1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዘንድሮው የሩሲያ ፓርላማ

ሰኞ፣ ኅዳር 25 2004

በሩሲያ ትናንት በተካሄደው የፓርላማ ምርጫ ፤ የጠ/ሚንስትር ቭላዲሚር ፑቲን ፓርቲ ፣ «የተባበረች ሩሲያ» ብዙ ድምጽ አላገኘም ቢባልም፤ አሁንም በፍጹም ድምፅ ብልጫ ያለተጣማሪ ፓርቲ ማስተዳደር እንደሚችል ተገለጠ።

https://p.dw.com/p/S0FK
የፓርላማ ምርጫ በሩሲያ፣ የተባበረች ሩሲያ ፓርቲ ተወካዮች፣ ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭና ጠ/ሚ ፑቲንምስል dapd

«የተባበረች ሩሲያ» ፓርቲ ፣ ከ 450 ው መናብርት ፣ 238 ቱን መያዝ እንደሚችል የምርጫ ኮሚሽኑ አስታውቋል። ፓርቲው ፤ ከዚህ ቀደም፣ በህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት የ 2/3ኛ ብልጫ ነበረው ። በትናንቱ ምርጫ 3 ተጫማሪ ፓርቲዎች በፓርላማ ለመወከል የሚያስችል ውጤት አስመዝግበዋል። እነርሱም፤ ኮሚዩኒስቱ ፓርቲ፣ «ፍትኀዊት ሩሲያ» የተሰኘውና ለዘብተኛ ዴሞክራት ፓርቲ የተባለው ፤ አክራሪ ብሄርተኛ የፖለቲካ ድርጅት ናቸው። ስለሩሲያው የፓርላማ ምርጫና ውጤቱ፤ ከሞስኮ ፤ ሽቴፈን ላክ የላከውን ዘገባ ፤ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው አሰባስቦታል።

ትናንት ማታ፤ የምርጫው ውጤት ይገልጥ በነበረበት ወቅት፤ የተባበረች ሩሲያ ፓርቲ የተጠበቀውን ያህል አለማግኘቱን የተገነዘቡት ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭና ጠ/ሚንስትር ቭላዲሚር ፑቲን፣ በቴሌቭዝን የቀረቡ ሲሆን፤ ዋናው እጩ ተወዳዳሪ ባይጥምም ይላል እስቴፋን ላክ ፤የደጋፊዎቻቸውን ደስታ ላለመቀነስና ለማበረታትም ሲሉ ቀልድ ቢጤ መወርወራቸው አልቀረም። ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭ--

«የተባበረች ሩሲያ ፓርቲ፤ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚወከል እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። ባሁኑ ቅጽበት ፓርቲው በውጤት እየመራ ነው። በፓርላማው እጅግ ጠንካራ ኃይል እንደምንሆን እገምታለሁ።»

(የተባበረች ሩሲያ ፓርቲ ከዚህ ቀደም እ ጎ አ በ 2007 ዓ ም በተካሄደው ምርጫ ፣ 64 ከመቶ ድምጽ ፣ በዚህም መሠረት፣ 315 መቀመጫዎችን አግኝቶ እንደነበረ የሚታወስ ነው። አሁን እንደተባለው፣ 49,54 ከመቶ በሆነ ድምጽ፣ 238 መናብርት ፤ ዋናው ተፎካካሪ ኮሙዩኒስቱ ፓርቲ 92 ፍትኀዊት ሩሲያ 64፣ አክራሪ ብሔርተኛው ለዘብተኛ ዴሞክራት ፓርቲው ደግሞ፣ 56 መቀመጫዎችን ሳያገኝ አልቀረም።

በአሁኑ ምርጫ፣ ሰፊ የማጭበርበር ተግባር ተፈጽሟል ፤ በዛ ያሉ የተቃውሞ ፓርቲዎች እንዲያውም በምርጫ እንዲሳተፉ አልተፈቀደላቸውም በማለት፣ በገዥው ፓርቲ ላይ ስሞታ ያቀረቡ ባይታጡም ሜድቬዴብ፤ ነቀፌታው መሰረተቢስ ነው፣ ምርጫው ፍጹም ዴሞክራቲክ ነበረ ባይ ናቸው።

«በህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት ያለው ውክልናም ሆነ ተጨባጭ ይዞታ፤ የሀገሪቱ ን ገሀዳዊ ፖለቲካ የሚያንጸባርቅ ነው። ስለሆነም፤ ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር፣ እንደሁኔታው ተባብረን መሥራት ይኖርብናል። ጥምረት፣ ወይም ቡድን ያስፈልገን ይሆናል። ይህ ደግሞ የተለመደ አሠራር ነው። የፓርላማ ደንብ ነው ። ዴሞክራሲ ይሏል ይህ ነው። »

የተባበረች ሩሲያ፣ ወደ 50 ከመቶ በሚጠጋ ውጤት ፍጹም አብላጫውን በመያዝ ብቻውን ማስተዳድርም ይችል ይሆናል። ሜድቬዴቭ እንዳደረጉት ሁሉ፣ ፑቲንም ውጤቱን በአወንታዊ መልኩ ለማየት ቢሞክሩም ፣ ምኞታቸው ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደነበረ በቴሌቭዥን እንደቀረቡ ለመገንዘብ ሳይቻል አልቀረም።

3,«አገራችን ከበድ ያለ የፈተና ጊዜ እንዳጋጠማት ቀውስም እንደተከሠተ ፣መሪው የፖለቲካ ኃይል፣ የተባበረች ሩሲያ ፓርቲ ፣ ኀላፊነቱን መወሰድ ግዴታው ነበረ። ውስብስብ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥምም እንኳ፣ ዜጎቻችን ፣ የተባበረች ሩሲያን ፓርቲ መሪ የፖለቲካ ኃይል ይሆን ዘንድ መርጠውታል ፣ አረጋግጠውለታል።»

በዘንድሮው ምርጫ ከተወዳደሩት መካከል፣ 3ቱ ቀደም ሲል የተጠቀሱት ፓርቲዎች እንዳሸነፉ ነው የሚሰማቸው። ለምሳሌ ያህል እ ጎ አ በ 2007 ዓ ም፤ በተካሄደው ምርጫ 11,6 ከመቶ አግኝተው የነበሩት ኮሙዩኒስቶች፣ በትናንቱ ምርጫ፣ ከሞላ ጎደል 20 ከመቶ ነው ድምፅ ለማግኘት የበቁት።

የተባበረች ሩሲያ ፓርቲ፤ ተወዳጅነቱ መቀነሱ እሙን ነው። በሰሜናዊው የካውካሰስ ክፍላተ ሀገር፤ በተለይም የሚስሊሞች ቁጥር በሚያመዝኑናቸው አውራጃዎች 90% ድጋፍ ሲያገኝ።፣ በሰላማዊው ውቅያኖስ አዋሳኝ ግዛቶች ለምሳሌም ይህል በ ቭላዲቮስቶክ ከተማ 33 ከመቶ ገደማ ብቻ ነው የድምፅ ድጋፍ ያገኘው። በትናንቱ ምርጫ ውጤት እርካታ ከተሰማቸው የፓርቲዎች መሪዎች መካከል፣ የፍትኀዊት ሩሲያ ሊቀ-መንበር፣ ሰርጌይ ሚሮኖቭ፣ --

«ሶሺያል ዴሞክራቱ ፓርቲ ፣ ፍትኀዊት ሩሲያ፣ በፓርላማ ያለውን ቦታ ላለማጣት ዋስትና ማግኘት ብቻ ሳይሆን፤ ጨምሯል። የዱማ ይዞታ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው እጅግ የተለየ ነው የሚሆነው። ፓርቲያችን በትጋት መሥራቱን ይቀጥላል።»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ