1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬኗ ፖለቲከኛ ቲሞሼንኮ

ረቡዕ፣ የካቲት 19 2006

ባለፈው ቅዳሜ በነፃ የተለቀቁት የቀድሞዋ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዩልያ ቲሞሼንኮ ለፕሬዝዳንትነት የመወዳደር እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል ። ከእስር እንደተለቀቁ ወደ ክየቩ የነፃነት አደባባይ በመሄድ ደስታቸውን እዚያ ከተሰበበሰው ከ100 ሺህ ከሚበልጥ ህዝብ ጋር የተጋሩት ቲሞሼንኮ በውዝግቡ የተገደሉት ሰዎች ጉዳይ እንዲጣራም ጠይቀዋል ።

https://p.dw.com/p/1BFY2
ምስል Reuters

የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ነፃ በመለቃቀቸው ደስታና ፈንጠዝያ የፈጠረውን ያህል ነቀፌታም ይሰነዘርባቸዋል ። ስለቲሞሼንኮ የዶቼቬለው ሽቴፋን ላክ ያዘጋጀውን ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች

እጎአ በ2004 የተካሄደው የዩክሬን ቡርቱካናማው አብዮት ጀግና የሚባሉት የ53 ዓመቷ ዩልያ ቲሞሼንኮ ሁለት ጊዜ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ ። እጎአ ከጥር እስከ መስከረም 2005 እንዲሁም ከታህሳስ 2007 እስከ መጋቢት 2010 ።እጎአ መጋቢት 2010 ነበር የዩክሬን ፓርላማ የመታመኛ ድምፅ ነፍጓቸው ከሥልጣን የወረዱት ። ቲሞሼንኮ በውድ ዋጋ ከሩስያ የተፈጥሮ ጋዝ ለመግዛት ተዋውለዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ በ2011 ጥፋተኛ ተብለው የ7 ዓመት እስር ተበየነባቸው ። ከሁለት ዓመት ተኩል እስር በኋላ ባለፈው ቅዳሜ የሃገሪቱ ፓርላማ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ወስኖላቸው በነፃ ተለቀቁ ። ቲሞሼንኮ ያሰቡት ተሳካላቸው ።

« አንድ ነገር ለመፈፀም ካሰብኩ ውጤቶችም ይገኛሉ ። ውጤቶች »

የቀድሞዋ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር በሃገሪቱ የተለያዩ ስብዕናዎች ካሏቸው ሰዎች አንዷ ከመሆናቸውም በተጨማሪ አወዛጋቢም ናቸው ። በአንዳንዶች ዘንድ በህዝብ ገንዘብ የበለፀጉ የጋዝ ልዕልት ተደርገው ነው የሚታዩት ። ሌሎች ደግሞ የዩክሬኑ ቡርትኳናማው አብዮት ተምሳሌት ነው የሚሏቸው ። ቲሞሼንኮ በኃይል ምንጭ ገበያ የተገኘን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አለግባብ ለግል ጥቅማቸው በማዋል የናጠጡ ባለኩባንያ ለመሆኑ በበቁበት በ90 ዎቹ ነበር እርሳቸው እንደሚሉት ሃገራቸውን ለማገልገል በፖለቲካው መስክ የተሰማሩት ።

Ukraine Parlament Kiew Julia Timoschenko Freilassung abgelehnt
የዩክሬን ፓርላማ ቲሞሼንኮ እንዲለቀቁ ሲወስንምስል Reuters

« ዘወትር ሰዎች እኔን የኤኮኖም ጥቅም ፈልጋ ነው እያሉ ይናገራሉ ። ለእኔ ግን ይሄ ጠቃሚ አይደለም እንደ ፖለቲካኛም ስለ ኔ የሚፃፈው ረብ የለውም እኔ ጠቃሚ አድርጌ የማየው ሥራየን ነው ። »

ቲሞሼንኮ በፖለቲካው መድረክ የተሳካላቸው በ2004 ነው ። በዚያን ወቅት በተጭበረበረ ድምፅ ሊዮኒድ ኩችማን ሥልጣን ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ ብርቱካናማው አብዮትን አነሳሳ ። ያኔ ቲሞሼንኮ ከቀድሞው ተቀናቃናቸው ከቪክቶር ዩስቼሼንኮ ጋር በዩክሬን የዴሞክራሲ ትግል እንዲካሄድ በማድረግ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ። ይሁንና በርሳቸውና በዩሴቼንኮ መካከል የነበረው የፖለቲካ ሽኩቻ ተራዝሞ በመቀጠሉ ዩክሬንን በፖለቲካው ረገድ አሽመድምዷት ነበር ። ሃገሪቱን ወደ ተሻለ አቅጣጫ ይመራሯታል የሚል ተስፋ የነበራቸው ብዙዎች ሰዎች በርሳቸው ክፉኛ ነበር ያዘኑት ። በ2010 ሳይታሰብ ቪክቶር ያኑኮቪች በሁለተኛ ዙር ምርጫ ፕሬዝዳንት ሆኑ ። ብዙም ሳይቆይ ተቀናቃናቸው ቲሞሼንኮ ከሩስያ ጋር በተስማሙት የጋዝ ግዥ ውል ተከሰው ለፍርድ ቀረቡ ። መጋቢት 2011 የ7 ዓመት እስር ና የ137 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት እንዲሁም በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ለ3 ዓመት ከመካፈል የሚያግድ ፍርድ ተበየነባቸው ። ከዚህ በኋላ የአውሮፓ ህብረት ያኔ በነበረው ተቃውሞ ሳቢያ ዩክሬንን የአውሮፓ ህብረት ተባባሪ ማህበረተኛ ለማድረግ ለፊርማ ቀርቦ የነበረው ሰነድ ውድቅ አደረገው ። እስር ቤት የታመሙት ቲሞሼንኮ የረሃብ አድማ ካደረጉ በኋላ በጀርመን ሃኪሞች እንዲታዩ ተፈቀደላቸው ። ግን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ተከልክለው ነበር ። ያልተቋረጠ የቪድዮ ቁጥጥርና ሁልጊዜም የሚጠብቃቸው የደህንነት ሰዎች ስለነበሩ ህክምናው አልተሳካም ። በ2012 የተካሄደውን ምርጫ እሥርር ቤት ሆነው ይከታተሉና ብዙውን ጊዜም መልዕክታቸውን ለህዝብ ያደርሱ ነበር ለምሳሌ ያህል በእስር ቤት የቀረፁት ንግግራቸውም በድብቅ እየወጣ ለህዝብ ይደርስ ነበር ። በአንድ ወቅት ቀርፀው ካስተላለፉት መልዕክት አንዱ

Ukraine Regierung Julia Timoschenko als Ministerpräsidentin Parlament in Kiew
ቲሞሼንኮ በ2007 በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመረጡምስል SERGEI SUPINSKY/AFP/Getty Images

« እያንዳንዱ ዩክሬናዊ ያኑኮቪች በዘረጉት ስርዓት ስር ባለ ወንጀል በሚፈፀምበት ሃገር መኖር እጣቸው ሆኗል ። ህጉ እንደሚጣስ ዜጎች ሙሉ በሙሉ እንደሚዋረዱ ሁሉም የሚያየው ነው ። እኔም ብሆን የዚህ ሰለባ መሆኔን እየተገነዘብኩት ነው »

ቲሞሽንኮ ከእስር ተለቀዋል ። የዩክሬን የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን መገመት አስቸጋሪ ነው ።

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ