1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የየመን ቀዉስና የዉጪ ሐይላት

ሰኞ፣ የካቲት 23 2007

የሁቲ አማፂዎች ርዕሰ-ከተማ ሰነዓ የዶለዉ ግን ከኢራን ርዳታ ይልቅ በዩናይትድ ስቴትስና በአረብ ተባባሪዎችዋ የሚረዱት የየመን ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ግራ አጋቢ ግን ተመሳሳይ የጅል ስልት ነዉ።የፕሬዝዳንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ፤ የዓሊአብደላ ሳላሕና የጄኔራል አሊማ ሑሴይን ተቃራኒ ግን ተመሳሰይ ሴራ።

https://p.dw.com/p/1EjzE
ምስል picture-alliance/AP Photo/Mohammed

የየመን ሕዝብ ሠላም፤ ፍትሕ፤መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በየአደባባዩ ይሰለፋል።የጎሳ መሪዎች፤ የጦር ጄኔራሎች፤ ፖለቲከኞችና ቴቱጃሮች ለሥልጣን ይፋለማሉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማቶች ተፋላሚ ሐይላትን ለማደራደር ከኒዮርክ፤ ሰነዓ፤ ከሪያድ ዶሐ ይመላለሳሉ።አሜሪካኖች ከተፋላሚ ሐይላት አንዱን ደግፈዉ፤ሌላዉን አግልለዉ፤ ሌላዉ በአሸባሪነት እየወንጀሉ ይወጋሉ።ሳዑዲ አረቢያዎች የአሜሪካኖችን መስመር ተክትለዉ የአሜሪካኖችን ወዳጆች ይደግፋሉ።ርዕሰ-ከተማ ሰነዓን የሚቆጣጠሩት ግን አሜሪካኖችም፤ ሳዑዲ አረቢያም፤ ሌሎች አረቦችም የሚቃወሟቸዉ፤ ኢራኖች የሚደግፏቸዉ ሐይላት ናቸዉ። የየመን ቀዉስና የዉጪ ሐይላት ሽኩቻ የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ ።

በመጀመሪያ ሥሙ ብቻ ሁሴይን መባሉን የመረጠዉ የሰነዓ ነዋሪ እንደ አብዛኛዉ የመናዊ ሁሉ የቀድሞዉ የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት የዓሊ አብደላሕ ሳላሕ አምባገነናዊ ሥርዓት እንዲወገድ በአደባባይ ሲሰለፍ፤ ሲጮሕ ሲታገል ነበር።ለሠላሳ ሰወስት ዘመናት የፀናዉ የሳላሕ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥት በ2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) መወገድ ግን የነሁሴይንን ፍላጎት፤ የሐገራቸዉን ሠላምና ደሕንነት ለማረጋገጥ የተከረዉ የለም።

የሳላሕን ሥልጣን የተረከቡት የቀድሞዉ የሳላሕ ምክትል መንሱር አብድ ረቦ ሐዲ ለሥልጣን ያበቃቸዉን ሕዝብ ጥያቄ ከማሟላት ይልቅ በትረ-ሥልጣናቸዉን የሚያጠናክሩላቸዉን የዉጪና የዉስጥ ሐይላት ፍላጎትን ለማሟላት ሲባትሉ-ወትሮም ሠላም የማታዉቀዉን ሐገር ከከፋ ሥርዓተ አልበኝነት፤ ከጦርነትና ትርምስ ማጥ ዶሏት።

ከአረብ የደኸየችዉን ሐገር ደሕ-ሕዝብ ከድሕነትም አልፎ ለረሐብ እና ርዛት አጋለጡት።እነ ሁሴይን መከራዉን ለማስወገድ ያላቸዉ አቅም-አንድ ነዉ።የአደባባይ።«ይሕን በሙስና የተዘፈቀ መንግሥት እየተቃወምን ነዉ።ምክንያቱም ከ2011ዱ አብዮት ወዲሕ የመን ዉስጥ ምንም የተለወጠ ነገር የለም።እንዲያዉም ሁሉም ነገር እየከፋ ነዉ።ፀጥታዉ፤የትምሕርቱና፤ የጤናዉ ሥርዓት እየተበላሸ ነዉ።ሥለዚሕ ይሕ መንግሥት ከቀዳሚዉም በጣም በሙስና የተዘፈቀ ነዉ።ሥራዬ አስተራጓሚነት ነዉ።ሐገር ጎብኚዎች ወደየመን መምጣት ሥላቆሙ ሥራ ከፈታሁ ቆይቻለሁ።ነዉ።ሥለዚሕ በግሌ በጣም የጎዳኝ ፀጥታዉ መናጋቱ ነዉ።»

Jemen Demonstration gegen die Huthi-Miliz in Taiz
ምስል Reuters/Anees Mahyoub

የፕሬዝዳንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ መንግሥት የተናጋዉን ፀጥታ ለማረጋጋት ያደረገዉ ጥረት የለም።በመሠረቱ ነበር።የጎሳ መሪዎች፤ የታጣቂዎች ወይም ያማፂ ቡድን አዛዦች፤ የጦር ጄኔራሎች ያሻቸዉን በሚያደርጉባት የመን ማዕከላዊዉ መንግሥት ያለዉ እቅም ትንሽ ወይም ምንም ነዉ።

የሰነዓዉ ተባባሪ ዘጋቢያችን ግሩም ተክለ ሐይማኖት።የየመን መንግሥት እንደግፋለን የሚሉት ሳዑዲ አረቢያ፤ የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ አረብ ሐገራት እና ዩናይትድ ስቴትስ በዝባዊ ተቃዉሞ፤ በተከፉና ለሥልጣን በሚቋምጡ ጄኔራሎች፤ከደቡብ ተገንጣዮች፤ ከመሐልና ከደቡብ የአል ቃኢዳ ታጣቂዎች፤ ከሰሜን የሁቲ አማፂያዎች የሚያካልቡትን የመንሱር አብድ ረቦን መንግሥት ለማጠናከር የተከሩት የለም።ወይም አልፈለጉም።

ዩናይትድ ስቴትስ የአልቃኢዳ አሸባሪዎች የምትላቸዉን ሐይላት በሰዉ አልባ አዉሮፕላን ከመግደል-ወይም በተባባሪዎችዋ ከማስገደል ባለፍ የመከረኛይቱ ሐገር መከራ እንዲያበቃ ምንም አላደረገችም።ሳዑዲ አረቢያ ከጄኔራል፤ ጄኔራል እያማረጠች በመርዳት ትርምሱን ማጋጋሙን የመረጠች ነዉ-የሚመስለዉ።

የሳዑዲ አረቢያዊዉ የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ኻሊድ ባትራፊ በቅርቡ እንዳሉት ግን ሪያድ ቢሆንላት የምትደግፈዉ መንግሥትን ነበር።የመን ደግሞ መንግሥት የለም።

«ሳዑዲ አረቢያ ለወትሮዉ የምትደግፈዉ(የየመን) መንግሥትን ነዉ።አሁን ግን መንግሥት የታለ።መንግሥቱ በሁቲና በተዘዋዋሪም በኢራን ታግቷል።ሥለዚሕ መንግሥትን የምትደግፈ ከሆነ የሚሰጠዉ ድጋፍ ለተቃራኒዉ ወገን ላለመድረሱ እርገጠኛ መሆን አትችልም።ሥለዚሕ አሁን ባለበት ደረጃ ማድረግ የሚቻለዉ እነዚሕ አሸባሪዎች ድንበራችንን አቋርጠዉ እንዳይገቡ ወይም የጦር መሳሪያ አስርገዉ እንዳያስገቡ፤ ወይም ሁቲዎች ከጥቂት አመታት በፊት እንዳደረጉት ደቡባዊ ግዛታችንን እንዳያጠቁ ድንበራችንን መቆጣጠር ብቻ ነዉ።»

ከሃያ-ሰባት ሚሊዮኑ የየመን ሕዝብ አምስት ከመቶ የሚቆጠሩት ሁቲዎች አሁን ከደረሱበት ለመድረሳቸዉ፤ አያሌ ታሪካዊ፤ ፖለቲካዊ፤ ሐይማኖታዊ ምክንያት-እዉነቶችን መደርደሩ አይገድም።ኢራንም የሥልታዊ ጠላቶችን የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤልን ወይም እንደ ና የሳዑዲ አረቢያንና ባሕሬን ያሉ ተፎካካሪዎችዋን እንቅስቃሴ እግር በእግር እየተከታተለች ጥቅሟን ለማስከበር መፍረምረሟም ግልፅ ነዉ።

Abd Rabbo Mansur Hadi Präsident Jemen
ምስል picture-alliance/dpa/AP Photo//Yemen's Defense Ministry

የቴሕራን መሪዎች ከኢራቅ፤ እስከ ሶሪያ ከግብፅ እስከ ሱዳን እንዳደሩጉት ሁሉ የጠላቶቻቸዉን ወይም የተፎካካሪዎችዋን የበላይነት ለመገደብ የመን ዉስጥ እግሯቸዉን ለመትከል የሁቲ አማፂያንን ለአስር ዓመታት ያክል ሲረዱ ነበር።

የሁቲ አማፂዎች ርዕሰ-ከተማ ሰነዓ የዶለዉ ግን ከኢራን ርዳታ ይልቅ በዩናይትድ ስቴትስና በአረብ ተባባሪዎችዋ የሚረዱት የየመን ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ግራ አጋቢ ግን ተመሳሳይ የጅል ስልት ነዉ።የፕሬዝዳንት አብድ ረቦ መንሱር ሐዲ፤ የዓሊአብደላ ሳላሕና የጄኔራል አሊማ ሑሴይን ተቃራኒ ግን ተመሳሰይ ሴራ።

ሐዲ በሪያድና በዋሽግተን ደጋፊዎቻዉ እየተገፉ አንዱን ታጣቂ ሐይል በሌላዉ ታጣቂ፤ ወይም ጦር ሐይል ለማስመታት ሲያሴሩ፤ የቀድሞዉ የሐዲ አለቃ ዓሊ አብደላ ሳሌሕም በልጃቸዉ በጄኔራል አሕመድ ዓሊ በኩል የሰነዓን ቤተ-መንግሥት ዳግም ለመቆጣጠር ተመሳሳዩን ስልት ያዉጠነጥኑ ነበር።ሐዲ የጄኔራል ሁሴንና የጄኔራል አሕመድን ሥጋት ለማስወገድ ሁቲዎች ሰነዓ እንዲገቡ በር ከፈቱላቸዉ።አከታትለዉም ሁለቱን ጄኔራሎች በአምባሳደርነት ሥም ወደ ሌላ ሐገር ሸኙ።

ይሕ ያናደዳቸዉ ዓሊ አብደላ ሳላሕ ባንፃሩ ወደ ሰነዓ የሚገሰግሱትን የሑቲ አማፂያንን የሌሎች ጎሳ ታጣቂዎች እንዳይወጓቸዉ አግባቡላቸዉ።ሁቲዎች ባለፈዉ መስከረም ሰነዓ ከገቡበት የሐዲን መንግሥት በግልፅ ከሥልጣን እስካስወገዱበት ድረስ ግልፅ ዉጊያ የገጠማቸዉ ከአል ቃኢዳ ታጣቂዎች ብቻ ናቸዉ።

የአል ቃኢዳ ታጣቂዎችን ደግሞ የአሜሪካ ሰዉ አልባ የጦር አዉሮፕላኖች እያደኑ ይለቅሟቸዋል።በዚዚሕም ሰበብ በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ሚሊሺያዎች ያለብዙ ተቀናቃኝ ርዕሠ-ከተማ ሰነዓን ሙሉ በሙ ተቆጣጠሩ።

በየአደባባዩ የሚሰለዉ የመናዊ ለጥይት ራትነት ተዳረገ እንጂ ጩኸቱ ሰሚ አላገኘም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማቶችም ተቀናቃኝ ሐይላትን ለመሸምገል ያደረጉት ሙከራ ያመጣዉ ለዉጥ የለም።እንዲያዉም ድርድር መጀመሩ ተነግሮ ሳያበቃ ሐገሩ በዉጊያ መተራመሷን ያየዉ የሰነዓ ነዋሪ አደራዳሪዎቹን እንደ ገደ-ቢስ ይመለከቷቸዉ ያዘ።

Jemen Mohammed Houthi
ምስል Reuters/Khaled Abdullah

የሰነዓዎች ጭንቀት፤ መገደል፤ መራብ መጠማትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት አደራዳሪዎች ዉል አልባ ዲፕሎማሲ የምዕራባዉያንንም ሆነ የአረብ ተባባሪዎቻቸዉ መንግሥታት ልብን ለሁነኛ መፍትሔ የሚያነሳሳ አልሆነም።በተቃራኒዉ የሁቲ ሚሊሺያዎች ሰነዓን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸዉ ሲረጋገጥ ኤምባሲዎቻቸዉን እየዘጉ ከሰነዓ ዉልቅ አሉ።

ምዕራባዉያንና የአረብ መንግሥታት ኤምባሲዎቻቸዉን መዝግታቸዉን ባስታወቁበት ሳምንት የዩናይትድ ስቴትስ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ዋሽግተን ላይ ገጥመዉት የነበረዉ ክርክር ሥለየመን ሕዝብ የወደፊት ዕጣ ፋንታ አልነበረም።ሥለ አካባቢዉ ሠላምም አልነበረም።ዩናይትድ ስቴትስ የመን የመሸጉ ተጠርጣሪ የአልቃኢዳ አባላትን መግደል-ማስገደሏን ማቆም-የለባትም-አለባት የሚል ነበር እንጂ።

የአረብ ሐገራት የኦማንን እና የኢራንን ምዕራባዉያን ደግሞ የሩሲያና የቻይናን ዲፕሎማቶች ሰነዓ ላይ ትተዉ ሲወጡ፤ ኢራን ባንፃሩ ለታማኝ ወዳጆችዋ ድል ከቴሕራን፤ ሰነዓ የቀጥታ የአዉፕራላን በረረ ጀመረች።መሐን የተሰኘዉ የኢራን አየር መንገድ በቀን ሁለቴ፤ በሳምንት አስራ አራቴ ከእና ወደ ቴሕራን ሰነዓ ይበራል።ኢራኖች በሁቲዎች በኩል ሰነዓን መቆጣጠራቸዉን በአዉሮፕላን በረራቸዉ ሲያረጋግጡ ከሰነዓ ቤተ-መንግሥት ጠፍተዉ የድሮ ከተማቸዉ አደን-ደቡብ-የመን የገቡት አብድረቦ መንሱር ሐዲ ባንጻሩ ሁቲዎች ወደ ደቡብ የሚያደረጉትን ጉዞ ለመግታት የጎሳ መሪዎችን እያስተባበሩ ነዉ።

የቀድሞዉ ጄኔራል ሰነዓን ለሁቲዎች አስረክበዉ እንደ ሴት ጅልባብ ለብሰዉ ወደ አደን ሲሸሹ የሰነዓ ኤምባሲዎቻቸዉን ለመዝጋት የተጣደፉት የአካባቢዉ አረብ ሐገራትም ሐዲን ተከትለዉ አደን ላይ አዲስ ኤምባሲ ከፍተዋል።እስካሁን ድረስ ሳዑዲ አረቢያ፤ኩዌይትና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፤ ኤምባሲ መክፈታቸዉን ሲያስታዉቁ።ቀጠር ሰሞኑን ለመክፈት እየተዘጋጀች ነዉ።

ፕሬዝዳንት ሐዲ የጎሳ መሪዎችን ድጋፍ መጠየቃቸዉ፤ኢራንን በክፉ የሚይዋት የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ አካባቢ ሐገራት ሐዲን ተከትለዉ አደን ላይ ኤምባሲ መክፈታቸዉ፤ አንዳድ የየመን የፖለቲካ ተንታኞች የሌላ ጦርነት ዝግጅት አድርጎዉ ነዉ ያዩት።

Jemen Huthi-Rebellen verkünden Übergangsverfassung
ምስል picture-alliance/dpa/Str

የመን ከሕዝቧ ቁጥር በሰወስት እጥፍ የሚቆጠር ጦር መሳሪያ በየቤቱ ተከማችቶባታል።ሕዝብ ግን ይራብባታል።እንደ ሁቲ አማፂያን ሁሉ የየዛይዲ ሺዓ ዕምነት የሚከተሉት ዓሊ አብደላ ሳሌሕም፤ የደቡብ ኮሚንስት የነበሩት አብድ መንሱር ሐዲም፤ የሁቲ አማፂያንም ለየመን ቢያንስ እስካሁን የተከሩት ነገር የለም።የቴሕራን-ዋሽግተን-ሪያድ መጓተትም ከየመን አልፎ ሰላም የማያዉቀዉን ያን አካባቢን ይበልጥ ከማንደድ ሌላ የሠላም ጭላንጭል እንኳ አይታይበትም።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ