1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ሰብዓዊ እርዳታና ችግሩ

ሰኞ፣ ግንቦት 17 2007

የመን የገባውን ሰብዓዊ እርዳታ ፣ በየመን ከተሞች በሙሉ ማከፋፈል አለመቻሉን የተመድ አስታወቀ ።የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን የየመን ቢሮ ቃል አቀባይ ሙጂብ ሃሰን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በሁቲ አማፅያን ቁጥጥር ስር ባሉ አንዳንድ ከተሞች የእርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞች እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው እርዳታ ማከፋፈል አልቻሉም ።

https://p.dw.com/p/1FWFp
Jemen Krieg Zerstörung Militärcamp
ምስል picture alliance/AA/A. M. Yahya Haydar

ሆኖም በዚህ ሳምንት ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የየመን ተፋላሚ ኃይላት የሰላም ንግግር ችግሩን ያቃልላል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ።ይሁንና ጉባኤው ላልተወሰነ ጊዜ መገፋቱ እየተነገረ ነው ።

በየመን የተኩስ አቁም በተደረገባቸው 5 ቀናት አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ አቅርቦች ሃገሪቱ ማስገባት እንደተቻለ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል ። በዚሁ የ5 ቀናት ሰብዓዊ ፋታ የUNHCRን እርዳታ የጫኑ 6 አውሮፕላኖች ዋና ከተማይቱ ሰንአ መግባት ችለዋል ።በዚሁ ወቅትም ድርጅቱ ከየአካባቢው ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ይዞታም ተመልክቷል ። የHNHCR የየመን ቢሮ ቃል አቀባይ ሙጂብ ሃሰን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ውጊያና የአየር ድብደባው ቀድሞም ችግር ውስጥ የነበረውን የሃገሪቱን ኤኮኖሚና ህዝቧን ይበልጥ ጎድቷል ።በተኩስ አቁሙ ቢያንስ ሰብዓዊ እርዳታ ለማስገባት መቻሉ መልካም ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር ሲታይ ግን በቂ ሆኖ አላገኙትም ።

«የተኩስ አቁሙ መጠነ ሰፊ ለውጥ አምጥቷል።እርግጥ በቂ አይደለም ። ምክንያቱም ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ። የመኖችም በአጠቃላይ የኤኮኖሚ ችግር ውስጥ ወድቀዋል።አብዛኛው ህዝብ የኤኮኖሚ ችግር ውስጥ ነው የሚገኘው ።ከድህነት ወለል በታች የሆነ ህይወት ነው የሚመሩት።ስለዚህ በቂ አይደለም »

Jemen Bombenanschlag auf eine Moschee in Sanaa
ምስል Reuters/K. Abdullah

ሆኖም ቃል አቀባዩ በየመን በሁቲ ሚሊሽያዎች ላይ የአየር ድብደባ የሚያካሂደው በሳውዲ አረቢያ የሚመራው የአረብ ሃገራት ህብረት ከተኩስ አቁሙ በኋላ በቀጠለው የአየር ጥቃት ወደቦችንና አውሮፕላን ማረፊያዎችን እንደማይመታ ማስታወቁ ለቀጣዩ የእርዳታው አቅርቦት ተስፋ ሰጭ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎችም ትልቅ ድጋፍ ነው ይላሉ ።ሆኖም ሙጂብ ሃሰን እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ከተሞች የእርዳታ ድርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታ ማከፋፈል አለመቻላቸው አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል ።

«ለኛ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ የመን ማስገባት ትልቅ ጉዳይ ነው ። ሆኖም ሰብዓዊ እርዳታውን በተጨማሪ እርዳታው ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ማድረስ ማከፋፈልም አለብን ።ይህ ደግሞ በተፋላሚ ኃይላት የሚወሰን ነው የሚሆነው ።አንዳንድ መንግስታዊ ካልሆኑ የሃገር ውስጥ የእርዳታ ድርጅቶች በአንዳንድ አካባቢዎች እርዳታ ለማከፋፈል ሲሞክሩ የሁቲ ሚሊሽያዎች እንደሚከለክሏቸው ይናገራሉ ።ይህን የሚያደርጉትም እርዳታው እንዲደርስ የሚፈለግበት ቦታ ያሉት ሰዎች የነርሱ ደጋፊዎች ባለመሆናቸው ነው ። ይህም በእጅጉ ያሳስባቸዋል »

ሆኖም በዚህ ሳምንት ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ሊካሄድ የታቀደው የየመን ተፋላሚ ኃይላት የሰላም ንግግር ችግሩን ያቅላል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር።ይሁንና ጉባኤው ላልተወሰነ ጊዜ መገፋቱን በስደት ላይ የሚገኙት የየመን ፕሬዝዳንት አብዱ ራቡ ማንሱር ሃዲ ረዳት ተናግረዋል ።የተመድ ግን የጉባኤውን ለሌላ ጊዜ መገፋት አላረጋገጠም ።የመን ውስጥ ከ250 ሺህ እስከ 300 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች ይገኛሉ ። አብዛኛዎቹም ደቡብ የመን ውስጥ ባሉ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ነው ያሉት ። ከነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች አንዳንዶቹ የመኑ ግጭት ሰለባዎች መሆናቸው አልቀረም ። ሙጃብ UNHCR ስደተኞቹን ወደ ተሻሉ አካባቢዎች ለመውሰድ እየተሞከረ መሆኑንም ተናግረዋል ።

Jemen Ende der Waffenruhe
ምስል M. Huwais/AFP/Getty Images

«አደን ውስጥ ያለው አልባ ባሽቲን መጠለያ ጥቃት ደርሶበታል ከአደን ብዙም የማይርቀው በሃላል መጠለያ ጣቢያም ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነው ።ብዙዎቹ ስደተኞች UNHCR እንዲረዳቸው ጠይቀዋል ።ሆኖም መጀመሪያ ላይ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት በርካታ ሠራተኞቻችን ከሃገሪቱ ወጥተው ነበር ። አሁን ግን የድርጅቱ ሃላፊና ሌሎች የድርጅቱ ሠራተኞች ተመልሰው ሥራ ጀምረዋል ።ስደተኞቹን ለመርዳትና ደህንነታቸው ሊጠበቅ ወደሚችልባቸው አካባቢዎች ለመውሰድ ከነርሱ ጋር ግንኙነት ፈጥረናል ። ከአካባቢው ህዝብ ጋር በመተባበርም ከሶማሊያ የመጡ በርካታ ስደተኞች ወደ ጁቡቲና ሶማሊያ እንዲሄዱ ተደርጓል ።»

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ