1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ ገቡ

እሑድ፣ ሐምሌ 19 2007

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳት ባራክ ኦባማ የኬንያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ኢትዮጵያ ገቡ። ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

https://p.dw.com/p/1G4xx
Äthiopiens Pemierminister Hailemariam Desalegn begrüßt US Präsident Barack Obama in Addis Abeba
ምስል Reuters/J. Ernst

ኦባማ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና የአከባቢው ሃገራት መሪዎች በተገኙበት መድረክ በአከባቢያዊ የፀጥታ ስጋቶችና በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩም ተዘግቦአል። ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን የጎበኙ በስልጣን ላይ የሚገኙ የመጀመርያዉ ጥቁር የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት ናቸዉ። ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት በናይሮቢ ስታዲዮም በሺ ለሚቆጠሩ ኬንያውያን ንግግር አድርገዋል። ኦባማ ለኬንያ ህዝብ ባደረጉት ንግግር በኬንያ ዲሞክራሲ ዘላቂነት እንዲኖረው የሁሉም ሰው ነፃነት መከበር አለበት ሲሉ አሳስበዋል። ከነዚህ መብቶች መካከል ህፃናት እና እናቶች እንደ ሁለተኛ ደረጃ መቁጠሩ እንዲቆም ይመለከታል። ከዚህ በተጨማሪም ኬንያ ሙስናን ከሀገሪቱ ማጥፋት እና በተለያዩ ጎሳዎች መካከል ያሉ ጭቆናዎች መቆም እንዳለባቸው ኦባማ አሳስበዋል። ከዚህም ሌላ ኦባማ፤ «የአፍሪቃ የወደፊት እጣ ፋንታ በራሷ በአፍሪቃውያን እጅ ስር ነው» «አፍሪቃ ለረዥም ጊዜ የውጭ አካል መጥቶ ለችግሮቿ በሙሉ ኃላፊነት የሚወስድ ስትጠብቅ ቆይታለች» ሲሉ ፕሬዚዳንቱ በኬንያ የመጨረሻ ጉብኝታቸው ቀን ተናግረዋል። እሁድ ማምሻውን ኢትዮጵያ የገቡት ፕሬዚዳት ኦባማ ማክሰኞ ዕለት መቀመጫውን አዲስ አበባ ባደረገው የአፍሪቃ ህብረት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በአፍሪቃ ህብረት ንግግር ሲያደርግ ይህ የመጀመሪያው ይሆናል።

Äthiopiens Pemierminister Hailemariam Desalegn begrüßt US Präsident Barack Obama in Addis Abeba
ምስል Reuters/T. Negeri

አዜብ ታደሰ

ልደት አበበ