1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዚምባባዌ ምርጫ መተላለፍ

ሰኞ፣ ሰኔ 17 2005

የዚምባብዌን የፕሬዚደንታዊ እና ምክር ቤታዊ ምርጫ ቀነ ቀጠሮ በተመለከተ ውዝግብ ተፈጥሮዋል። የሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ምርጫው ቢዘገይ እስከ ሐምሌ ፣ 2013 ዓም እንዲካሄድ ከአንድ ሣምንት በፊት ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

https://p.dw.com/p/18uAA
ምስል Reuters

ሀገሪቱን ካለፉት 33 ዓመታት ወዲህ በመምራት ላይ ያሉት እና ለቀጣዩ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በዕጩነት መቅረብ የሚፈልጉት ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ የተወሰነውን የምርጫ ጊዜ ከዚህ የተሻለ ሌላ ዕለት የለም በሚል በደስታ መቀበላቸውም የሚታወስ ነው።

« ውሳኔውን ተቀብለናል፤ የፍርድ ቤቱን ብይን በሕጉ መሠረት ተግባራዊ እናደርጋለን። »

ጠቅላይ ሚንስትር ሞርገን ሻንጊራይ ግን ጊዜው አጭር ነው፣ የመራጮችንም መብት ይጥሳል በሚል ውሳኔውን እንደማይቀበሉት በመግለጽ ተቃውመውታል።

የዚምባብዌን ውዝግብ በተመለከተም የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ትብብር ድርጅት፣ በምሕፃሩ ሳዴክ ባለፈው የሣምንት መጨረሻ በሞዛምቢክ መዲና ማፑቶ ልዩ ጉባዔ ባካሄደው እና ፕሬዚደንት ሙጋቤ እና ጠቅላይ ሚንስትር ሞርገን ሻንጊራይ በተገኙበት የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ሙጋቤ የምርጫውን ዕለት ወደሌላ ጊዜ እንዲገፉት ጠይቋል። የሳዴክ ዋና ፀሐፊ ቶማስ ሳሎማዎ እንዳስረዱት፣ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል፤ በዚህም የተነሳ 15 ሀገራትን በአባልነት ያቀፈው ሳዴክ ሙጋቤ የምርጫውን ዕለት ቢያንስ በሁለት ሣምንት እንዲገፉት ወስኖዋል። የሳዴክ ውሳኔ ይህ ይሆናል ብለው ላልጠበቁት ለፕሬዚደንት ሙጋቤ የሳዴክ ርምጃ ትልቅ ሽንፈት ሆኖዋል። የሳዴክ የዚምባብዌ ሸምጋይ የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ የድርጅታቸው ርምጃ  ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል።

Zimbabwe Wahlen Morgan Tsvangirai 13.06.2013
ምስል Reuters

« የፖለቲካ ፓርቲዎቹ፣ ከሸምጋዮቹና ከሳዴክ ጋ ባንድነት በመሆን ዚምባብዌን ወደፊት የሚያራምድ አንድ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ይቻል ዘንድ የዚምባብዌን ጊዚያዊ ሁኔታ በጥሞና ይከታተላሉ። » 

Afrika Treffen der EU und der SADC in Mosambik
ምስል DW/R. da Silva

የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ትብብር ድርጅት፣ በምሕፃሩ ሳዴክ በፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ላይ ግፊት ካሳረፈበኋላ ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ለምርጫው ዝግጅት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጥ - ብሎም በሁለት ሣምንት ተራዝሞ እአአ ለፊታችን ነሀሴ 14 እንዲሆን  በመጠየቅ ፕሬዚደንት ሙጋቤ አስፈላጊውን ማመልከቻ ማስገባታቸውን የዚምባብዌ የፍትሕ ሚንስትር ፓትሪክ ቺናማሳ አስታውቀዋል።

Kapstadt Weltwirtschaftsforum
ምስል picture-alliance/dpa

ቀደም ሲል የምርጫው ዕለት እንዲቀየር ያልፈለጉት ፕሬዚደንት ሙጋቤ እንዳሉት፣ ተቀናቃኞቻቸው ሽንፈት ስለሚያስፈራቸው ምርጫውን አይፈልጉትም። የ89 ዓመቱ ፕሬዚደንት የሀምሌ 31፣ 2013 ዓም የምርጫን ዕለት ለማስከበርም ባላቸው አቅም ሁሉ ቢሞክሩም የተቀናቃኞቻቸው መከራከሪያ ሀሳብ ጥረታቸውን መና አስቀርቶታል። ለዚህም ነው የፖለቲካ ተንታኙ ኢቦ ማንዳዝ  የሳዴክን ወሳኔ ያደነቁት።

« 99% የዚምባብዌ ሕዝብ ሳዴክ እንዳለው ምርጫው ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ይፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው መራጩ ሕዝብ በጠቅላላ ሊመዘገብ የሚችለው። »

ይሁንና፣ ፕሬዚደንት ሙጋቤ የምርጫው ዕለት እንዲገፋ ቢስማሙም ለነፃ እና ለትክክለኛ ምርጫ አስፈላጊ የሆነውን እና ብዙዎች በምርጫው ደንብ ላይ እንዲደረግ የጠየቁትን ተሀድሶ ዕውን ማድረጋቸውን ኢቦ ማንዳዛ ይጠራጠሩታል።

የማፑቶው ልዩ ጉባዔ ለሙጋቤ ተቀናቃኞች ትንሽ ድል ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ሞርገን ሻንጊራይ አስፈላጊው ዝግጅት መጛደሉን በማመልከት ሳዴክ ጣልቃ እንዲገባ ወትውተዋል። « የሀገሪቱ መንግሥት ለምርጫው የሚሆን ገንዘብ እንደሌለው ደግሞ ደጋግሞ ተናግሮዋል። እና ገንዘቡን ማፈላለግ ይኖርበታል። » 

ወደ 110 ሚልዮን ዩሮ ያስፈልጋል። ዚምባብዌ ገንዘቡን ማዘጋጀት ካልቻለች ሳዴክ ሊተባበር እንደሚችል የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ገልጸዋል።   « ዚምባብዌ የሳዴክ አባል ናት። እና ችግሩ ከተነሳና ዚምባብዌ ለምርጫ ገንዘብ ከሌላት ያኔ ሳዴክ ጉዳዩን በጥሞና መመልከት ይኖርበታል። » ምርጫውን እና በሰበቡ የተከተለውን ውዝግብ  በተመለከተ የዚምባብዌ ዜጎች የተለያየ አስተያየት ይሰንዝረዋል። አንዳንዶች ለምሳሌ፣« እንደ የዚምባብዌ ዜጋ አሁን ባለው ሁኔታ በምርጫው ድምፄን ለመስጠት ገና እያመነታሁ ነው። የምጠብቀው ተሀድሶ አይኖርም። » ሌላው፣ « እንደ ወጣት የዚምባብዌ ዜጎች የመገናኛ ብዙኃን ወይም የፀጥታ ተሀድሶ ኖረ አልኖረ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል። ምክንያቱም አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምንፈልገው ተሀድሶ እንዳይደረግ አከላክለዋልና። » በመጨረሻም ሌላዋ « ምርጫ ኖረ አልኖረ ለኛ ለሰራተኛው መደብ ብዙም የሚለውጠው ጉዳይ የለም ። የሚጠቅመው ገዢውን መደብ ብቻ ነው። ይህ ስለሆነም ደንታ የለኝም። »

Sitz der Wahlkommision in Harare
ምስል AFP/Getty Images

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ