1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓረብ ሊግ ዉሳኔና ሶሪያ

ሰኞ፣ ጥር 14 2004

ጥልቁ ክፍፍል፥- አረቦችን የሶሪያ ሁከት-አመፅ፥ ግጭትን ለማስቆም ልክ እንደ ሊቢያ ሁሉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔ ማግኘት አለበት-በሚሉት እና የለም የአረብ ችግር በአረቦች መፈታት አለበት በሚሉ ሁለቱ ጠርዞች ላይ አቁሟቸዋል

https://p.dw.com/p/13obt
የዓረብ ሊግ ስብሰባምስል Reuters

23 01 12

ከአንድነቱ ይልቅ ሁለት፥ምናልባትም ከዚያ በላይነቱ ፈጥጦ የወጣበት የአረብ ሊግ አንድ የመሰለበት ዕቅዱን ወሰነ።አንድ ያልሆኑት፥ ጨርሶም አንድ የማይሆኑት የሶሪያ መንግሥትና ተቃዋሚዎቹ ዕቅዱን እንደ አንድ ተቋም እኩል ተቃወሙት።ዛሬም እንደገና አረብ-ሶሪያ እያልን እንጠይቃለን።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ባለፈዉ ሳምንት ከዮርዳኖሱ ንጉስ አብደላሕ ጋር በእነሱ አገላለፅ «ከተዘጋ በር ጀርባ» ያደረጉትን ዉይይት፥ምናልባትም የተስማሙበትን ነጥብ ሙሉ በሙሉ አልደበቁም ነበር።«እንደለ መታደል ሆኖ እዚያች ሐገር ዉስጥ ተቀባይነት ከሌለዉ ደረጃ የደረሰ ሁከት ማየታችን አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።ሥለዚሕ ያሁኑ የሶሪያ ሥርዓት ሥልጣን እንዲለቅ ሊደረግበት ሥለሚገባዉ ዓለም አቀፍ ግፊትና መፈጠር ሥላለበት ድባብ ከዮርዳኖስ ጋር በቅርብ እየተመካከርን ነዉ።»

የቱኒዚያና የግብፅን የዘመናት ፖለቲካዊ ሥርዓት የገለባበጠዉ ሕዝባዊ አመፅ እንደ ብዙዎቹ የአረብ ሐገራት ሁሉ፥ ዮርዳኖስ የሐገር-መንግሥትነት ወግ-ሥርዓትን ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ የምትገዛበትን ዘዉዳዊ ሥርዓት ማርገፍገፉ አልቀረም ነበር።ንጉስ አብደላሕ የሐሽማይት ዘዉዳዊ ሥርዓታቸዉን ያንገዳገደዉን ሕዝባዊ አብዮት ያዳፈኑት በስምንት ወራት እድሜ ሰወስት ጠቅላይ ሚንስትሮች የሚመሯቸዉ መንግሥታት በመቀያየር ነበር።ለአመፀኞች ገንዘብ በመክፈልም ነበር።

ሶሪያ ከእስራኤል ቀንደኛ ጠላቶች-አንዷ ናት።የሐማስ ደጋፊነቷ፥ የኢራን የቅርብ ወዳጃነቷ፥በሊባኖስ ፖለቲካ-ምጣኔ ሐብታዊ ሒደት ላይ ከፍተኛ ተፅኖ ማሳደሯ አያጠያይቅም።የደማስቆ ገዢዎች ለምዕራባዉያን መንግሥታት እና ለወዳጆቻቸዉ «አስጊ» የመባላቸዉን ያክል ለአረቦች በጣሙን ለአጓራባቾቿቸዉ ለአማን ገዢዎች ወዳጅ እንጂ አሳሳቢ የሚሆኑበት ምክንያት መሠረትም በርግጥ የለም።

ይሁንና የሐሺማይት ዙፋን ጠባቂዎች በዋሽንግተን-ለንደኖች ለመታመን ይሻሟቸዉ የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ በመወገዳቸዉ የመደሰታቸዉን ያክል ሙባረክን ያስወገደዉ አይነት ሕዝባዊ አብዮትን በተለይ ምዕራቦች የሚያራግቡትን አመፅ-ቁጣ በየተቀጣጠለበት ማጋጋም ወደ ራሳቸዉ እንዳይመጣ እንደ ጥሩ የመከላከያ-ሥልት ማየታቸዉ አልቀም።

ሊቢያ እንደታየዉ ሕዝባዊ ማዕበሉ ወደ ራስ እንዳይመጣ ሌላ ሥፍራን በተለይ በምዕራቦች የሚወገዝ-ሥርዓትን ሲነዉጥ-ነዉጡን ማንኮር ማንኮር የአማኖች ብቻ ሳይሆን የሪያድ፥ የዶሐ፥ የማናማ፥ የመስካት፥ ኩዌይት ሌላዉ ቀርቶ የራባት ነገስታት አዲስ ሥልት ነዉ።እርግጥ ነዉ የአረብ ሊግ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በነገስታት፥ በጦር ሐይል፥ በሶሻሊስቶች ወይም በሪፐብሊካዊ መንግሥት የሚመሩት መንግሥታት መነታረኪያ ያልነበረበት ጊዜ አልነበረም።የለምም።

የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ አዋቂ ፈዋዝ ጌርጌስ ትናንት እንዳሉት የሶሪያ ጉዳይ የአረብ ሊግን ቢያንስ ሁለት የተለያዩ ቡድናት አንድ ማሕበር ነዉ አስመስሎታል።«ዛሬ ያየነዉ ትልቁ ነገር በአረብ ሊግ ዉስጥ ያሉ የምላቸዉ ሁለት ተጣማሪዎች መካካል ጥልቅ ክፍፍል መፈጠሩን ነዉ።»

ጥልቁ ክፍፍል፥- አረቦችን የሶሪያ ሁከት-አመፅ፥ ግጭትን ለማስቆም ልክ እንደ ሊቢያ ሁሉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔ ማግኘት አለበት-በሚሉት እና የለም የአረብ ችግር በአረቦች መፈታት አለበት በሚሉ ሁለቱ ጠርዞች ላይ አቁሟቸዋል።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ «የሶሪያን ሥርዓት ለማስወገድ አለም አቀፍ ግፊት» ያሉት እርምጃ የሶሪያን ጉዳይ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ከማስወሰን የተለየ ሊሆን አይችልም።።

የዋሽግተኖችን መመሪያ አከል ሐሳብ ቋጥረዉ ባለፈዉ ሳምንት አማን የገቡት ንጉስ አብደላሕ ቅዳሜ ወደ ካይሮ ለወረዱት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ሌላ-ትዕዛዝ ይሰጣሉ ብሎ ማሰብ ሲበዛ ከባድ ነዉ።ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን ከነዘር-መንዘራቸዉ፣ የሥርዓታቸዉ መሠረት ከነ-ማግ ድሩ ላጠፋዉ ለምዕራባዉያን ድብደባ አጣድፎ ያጋለጠዉ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ነበር።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የአዉሮፕላን በረራ ማገድን፥ ተቃዋሚዎችን በቀጥታ ከሚረዳ የአየር፥ የምድር፥ የባሕር ድብደባ ጋር ያሳካረዉን ዉሳኔ እንዲያሳልፍ ጠያቂዉ ደግሞ በሪያድና በዶሐ-የሚገፋዉ የአረብ ሊግ ነበር።

የሶሪያ ጉዳይም ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መቅረብ አለበት ባዮቹ-እኒያዉ በነገስታት የሚመሩት መንግሥታት ናቸዉ።በሕዝባዊ አመፅ ለሥልጣን ከበቁት መንግሥታት ይልቅ በዉርስ ዙፋን ላይ የተቀመጡት፥ ሕዝባቸዉን የሚረግጡ፥ ጨቋኝ፥ሙሰኛ ነገስታት ለሶሪያ ሕዝብ ተቆርቋሪ፥ አምባገነናዊ ሥርዓትን ተቃዋሚ መምሰላቸዉ በርግጥ-ግራ አጋቢ ነዉ።የፖለቲካ ተንታኝ ፈዋዝ ጌርጌስ እንዳሉት ግን ነገሩ ያሻዉን ያክል ግራ ቢያጋባም የአረብ ክፍፍል እዉነት፥ እዉነቱ ደግሞ በተለይ አሁን ገሐድ ነዉ።

«የሶሪያ ጉዳይ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ለማድረስ በሚሹት በቀጠርና በሳዑዲ አረቢያ የሚመሩት የባሕረ-ሠላጤዉ አካባቢ መንግሥታት፥-ባንድ ወገን፥ በሌላ በኩል ደግሞ የሶሪያ ጉዳይ አረባዊ መፍትሔ ሊፈለግበት ይገባል የሚሉት በግብፅ፥ በኢራቅና በአልጀሪያ የሚመሩት ቡድን ነዉ።»

የሊጉ አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ዕቅድ ወይም ሐሳብ ለአረቦች ችግር አረባዊ መፍትሔ መፈለግ አለበት የሚሉት ሐይላትን አቋም ያንፀባረቀ ነዉ-የሚመስለዉ።የአረብ ሊግ ባቀረበዉ መሠረት የአረብ ታዛቢዎች ለተጨማሪ አንድ ወር ሶሪያ ይቆያሉ።ፕሬዝዳት አሰድ ሥልጣናቸዉን ለምክትላቸዉ ያጋራሉ፥ በሁለት ወራት ዉስጥ ተቃዋሚዎች የሚሳተፉበት መንግሥት ይመሰረታል።እና ብጤዎቹ።

«የሶሪያ መንግሥት አያችሁ እኛ የራሳችን አጀንዳ አለን፥ ለተሐድሶ፥ ለምርጫ፥ ለእርቀ-ሠላም፥ እናንተ ለጠየቃችሁት ለሁሉም አስፈላጊዉን ነገር ሁሉ አድርገናል ሊል ይችላል።እና ጥያቄዉ የአረብ ሊግ የደረደረዉን ሐሳብ ሶሪያዎች ይቀበሉታል ወይ ነዉ።»

ተራዉ ሶሪያዊን የጠየቀዉ፥ሊጠይቀዉ የፈለገ ፥ወይም ተጠይቆ የሰጠዉ መልስ ሥለ-መኖር አለመኖሩ እስካሁን ቢያንስ እኛ ዘንድ የታወቀ ነገር የለም።የሶሪያ መንግሥት የሚቆጣጠረዉ ዜና አገልግሎት SANA ዛሬ እንደዘገበዉ «የአረብ ሊግ የሚንስትሮች ምክር ቤት ዉሳኔን ሶሪያ አትቀበለዉም።ዉሳኔዉ የሶሪያን ብሔራዊ አንድነትና ሉዓላዊነትን የሚጥስ፥ በዉስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ከመግባት እኩል የሚቆጠርም ነዉ።

የደማስቆ ባለሥልጣናት በአረብ ሊግ ላይ ከፍተኛ ተፅኖ የሚያሳድሩትን እንደ ስዑዲ አረቢያና ቀጠር የመሳሰሉ መንግሥታትን የሶሪያን መንግሥት የሚወጉ፥ የሚቃወሙ ሐይላትን ይረዳሉ።ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ ራሳቸዉ በቅርቡ ባደረጉት ንግግር አንዳድ ያሏችዉን የአረብ መንግሥታት አረብን ለጥቅም የሽጡ ብለዋቸዉ ነበር።

«አንዳዶች እኛን ከ (አረብ) ሊግ ለማስወጣት እንችላለን ብለዉ ካሰቡ ከሆነ እራሳቸዉን ነዉ-የሚታልሉት።የአረብ ማንነት የፖለቲካ ዉሳኔ አይደለም፥ ታሪካዊ ጥያቄ እንጂ።እኔ የምላቸዉ ሐገራት እዉነተኛ አረቦች አይደሉም። ማንነታችንን እየሸጡ ነዉ።ይሁንና እነሱ የአረብን ታሪክ ለመሸጥ በሞከሩ ቁጥር ሙከራቸዉ እየከሸፈ ነዉ።ሐገርም ሥልጣኔም በገንዘብ አይገዛም።»


በዚሕም ሰበብ አሰድ ሥልጣናቸዉን ለሎች እንዲያጋራ በተለይ «አሸባሪ» ከሚሏቸዉ ጠላቶቻቸዉ ጋር ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት እንዲመሠርቱ የሚጠይቀዉን የአረብ ሊግን ዕቅድ እንደማይቀበሉት ዕቅዱ ይፋ ከመሆኑ በፊት የታወቀ ነበር።የፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድን አገዛዝ ለማስወገድ በነፍጥ የሚዋጉትም፥ የአደባባይ ሠልፍ የሚያደራጁትም ሐይላት ልክ እንደ እንደ ደማስቆ መንግሥት ሁሉ የአረብ ሊግን ዉሳኔ ዉድቅ ማድረጋቸዉ ነዉ አነጋጋሪዉ።ግን በተለየ ምክንያት።

የተቃዋሚ ሐይላት የሐገር ዉስጥ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰኘዉ ቡድን ባወጣዉ መግለጫዉ «የአረብ ሊግ አዲስ ዕቅድ የፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ መንግሥት የገጠመዉን ተቃዉሞ ለማስወገድ ለሚወስደዉ ደም አፋሳሽ እርምጃ ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጥ ነዉ።ቡድኑ እንደሚለዉ የአረብ ሊግ ከዚሕ ቀደም ወደ ሶሪያ የላከዉ የታዛቢዎች ቡድን የአሰድ መንግሥት በተቃዋሚዎቹ ላይ የሚወስደዉን የሐይል እርምጃ አላስቆመም።በዚሕም ሰበብ ቡድኑ «የሶሪያ ሕዝብ በሊጉ ላይ ያለዉ እምነት ተሸርሽሯል ባይ ነዉ።»

ካይሮ-ከሪያድ፥ ዶሐን-ከባግዳድ፥ አማንን-ከአልጀርስ ያነካካዉ ሽኩቻ ከአረብ ሊግ ዉሳኔ በሕዋላም እንደቀጠለ ነዉ።በዉሳኔዉ ያልተደሰተችዉ ሳዑድ አረቢያ የሊጉ ታዛቢ ቡድን አባላት የነበሩ ዜጎችዋን ከቡድኑ አስወጥታለች።የአረቦቹ ሽኩቻ፥ የሶሪያ ፖለቲከኞች ቁርቁስ «ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ» የሚሰኘዉ ሐይልም የማዕቀብ፥ የመዘዋወር ቅጣት-እርምጃ ለሶሪያ ሕዝብ እስካሁን የተከረዉ ነገር የለም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለዉ አስራ-አንደኛ ወሩን በያዘዉ አመፅ-ሁከት የተገደለዉ ሰዉ ቁጥር ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ በልጧል።በበይሩቱ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ፕሮፌሰር ሒላል ካሻን እንደሚሉት ከዚሕ ቀደም ሊቢያ ላይ የተፀመዉ ለሶሪያ ምሥቅልቅል ሁነኛ መልስ እንዳይገኝ እያነቀፈ ነዉ።

«ሶሪያ እንደ የመን ወይም እንደ ሊቢያ ሳትሆን የአረብ መሠረታዊ ሐገር ናት።የደማስቆ ሥርዓት ደግሞ የሚጫወታቸዉ በርካታ ካርዶች አሉት።ለምሳሌ ሩሲያዎች ሶሪያ ዉስጥ ትልቅ ጥቅም አላቸዉ። ከዚሕም በተጨማሪ በሊቢያ ሁኔታ የገጠማቸዉ እንዲደገም አይፈልጉም።(ሩሲያዎች) ሊቢያ ላይ ለተወሰደዉ እርምጃ ብዙ ሰጥተዉ በምትኩ ምንም አላገኘኙም።ምዕራቡም በደማስቆ መንግሥት ላይ ወሳኝ እርምጃ ለመዉሰድ ተቸግሯል።»

የሶሪያ ሕዝብ የሐገሪቱን መንግሥት በመቃወም የሚያደርገዉ የአደባባይ አመፅ፥ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጦር ጋር የሚያካሒዱት ዉጊያ እንደቀጠለ ነዉ።የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ሐይለኛ አፀፋም እንዲሑ።በዚሕ መሐል የአዉሮጳ ሕብረት፥የሰሜን አሜሪካ ሐገራትና ተባባሪዎቻቸዉ፥ የአረብ ሊግ አባል መንግሥታት በሶሪያ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ከአሰድ መንግሥት ባለሥልጣናት ይልቅ ተራዉን ሕዝብ እየቆጠቆጠዉ ነዉ።እስከ መቼ አይታወቅም።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ





























Syrien Gewalt Proteste Deraa Daraa
የአሰድ ተቃዋሚዎችምስል picture alliance/abaca
Baschar Hafiz al-Assad
ፕሬዝዳንት አሰድምስል picture alliance/dpa