1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘመናዩ ዓለም አቀፍ የባርነት ቀንበር መታሰቢያ ቀን

ሐሙስ፣ ነሐሴ 17 1999

ሰዎችን በባርነት ቀንበር ስር የማዋሉ ተግባር ዛሬም ታሪካዊ ርዕስ እንደሆነ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/E87n
የጡብ ፋብሪካ ሰራተኞች በቻይና
የጡብ ፋብሪካ ሰራተኞች በቻይናምስል AP

ሰዎች እንደ ዕቃ የሚሸጡበት የሚለወጡበት አሰራር ያለፈ ታሪክ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል፤ ይሁንና፡ በሁሉም የዓለም አህጉሮች ውስጥ ዘመናዩ የባርነትን ስርዓት ሲሰራበት ይታያል። ፎልከር ዋግነር ላቀረበው ዘገባ አርያም ተክሌ፡

የሞሪታንያ ምክር ቤት የባርነትን አሰራር ሲያስፋፋ በሚገኝ ላይ ጠንካራ ቅጣት የሚሰጥበት አዲስ ህግ ከጥቂት ቀናት በፊት አጸደቀ። በአዲሱ ህግ መሰረት፡ ሞሪታንያ ውስጥ ሰው ሲሸጥ፡ ሲለውጥ፡ ወይም በባርነት ቀንበር የሚያውል ግለሰብ እስከ አስር ዓመት እስራት ይፈረድበታል። ባርነት እአአ ከ 1981 ዓም ወዲህ በታገደባት ሞሪታንያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ አዲስ የመቅጫ ህግ ለምን ማውጣት ያስፈለገው፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚገምቱት፡ እስከ ስድስት መቶ ሺህ ጥቁር አፍሪቃውያን ናቸው በአሁኑ ጊዜ በዐረባውያኑ የሀገሪቱ ዜጎች መኖሪያ ቤት ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ከባርነት በማይሻል ሁኔታ ላይ የሚገኙት። ዘመናዩ ባርነት ቻይናም ውስጥ በጡብ ፋብሪካ ውስጥ ይታያል፤ ባርነት ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ በህግ ቢታገድም በደቡብ አሜሪካም ቢሆን ጨርሶ አልተወገደም። በተለይ ህጻናት የሚሸጡበት፡ በስራ የሚበዘበዙበት እና በአንጻራቸውም የኃይል ተግባር የሚፈጸምበት አሰራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተስፋፍቶ ሲሰራበት ይታያል። ለምሳሌ፡ ኢንዶኔዥያ ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ልጃገረዶችና ሴቶች የኃይል ተግባር እንደሚፈጸምባቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይገምታሉ። በጀርመን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ቅርንጫፍ አባል ኤስተር ሆፍማን የኢንዶኔዝያውያቱን የስራ ሁኔታ እንዲህ ገልጻዋለች።
« ካነጋገርናቸው በርካታ ሴቶች መካከል ብዙዎቹ በአማካይ በሳምንት ሰባ ሰደዓት ይሰራሉ። ከነዚሁ መካከልም ብዙኃኑ በሳምት ውስጥ አንድም የዕረፍት ቀን እንደሌላቸው ነግረውናል። »
ኢንዶኔዝያ ውስጥ ሴቶቹ የቤት ሰራተኞች መብት በሌለበት ሁኔታ ከመስራታቸው ሌላ፡ ይኸው የስራ ዓይነት እንደ መደበኛ ስራ ስለማይቆጠር ይፋ የደሞዝ ደረጃም ሆነ ሴቶቹ በሳምንት መስራት ያለባቸው ጊዜም አልተተጠቀሰም፤ የዕረፍትም ጊዜ አልተመደበላቸውም። ከዚህ በተጨማሪም ሴቶቹ የኃይሉ ተግባር፡ በተለይ ከቤቱ አባወራ በኩል የግዳጅ ወሲብ ሰለባ የሚሆኑበት ሁኔታ የተስፋፋ ነው። አፍሪቃም ውስጥ ለምሳሌ በጊኔ ወጣት ሴቶች የቤት ሰራተኞች ከባርነት ባልተሻለ ሁኔታ እንደሚበዘበዙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች አባል ጁልየን ኪፐንበርግ የገለጸችበት ሁኔታ ኤስተር ሆፍማን በኢንዶኔዝያ ካየችው ጋር የሚመሳሰል ነው።
« ከባርነት ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ እንዳለ ነው የተገነዘብነው፤ ምክንያቱም፡ ሴቶቹ ተገደው ነው ከባድ ስራ የሚሰሩት። በቀን እስከ አስራ ስምንት ሰዓት ድረስ ካላንዳች ዕረፍት ይሰራሉ። በሳምንቱም ውስጥ ሆነ በዓመት አንድም ቀን አያርፉም። ለሚሰሩት ከባድ ስራም ገንዘብ አይከፈላቸውም። ብዙ ጊዜ እንደታየውም፡ ልጃገረዶቹ ካለደሞዝ ነው የሚሰሩት። »
የሴቶቹ ሁኔታ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ የከፋ መሆኑን የተመድ አስታውቋል። በሺዎቹ በሚቆጠሩ የኮንጎ ሴቶች አንጻር የኃይልና የክብረ ንጽህና መድፈር ተግባር እንደሚፈጸምና በመጨረሻም እንደሚገደሉ ነው ዓለም አቀፉ ድርጅት ያመለከተው። በኪቩ ክፍለ ሀገር ብቻ በአውሮጳዊው ዓመት መጀመሪያ ላይ ወደ አምስት ሺህ ሴቶች ተገድለዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ህጻናትን በስራ ይበዘብዛሉ የሚባሉ አውሮጳውያን ተቋማትን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የታወቀው የአውሮጳውያኑ የሴቶች ልብስ ፋሽን « ኤስፕሪ »ን የሚሸጠው ተቋም ልብሶቹን ህንድ ሀገር ህጻናትን አስከፊ በሆነ ሁኔታ እያሰራ እንደሚያስመርት ተደርሶበታል።