1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘንባባ ዘይት ለምግብ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 10 2006

ከዘንባባ የሚገኘዉ ዘይት በእንግሊዝኛ ፓልም ኦይል የሚሰኘዉ ለምግብነት ከሚዉሉ የዘይት ዓይነቶች አንዱ ነዉ። ለሰዉ ልጅ ጥቅም መዋል የጀመረዉም ከአምስት ሺህ ዓመታት በፊት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

https://p.dw.com/p/1AL1M
ምስል CC/Cayambe

የተክል ዉጤት የሆነዉ ይህ ዘይት በምግብነቱ የሚጠቅሙ ንጥረነገሮች በተፈጥሮዉ የመያዙን ያህል፤ አዘዉትሮ መመገብም ሆነ መጠኑ ሲበዛ የጤና ጠንቅ የሚሆንበት ሁኔታም እንዳለ ይነገርለታል።

ከዘንባባ የሚገኘዉ ሁለት ዓይነት ዘይት ሲሆን ለምግብነት የሚመከረዉ ቀዩ ዘይት ነዉ። እሱም ሳይበዛ። የዘንባባ ዘይት ከዘንባባ ተክል ለምግብነት ከሚዉለዉ ፍሬዉ የሚገኝ ነዉ። ከዘንባባ ሁለት ዓይነት ዘይት የሚገኝ ሲሆን፤ ቀዩ በቀጥታ ከቀዩ ፍሬ የሚገኝ ነዉ። እንደኮኮናት ሁሉ የዘንባባ ዘይትም የአትክልት ቅባት ወይም ስብ የተከማቸበት የዘይት ዓይነት ነዉ። በአማካኝ የቤት ዉስጥ የሙቀት መጠንም ረግቶ ሊታይ ይችላል። የዘንባባ ዘይት በብዛት ርጥበት ያዘለ ሞቃት አየር ባለባቸዉ የአፍሪቃ ሃገራት፣ በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በብራዚል አንዳንድ ግዛቶች ለምግብ ዘይትነት ይዘወተራል።

Malaysia Palmöl Plantage
ምስል AP

ከዋጋዉ አንፃርም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በምግብ ኢንዱስትሪዉ ዘርፍ በሌላዉ ዓለምም ጥቅም ላይ መዋሉ ነዉ የሚነገረዉ። ለሰዉ ልጅ ምግብነት ከዋለበት አምስት ሺህ ዓመታት የሆኑት የዘንባባ ዘይት በተለይ በምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪቃ በምግብ ዘይትነት ረዥም እድሜን አስቆጥሯል። ከአካባቢዉ ሃገራት ጋ በንግድ ተሳስሮ የቆየዉ የአዉሮጳ ነጋዴዎች ይህንኑ ዘይት እየሸመቱ ወደአዉሮጳ ሲያስገቡ ቆይተዋል። በተለይ ብሪታንያ ከምግብ ሸቀጥነቱ በተጨማሪ በኢንዱስትሪ አብዮቷ ዘመን ለማሽኖቿ ማለስለሺያ ሁሉ ስትጠቀምበት እንደቆየች ይነገርላታል። ኢንዱስትሪዉን ካነሳን ደግሞ የዚሁ ተክል ዘይት ለተለያዩ ሳሙናዎች መስሪያም መዋሉ ይጠቀሳል፤ ከእነሱ መካከል ፓልሞሊቭ የገላ ሳሙናን መጥቀስ ይቻላል። ጋና እና ናይጀሪያ ኋላ ላይ በካካኦ ተክል ሳይበለጥ በፊት ከምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ይህን በግምባር ቀደምትነት ወደዉጭ በመላክ ይታወቃሉ። ወደእስያ ስናቀና ደግሞ ኢንዴዢያና ማሌዢያ በርከት ያለ የመሬት ስፋትን የሚሸፍን ተክል እንዳላቸዉና ህንድን ጨምሮ ለዓለም ገበያ በማቅረብም ይታወቃሉ።

Palmölplantage
ምስል CC/a_rabin

ቀይ የዘንባባ ዘይት ስያሜዉን ያገኘዉ ፍሬዉ በተፈጥሮዉ ካለዉ ዶክተር ቸርነት እንደገለፁት ካሮቲነን ከተሰኘዉ ንጥረነገር መሆኑን ነዉ መረጃዎችም የሚጠቁሙት። ይህም እንደቲማቲም፤ ካሮትና መሰል ፍራፍሬዎች እና አትክልቶችን ያላቸዉን የተፈጥሮ ቀለም የሚሰጥ ነዉ።

በተለይ ቀዩን የዘንባባ ዘይት ወይም ፓልም ኦይል እጅግ ሳያዘወትሩ መጠቀሙ እንደሚመከር የሚገልፁት የጤናና የምግብ ሳይንስ ባለሙያ፤ ቢሆን ቢሆንልስ የአኩሪ አተርና የወይራ ዘይቶችን ጨምሮ ሌሎች የዘይት ዓይነቶችን መመገቡ እንደሚመረጥ ነዉ አፅንኦት የሰጡት። ታሽገዉ ከዉጭ የሚገቡት እንደዚህ ዓይነት ለምግብ የሚሆኑ ነገሮችም ተገቢዉ ቁጥጥር እና ምርምርም እየተረደገ ለተጠቃሚዉ ህዝብ መረጃ የመስጠት ባህል ቢዳብር መልካምነቱን ያስገነዝባሉ።

በአሁኑ ወቅት ለምግብ ማብሰያ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ የታሸጉ ምግቦች ዝግጅት ተፈላጊነቱ የጨመረዉ የዘንባባ ዘይት በተለይ አዉሮጳ ዉስጥ በታየዉ ፍላጎት የተነሳ ኢንዶኔዢያ ዉስጥ ኗሪዎችን ከመኖሪያ ቀያቸዉ በማፈናቀል ሳይቀር ለዚሁ ተክል ማልሚያ መሬት ለባለሃብቶች መሰጠቱ ተቃዉሞና አቤቱታ ማስከተሉ የሰሞኑ ዜና ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ