የየመን ውጥንቅጥና የጸጥታ ስጋት
ሰኞ፣ መጋቢት 14 2007በየመን የሑቲ አማጽያን ፕሬዚደንትአብዱራባህማንሱርሃዲ ከሰንዓ ሸሽተዉ ወደ ተሸሸጉባት ኤደን እየገሰገሱ ነው። በየመን ሶስተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ታዒዝ የሚገኘውን የአዉሮፕላን ማረፊያ እሁድ መጋቢት 13/2007 የተቆጣጠሩት ሰሜናውያኑ የሺዓ አማጽያን ዛሬ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችን በመላክ ከሱኒዎች ጋር ውጊያ ላይ መሆናቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ባለፈው ሳምንት ለተፈጸመውና 29 ወታደሮች ለሞቱበት ጥቃት ራሱን እስላማዊ መንግስት ከሚለዉ ፅንፈኛ ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አለኝ የሚለው በየመን የአልቃኢዳ ክንፍ ሃላፊነት መውሰዱን አሶሲየትድ ፕረስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የፖለቲካ ተንታኙ ዩሱፍ ያሲን በየመን የታጣቂዎች እና የውጭ ሃይሎች መበራከት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዳለው ሃገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊከታት ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
«በየመን የሑቲ አማጽያን፤የቀድሞው ፕሬዝዳንት አሊ አብደላ ሳልህ ወታደሮች እና የጎሳ ሚሊሺያዎች አሉ።የደቡብ ንቅናቄም አለ።የሳዑዲ አረቢያ እና የገልፍ አገሮች ትብብር አቋም አለ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይኸ ጉዳይ የየመንን አንድነት ብቻ ሳይሆን ያካባቢው ሰላምና ጸጥታን ያደፈርሳል በሚል ጣልቃ እንዲገቡ እየተማጸኑ ናቸው። ግን ጣልቃ ከመግባታቸው በፊት እነሱ(የሑቲ አማጽያን) እስከ ኤደን ድረስ ሄደው ለመቆጣጠር እየሞከሩ ስለሆነ ይኸ ነገር ወደ ርስ በርስ ጦርነት ያመራል የሚለው ስጋት እንዳለ ነው።»
የመን በአልቃኢዳ ላይ ይደረግ በነበረው ዘመቻ አጋር የነበረች ቢሆንም አሁን ግን በኢራን እና ሳዑዲ አረቢያ የእጅ አዙር ጦርነት፤ በሺዓ እና ሱኒ ፍጥጫ ታምሳለች። ዩናይትድ ስቴትስ የመን ዉስጥ የነበራትን የመጨረሻ ኃይል ዛሬ ማስወጣቷ ተዘግቧል። የየመን መታመስ ግን በዚያው በየመን የሚያበቃ አይመስልም። ዩሱፍ ያሲን የውክልናው ጦርነትም ይሁን የታጣቂዎቹ እና የጦር ጄኔራሎቹ ፍጥጫ ሙሉ ቀጠናውን እንደሚያተራምሰው ይናገራሉ።
የሑቲ አማጽያን የሚዋጉት ከፕሬዚደንትአብዱራባህማንሱርሃዲ ሃይሎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከእስላማዊ መንግስት ግንኙነት አለኝ ከሚለው የየመን የአልቃኢዳ ክንፍ ጋር ጭምር ነው። አማጽያኑ የየመን ዋና ከተማ ሰንዓን ከመንግስታዊ ጽሕፈት ቤቶች ጋር ቢቆጣጠሩም እስካሁን መንግስት ለመመስረት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም። ከቀድሞው መሪ አሊ አብደላ ሳልህ በኋላ የፕሬዝዳንትነት መንበሩን የተረከቡት እና ሰንዓ ዉስጥ ከቆዩበት የቁም እስር አምልጠዉ ኤደን ላይ የከተሙት ማንሱር ሃዲ ደግሞ ሀገሪቱን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ የሚያረጋጋ ሃይል እንደሌላቸዉ እየታየ ነዉ። እናም የየመን እጣ ፈንታ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ከመዳከር ጋር ተመሳስሏል። ይህን ክፍተት በሀገሪቱ የሚገኘው አልቃኢዳ እና ኢራቅ እና ሶርያን የሚያምሰው እስላማዊ መንግስት ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚለው ስጋት አይሏል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ