1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ሕዝባዊ አመፅና የመንግሥት እርምጃ

ረቡዕ፣ መጋቢት 14 2003

የሰላሳ-ሁለት አመቱ ገዢ፥ የሁለቱ የመኖች አንድ አድራጊ፣ ግን ቀድሞዉ አስር-አለቃ የበርሊኑን ትልቅ ዲፕሎማት ምክር-ዝክር ሰሙ እንጂ አላደመጧቸዉም።የጊዜዉ ሒደት ያገዛዛቸዉ ፅልመት ምፅዓት መሆኑንም አላስተዋሉም

https://p.dw.com/p/RBxG
ምስል dapd

የየመኑን ፕሬዝዳት የዓሊ አብደላሕ ሳሌሕን አጋዛዝ በመቃወም የሐገሪቱ ሕዝብ የሚያደርገዉ አመፅ ዛሬም ተጠናክሮ ቀጥሏል።የየመን ካቢኔ ትናንት ያወጀዉን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሐገሪቱ ምክር ቤት ዛሬ አፅድቆታል።የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እና አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ግን አዋጁን ተቃዉሞታል።ፕሬዝዳንት ሳሌሕ በመጪዉ ጥር መጀመሪያ ሥልጣን ለመልቀቅ የገቡትን ቃልም ተቃዋሚዎቹ አልተቀበሉትም።የመንግሥት ባለሥልጣናትና የጦር አዛዦች ሥልጣናቸዉን እየለቀቁ ተቃዋሚዎቹን ተቀይጠዋል።ነጋሽ መሐመድ የመንን ዉሉ ባጭሩ ይቃኛል።

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጊዶ ቬስተርቬለ አስተያየት፥ ወይም የወዳጅነት ምክር አመት አልፎታል።እና ዛሬ ነበር ነዉ-የሚባል።ሚንስትሩ ግን ያኔ ያሉትን አልረሱትም።ለደቡባ አረቢያዊቱ ሐገር፥ ለመንግስቷም ይበጃል ያሉትን ለሐገሪቱ መሪ ገና ከአንድ አመት በፊት ነገርኳቸዉ አሉ-ትናንት አስታወሰዉ።

«ከአንድ አመት በፊት የመንን በጎበኘሁበት ወቅት ፕሬዝዳት ሳሌሕ (ከተቃዋሚዎች ጋር) ለብሔራዉ ዉይይት እንዲጥሩ ጠይቄያቸዉ ነበር።የየመንን ችግር በወታደራዊ ሐይል መፍታት ይቻላል ብለዉ እንዳያምኑ አሳስቤያቸዉ ነበር።ጊዜዉ ምንም ሳይሰራበት ሔደ።»

Jemen Proteste Demonstration gegen Präsident Ali Abdullah Saleh in Sanaa
ሕዝባዊ አመፅናምስል AP

የሰላሳ-ሁለት አመቱ ገዢ፥ የሁለቱ የመኖች አንድ አድራጊ፣ ግን ቀድሞዉ አስር-አለቃ የበርሊኑን ትልቅ ዲፕሎማት ምክር-ዝክር ሰሙ እንጂ አላደመጧቸዉም።የጊዜዉ ሒደት ያገዛዛቸዉ ፅልመት ምፅዓት መሆኑንም አላስተዋሉም።ወይም ሰላሳ-ሁሉት አመት የኖሩበት ቤተ-መንግሥት ምቾት፥ የገዙበት ሐይል-ጉልበት ማስተዋያቸዉን ነፈጋቸዉ።

ከሰባት ሳምንት በፊት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አደባባይ መዉጣት ሲጀምሩ ከሰነዓ እና ከአደን የተሰማዉ መልዕክት ከሳቸዉ በስተቀር ለሌዉ ግልፅ ነበር።የደወሉን ድምፅ ለመስማት፥ የቱኒዝና የካይሮ ብጤዎቻቸዉን እዉነት ለማየት በቂ ጊዜ ነበራቸዉ። እንደ ገና አልሰሙም።እንደገና አላዩም። ወይም ሁለቱንም አልፈለጉም።ይልቅዬ ለሰላማዊ ጥሪ አደባባይ የወጣ ሕዝባቸዉን በጥይት ያስለቅሙት ገቡ።የአርቡ የከፋ ነበር።በጥቂት ሠዓታት ከሐምሳ በላይ ሰዉ ተገደለ።ከሁለትለት መቶ በላይ ቆሰለ።የፖለቲካ አዋቂ አብዱል ጋኒ አል-ኢርያኒ እንደሚሉት ግድያዉ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይደረጋል የሚለዉን ተስፋ የሚያጨናጉል ነዉ።

«ይሕ በጣም አደገኛ ሁኔታ ነዉ።ሥርዓቱ የወሰደዉ የሐይል እርምጃና ሆን ተብሎ የተፈፀመዉ ግድያ ካሁኑ ችግር በሰላማዊ መንገድ የሚወጣበትንና የሰላማዊ የሥልጣን ሽግግርን ተስፋ የሚዘጋ ነዉ።»

የፖለቲካ አዋቂዉ ይበሉ እንጂ ምዕራባዉያኑ በፕሬዝዳት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ ላይ እንደ ቃዛፊ አልጨከኑም።የሳሌሕ ታማኞች የሐይል እርምጃ፥ ግድያ ቀጠለ።የሟች ቁስለኛዉ ቁጥር ሲበረክት የፕሬዝዳት ሳሌሕ የሰላሳ-ሁለት ዘመን አገዛዝም ይፈረካከስ ገባ።ዲፕሎማቶች፥ሚኒስትሮች፥ የምክር ቤት እንደራሴዎች፥ የጦር ጄኔራሎች ሕዝብ ከራቀዉ ሥርዓት እየራቁ ከለዉጥ ፈላጊዉ ጎን ተሰለፉ።

ፕሬዝዳቱ የተባባሰዉን ሕዝባዊ አመፅ ለመግታት እልባት ያሉትን ሁለት ነገር ትናንት እና ዛሬ አደረጉ።ሥልጣናቸዉን በመጪዉ ጥር እንደሚለቁ አስታወቁ።ዛሬ ለአንድ ወር የሚፀና ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤታቸዉ አሳወጁ።የተቀበላቸዉ የለም።የመናዊዉ ጋዜጠኛ እንደሚለዉ ከሳሌሕ አገዛዝ መወገድ በመለስ ለየመን መፍትሔ የለም።

ፕሬዝዳንቱ እስካሁን አልሰሙም።ዛሬዉኑ የሰሜን ምዕራብ እዝ ጦር አገዛዛቸዉን በመቃወም አመፅኛዉን ሕዝብ መቀላቀሉን ግን በርግጥ ሰምተዉታል።ዛሬዉኑ ሰነዓ አደባባይ የወጣዉ ሕዝብ ለአራጅ አንገዛም የሚል መፈክር ማንገቡን ሳሌሕ ባያዩት-ሰምተዉታል።

NO FLASH Der Präsident von Jemen Ali Abdullah Saleh
ሳሌሕምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ