውጥ 90% ነው ድጋፍ የተሰጠው። ህንድ፧ ብራዚልና አርጀንቲና፧ በሁለተኛው ዙር የተሃድሶ ለውጥ እርምጃ፧ በዚያ ዓለም አቀፍ እጅግ ታዋቂ የገንዘብ ተቋም፧ ዐቢይ ተሰሚነት እንደሚኖራቸው ነው ተስፋ የሚያደርጉት።

በአጠቃላይ፧ የቻይና፧ የቱርክ፧ የደቡብ ኮሪያና የሜክሲኮ ድርሻ በ 1.8 ከመቶ ከፍ ብሏል። የቻይና በተናጠል ከ ሦስት ወደ 3.7 ከመቶ ነው ያሻቀበው። የቱርክ፧ ከ 0.45-0.55 ከፍ ብሏል። ከአዳጊ አገሮች ላቅ ባለ ደረጃ ላይ የሚገኙት መንግሥታትበተቋሙ የነበራቸው እጅግ ዝቅ ያለ ውክልና አሁን በሲሦ ተሻሽሎ ከፍ እንዲል ተወስኗል። በሚመጡት ሁለት ዓመታት፧ በአዲስ መልክ የድርሻ መጠን ስምምነት ይደረግበታል። በዚሁ እርምጃም ሌሎች ታዳጊና ከታዳጊዎቹም ላቅ ባለ ደረጃ ላይ የሚገኙት አገሮች ጠቀሜታ እንደሚያገኙ ይታሰባል። በድርሻ አዲስ ድልድል ረገድ፧ እንደሌሎቹ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ መንግሥታት ጀርመን፧ በትጋት በመሳተፍ፧ የራሷ ድርሻ ና የድምጽ አሰጣጥ የመብቷ መጠን እንዲቀነስ ተስማማታለች። የጀርመን የገንዘብ ሚንስትር Peer Steinbrück...

«ጀርመን ውሳኔውን በመደገፍ፧ ከ 6.087 ድርሻዋ 0.107 ከመቶ እንዲቀነስ አድርጋለች ማለት ነው። አሁን የራሷ ድርሻ ከ 6.087 ወደ 5.980 ከመቶ ነው ዝቅ እንዲል ያደረገች። በዚህ ሂደት፧ ጀርመን ያላትን ትርጓሜ ታጣለች ወይም ፌደራዊት ጀርመን፧ ብሔራዊ ጥቅሟን ወደ ማስረከቡ አዘነበለች ለማለት በእውነት አስቸጋሪ ነው።«
Steinbrück በዓለም አቀፉ የገንዘብ መምሪያ ተቋም የራሷ ሥራ አስፈጻሚ በአባልነት እንዲገኝ ያበቃችው አገራቸው፧ በዓለም ውስጥ በኤኮኖሚ የሦስተኛነቱን ደረጃ እንደጠበቀች እንድትቆይ ማድረግ ጠቃሚ ነው ይላሉ። በሲንጋፑር፧ የአንዳንድ አገሮችን ድርሻ ከፍ ከማድረጉ፧ የዓለም ኤኮኖሚ የሚነቃቃበትን ፧ የዶሃው የዓለም የንግድ ድርጅት ድርድርም የከሸፈበትን ሁኔታ ከመመልከቱ ባሻገር፧ ሌሎች ዐበይት ጉዳዮች ምን ይሆኑ?! የተቋሙ ዋና ሥራ እኪያጅ ሮድሪጎ ደ ራቶ፧...

«በዓለም ዙሪያ ኤኮኖሚ የሚያንሠራራበት አዙሪት፧ ይህም እንዲቀጥል ማድረግ የሚቻልበት እርምጃ፧ በዓለም ንግድ መሥፋፋት ላይ የተመረኮዘ ነው። ይህ ካልሠመረ ደግሞ ሂደቱ አያምርም። ለዓለም የኤኮኖሚ ብልጽግና ሳንክ 3 ጉዳዮች ናቸው።
1. የነዳጅ ዘይት ዋጋ መናር የዕቃ ዋጋ ግሽበትን ያስከትላል። 2. የገቢና ወጪ ንግድ ሚዛን ያልጠበቀ ሁኔታ እየተስፋፋ የሚሄድ ከሆነ ቀውስ ይሆናል የሚያስከትለው።
3. ከጤናማ አስተሳሰብ በመራቅ በንግድም ሆነ ገበያ ላይ ገደብ ማስተዋወቅ ተጠናክሮ ከቀጠለ ሌሎች ችግርችም ይበልጥ አስከፊ መልክ ይይዛሉ።«

የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት Paul Wolfowitz በበኩላቸው አዳጊ አገሮች፧ ጥሩ አስተዳደር በመመሥረት፧ ሙስናን በመታገልና ድኅነትን የማስወገድ ብርቱ እርምጃ በመውሰድ፧ ብሩኅ ተስፋ ይኖራቸዋል ብለዋል። የዓለም የንግድ ድርጅት ድርድር እንደገና እንዲጀመር ተሳታፊዎች ሁሉ ጥረት ያድርጉ ሲሉ ጥሪ ያስተላለፉት ባለሥልጣን፧

« ዩ ኤስ አሜሪካ፧ ለግብርና የምትሰጠውን ድጎማ መቀነስ አለባት፧ የአውሮፓው ኅብረት በገበያ ላይ የጣለውን ገደብ ማላላት ይጠበቅበታል። ቻይና፧ ህንድና ብራዚል፧ ለኢንዱስትሪ ዕቃዎች የሚከፈል ቀረጥን መቀነስ ይኖርባቸዋል። አዳጊ አገሮች፧ በንግድ ዘርፍ እጅግ የደኸዩት ምርታቸው ገበያ የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲቃለል መጣር ይበጃል። የዶሃው የዓለም የንግድ ድርጅት ድርድር በተሣካ ሁኔታ ተደምድሞ፧ እጅግ የደኸዩት አገሮች በእጅጉ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ መጣር አለብን«።