1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዚምባቡዌ ረቂቅ ሕገ-መንግሥት

ሐሙስ፣ መጋቢት 5 2005

የፕሬዝዳት ሙጋቤን አገዛዝ የሚቃወሙት ማድሁኩ እንደሚሉት አዲሱም ረቂቅ የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን የሚፈለገዉን ያክል አይገድብም ባይ ናቸዉ።በዚሕም ምክንያት ደጋፊቻቸዉ ድምፅ እንዳይሰጡ ጠይቀዋል።የዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ ኮሲን ዚላላም ረቂቁ ሕገ-መንግሥቱ አላረካቸዉም።

https://p.dw.com/p/17yBu
ምስል AP

የዚምባቡዌ ሕዝብ የሐገሪቱን ሕገ-መንግሥት ለማሻሻል የተረቀቀዉን ሠነድ ለማፅደቅ በመጪዉ ቅዳሜ ድምፁን ይሰጣል።ረቂቁ ዚምባቡዌ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ለሚመሯት ለፕሬዝዳት ሮበርት ሙጋቤ የሠላሳ ሰወስት ዓመታት ሥልጣን የመጨረሻዉ ታላቅ ፈተና ሊሆን ይችላል።ረቂቁ ከፀደቀ የፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እና ዘመነ-ሥልጣን ይገደባል።የሕገ-መንግሥቱ መሻሻል በቅርቡ ሊካሔድ የታቀደዉን ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ ለማድረግም ጠቃሚ ነዉ ይባል።

ፕሬዝዳት ሮበርት ሙጋቤ፥ ዩሊያ ሐን እንደዘገበችዉ ሥልጣናቸዉን በቅጡ እያጣጣሙ ነዉ።በቀደም ሰማያ-ዘጠነኛ የልደት በዓላቸዉን ሲያከብሩ፥ ሰማንያ ዘጠኝ ኪሎ ግራም የሚመዝን ኬክ አስጋገሩ። ሰማያ ዘጠኝ በሬዎችን አሳርደዉ እንጎዶቻቸዉን በአሮስቶ፥ ስቴክ፥ በጥብሥ አምበሸበሹት። ማወራረጃዉም በሽ ነበር።

ሐገሪቱ ባንፃሩ ዩሊያ እንደምትለዉ እያጣች፥ እየገረጣች ነዉ።የመንግሥቱ ካዝና ባዶ ነዉ።የፊታችን ቅዳሜ ለሚደረገዉ የሕገ-መንግሥት ማሻሻ ሕዝበ-ዉሳኔ የሚያስፈልገዉን ወጪ እንኳ የሸፈኑት የዉጪ ለጋሾች ናቸዉ።ሙጋቤ ግን ለZANU-PF ፓርቲ ደጋፊዎቻቸዉን እናሸንፋለን ይላሉ።
         
«ሥለ ረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ የሚከተለዉን ልናገር።ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም።ኋላ የምናሻሽለዉ ትንሽ ነገር ነዉ።ረቂቁን ደግፈን ለምርጫዉ እንዘጋጅ።በምርጫዉ እናሸንፋለን።»

ከፕሬዝዳት ሙጋቤ ፓርቲ ጋር ተጣማሪ መንግሥት የመሠረተዉ የጠቅላይ ሚንስትር ሞርጋን ሸቫንገራይ ፓርቲ (MDC)ም ረቂቁን ደግፎታል።ሕገ-መንግሥቱ የሚሻሻለዉ ሁለቱ መሪዎች በሁለት ሺሕ ሥምንት ከተደረገዉ ምርጫ ዉጤት ደማ አፋሳሽ ዉዝግብ በሕዋላ ተጣማሪ መንግሥት ሲመሰርቱ ባደረጉት ሥምምነት መሠረት ነዉ።

በአንድ መቶ ሐምሳ ገፆች የተጠናቀረዉ ረቂቅ፥ ከሐገሪቱ ምክር ቤት አንድ መቶ ሐምሳ መቀመጫዎች ቢያንስ ሥልሳዉን ሴቶች እንዲይዙት ይደነግጋል።ትልቁ ለዉጥ የሚደረገዉ ግን በፕሬዝዳቱ ሥልጣን ላይ ነዉ።ፕሬዝዳንቱ በሥለላ ተቋምና እና በጦሩ ላይ የሚኖረዉ ሥልጣን ይቀንሳል።ዘመነ-ሥልጣኑም በሁለት የአምስት-አምስት ዓመታት የተገደበ ነዉ።

ብሔራዊ ሕገ-መንግስታዊ ምክር ቤት የተሰኘዉ ገለልተኛ ማሕበር መሪ ሎቨሞሬ ማድሁኩ እንደሚሉት ሙጋቤ ሐገሪቱን እዳሻቸዉ የገዙት ሥልጣናቸዉ በሕግ-ባለመገደቡ ነዉ።
                  
«ሙጋቤ ሐገራችንን በቅጡ ከመምራት ይልቅ ያጠፏት ለምንም ነገር ተጠያቂ ባለመሆናቸዉ ነዉ።ያሻቸዉን ለማድረግ ሥልጣኑ በሙሉ አላቸዉ።»

የፕሬዝዳት ሙጋቤን አገዛዝ የሚቃወሙት ማድሁኩ እንደሚሉት አዲሱም ረቂቅ የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን የሚፈለገዉን ያክል አይገድብም ባይ ናቸዉ።በዚሕም ምክንያት ደጋፊቻቸዉ ድምፅ እንዳይሰጡ ጠይቀዋል።የዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ባልደረባ ኮሲን ዚላላም ረቂቁ ሕገ-መንግሥቱ አላረካቸዉም።
              
«በረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ ያየነዉ ትንሽ ተስፋ አስቆራጭ ነዉ።የዚምባቡዌ መንግሥት በዚሕ ዘመን የሞት ቅጣትን በመረሠዝ የዘመኑን የእድገት አቅጣጫ ይከተላል የሚል ግምት ነበረን።ከዓለም ሐገራት ሁለት ሰወስተኛዉ የሞት ቅጣትን በሕግም፥ በገቢርም አስወግደዋል።ዙምባቡዌ ግን ከአናሳዎቹ ጎራ ሳትወጣ ልትቀጥል ነዉ።»

ሙጋቤን አጥብቀዉ የሚቃወሙት ምዕራባዉያን ሐገራት ግን ረቂቅ ሕገ-መንግሥቱን የሚደግፉት መስለዋል።ጊጋ በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የጀርመኑ ጥናት ተቋም የአፍሪቃ ጉዳይ ባለሙያ ክርስቲያን ዞስት እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች የአዉሮጳ ሕብረት ረቂቁ ለዚምባቢዌ የተሐድሶ ለዉጥ እንደ መሠረት ነዉ ያዩት።በዚምባቢዌ ምክር ቤት ባለፈዉ የካቲት ረቂቁን ሲቀበለዉ የአዉሮጳ ሕብረት በዚምባቡዌ ላይ ጥሎት የነበረዉን ማዕቀብ በከፊል አንስቷል።በረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ ላይ የሚሰጠዉ ድምፅና በሕገ-መንግሥቱ መሠረት የሚደረገዉ ምርጫ ነፃና ሚዛናዊ ከሆነ ደግሞ ሕብረቱ ማዕቀቡን ሙሉ በሙሉ ለማንሳት ቃል ገብቷል።


የሙጋቤ የወደፊት ዓላማ ግን አለየም።በረቂቅ ሕገ-መንግሥቱ ላይ የሚሰጠዉን ድምፅ ለመከታተል ወደ ዚምባቡዌ የወረዱት ክሪስቲያን ዞስት እንደሚሉት ሙጋቤ ምናልባት በጡረታ ለመገለል ሳያስቡ አልቀሩም።      

«እንደምንሰማዉ እሳቸዉ በሆነ ደረጃም ቢሆን እንደ ሐገር መሪ፥ ዛኑ ፒኤፍ በሚመሠርተዉ (ከመሠረተ) አዲስ መንግሥትም መቀጠሉን የሚፈልጉት አይመስሉም።ጥያቄዉ ግን፥ ሥልጣናቸዉን የሚያሸጋግሩበት ወርቃማ ድልድይ ያገኛሉ ወይ ነዉ?» ላሁኑ መልስ የለም። 

Simbabwe Referendum
ምስል AFP/Getty Images
Leben in Simbabwe
ምስል DW/C. Mavhunga

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ




 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ