1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የዞን ዘጠኙ የድረ-ገጽ ጸሐፊ ታሠረ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 3 2009

ዞን ዘጠኝ በሚል ስያሜ ከሚታወቁት የድረ-ገጽ ጸሐፍት መካከል በፍቃዱ ኃይሉ በድጋሚ ታሰረ። የድረ ገፅ ፀሐፊዉ ዛሬ ማለዳ ከመኖሪያ ቤቱ በፀጥታ ኃይሎች ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ መወሰዱን መረጃዉ የደረሳቸዉ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2SZwB
Äthiopien Zone9 Blogger Gruppe
ምስል Zone9

Zone 9 blogger Befekadu rearrested - MP3-Stereo

በአሁኑ ሰዓትም በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታሥሮ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል። በፍቃዱ ኃይሉ ከዞን ዘጠኝ የድረ ገጽ ፀሐፍት እና ከሦስት ጋዜጠኞች ጋር ከሁለት ዓመታት በፊት በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ ከዓመት ከስድስት ወራት እስራት በኋላ በ20 ሺህ ብር ዋስ ከተለቀቀ ጥቂት ወራት ተቆጥረዋል።የፌደራል ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት በወቅቱ የበፍቃዱን ክስ ወደ አመፅ ማነሳሳት የቀየረዉ ሲሆን አቃቤ ሕግ በእሱና በሌሎች ባልደረቦቹ ላይ ይግባኝ ጠይቋል። የእሱ እና የሌሎች ባልደረቦቹ ጉዳይም የፊታችን ማክሰኞ በጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲታይ ተቀጥሯል። በዛሬ ዕለት ደግሞ በማለዳ ከሚኖርበት ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ  በፀጥታ ኃይሎች ለጥያቄ ይፈለጋል ተብሎ መወሰዱን ከቤተሰቦቹ እና ከጓደኞቹ መስማቱን ፤ ከዞን ዘጠኝ የድረ ገጽ ጸሐፍት አንዱ አጥናፉ ብርሃኔ ገልፆልናል።
በድረ ገጽ ጸሐፊነት፣ ደራሲነት እና በመብት ተሟጋችነት የሚታወቀዉ በፍቃዱ ኃይሉ በፀጥታ ኃይሎች በመጀመሪያ የተወሰደዉ በሚኖርበት ፈረንሳይ አካባቢ ወደሚገኝ «ማቆያ ስፍራ» ተብሎ ወደሚጠራ እስር ቤት  እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።ዛሬዉኑ ከቀጥር በኋላ  ወደ የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መዛወሩ የተሰማ ሲሆን ለጥያቄ ትፈለጋለህ ተብሎ የተወሰደበት ምክንያት ግን አለመታወቁን የድረ ገጽ ጸሐፊዉ አጥናፉ ብርሃኔ አመልክቷል። በፍቃዱ ኃይሉ ከባልደረቦቹ የዞን ዘጠኝ የድረ ገጽ ጸሐፍት ጋር በጋራ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ሽልማቶችን አግኝቷል። የዓለም ዓቀፍ የድረ ገጽ ጸሐፍት እና ተርጓሚዎች ጥምረት አባል የሆነዉ በፍቃዱ፤ በግሉም ከአራት ዓመታት በፊት ቡርት የተሰኘዉን የአፍሪቃ የስነጽሑፍ ሽልማት ችልድረንስ ኦፍ ዜር ፓረንትስ /የወላጆቻቸዉ ልጆች/ በሚል ርዕስ በጻፈዉ ልብ ወለድ መጽሐፍ በሦሶስተኛ ደረጃነት ተሸልሟል። 
ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ