1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩጋንዳ መንግሥት እና የደቡብ ሱዳን ዓማፅያን ንትርክ

ቅዳሜ፣ የካቲት 7 2007

ዩጋንዳ በሀገሯ የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ዓማፅያን ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ ከጥቂት ቀናት በፊት ትዕዛዝ አስተላልፋለች። ይኸው የዩጋንዳ ፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ የወሰዱት ውሳኔ ከዓማፅያኑ ብርቱ ወቀሳ ተፈራርቆበታል።

https://p.dw.com/p/1EbYx
Yoweri Museveni
ምስል picture alliance/empics

በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኙት ያማፅያኑ ቃል አቀባይ የቀድሞው የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ጦር መሪ ጆን ጋራንግ ፣ ማቢዮር ጋራንግ የፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ አስተዳደር ካምፓላ የሚገኙትን ጽሕፈት ቤቶቻቸውን እንዲዘጉ ማዘዙን ከሰሙ በኋላ የዩጋንዳ ውሳኔ የተሳሳተ መሆኑን አስታውቀዋል።

« እኛ ባካባቢው በቀላሉ የማይገመት ሚና እንደምንጫወት ሊረሳ አይገባም። ይህን የሚያደርግ ካለ በራሱ ላይ መዘዝ ማስከተል መሆኑን ሊያውቀው ይገባል። እኛ፣ ዩጋንዳ ውጡ አለች አላለች፣ የራሳችን ዓላማ አለን። እና ዩጋንዳ ከእኛ ጋ መስራት እስክትጀምር ድረስ፣ ተልዕኳችንን ለማሳካት መስራታችንን እንቀጥላለን። »

Südsudan Rebellen 10.02.2014
ምስል Reuters

ዩጋንዳ መንግሥት ይህን ውሳኔ የወሰደው ጁባ የሚገኘው የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቀናቃኞቹ ዓማፅያን በካምፓላ መቆየት መቀጠላቸው እንዳሳሰባቸው ከገለጹ በኋላ እንደሆነ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የዩጋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባለሥልጣን ትር ኦኬሎ ኦሪየም አስታውቀዋል። ዩጋንዳ ዓማፅያኑ በሀገሯ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀዷን ኦሪየም አረጋግጠዋል።

« ከመጀመሪያውም ዩጋንዳ ዓማፅያኑ በሀገሯ እንዲንቀሳቀሱ የፈቀደችው ቤተሰቦቻቸው በዚያ ስለሚኖሩ ነው። ዓማፅያኑ በፈለጉበት ጊዜ ዘመዶቻቸውን በነፃ እንዲጎበኙ አስችሏቸዋል። አሁን ግን ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ ከደቡብ ሱዳን ጋር ላለፉት ብዙ ዓመታት አዳጋች ሆኖ የቆየውን ግንኙነት ለማሻሻል ሲሉ ዓማፅያኑን ለማስወጣት ወስነዋል። »

በደቡብ ሱዳን መንግሥት አንፃር የሚዋጉት ዓማፅያን እና የመንግሥቱ ጦር ካለፉት 14 ወራት ወዲህ የቀጠሉትን ጦርነት ለማብቃት በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ደንብ መፈራረማችው ቢታወስም፣ ውሎቹ ተጥሰው ውጊያው አሁንም እንደቀጠለ ነው።

Südsudan Armeesprecher Philip Aguer
ፊሊፕ አግዌርምስል DW/A. Kriesch

ዓማፅያኑ በዩጋንዳ እና በደቡብ ሱዳን ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ የዩጋንዳን ውሳኔ እንደሚቀበሉ ያማፅያኑ ቃል አቀባይ ማቢዮር ጋራንግ አስታውቀዋል።

« ምንም አይደለም፣ ምክንያቱም በሙሴቬኒ መንግሥት እና በዩጋንዳ ሕዝብ መካከል ልዩነት እንዳለ ሕዝባችንን በማስተማር ላይ ነን። እና በሁለቱ ሀገሮች ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር ወይም የሙሴቬኒ የሚመሩዋቸው መንግሥታት በሚወስዱዋቸው ውሳኔዎች እንዲበላሽ አንፈልግም። »

እንደሚታወሰው፣ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ በታንዛንያ በተገናኙበት ጊዜ፣ እስከ መጋቢት ወር ድረስ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመሥረት ተስማምተው ነበር።

ግን ባለፉት ቀናት በሀገሪቱ የተካሄደ ውጊያ ሲታይ፣ ሂደቶች ወደዚያ የሚያመሩ አይመስሉም። በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር መንግሥት አንፃር የሚዋጉት ዓማፅያን በዩኒቲ ግዛት ርዕሰ ከተማ ቤንቲዩ የሚገኙ የመንግሥት ሠፈሮችን በመደብደብ የተኩስ አቁሙን ደንብ ጥሰዋል ሲሉ የደቡብ ሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ፊሊፕ አግዌር ወቀሳ ሰንዝረዋል።

Rebellen ethnische Massaker in Südsudan
ምስል Reuters

« የመጀመሪያው ጥዝቃት በዩኒቲ ግዛት ላይ ነበር፣ ጦሩ ይህን ጥቃት መመከት ችሎዋል። ሁለተኛው ጥሰት የመንግሥት ሠፈሮችን በካባድ መሳሪያ ያጠቁበት ድርጊት ነው። »

ጥቃቱ የተሰነዘረው የተመድ ረሀብ ላሰጋቸው ከ2,5 ሚልዮን የሚበልጡ ደቡብ ሱዳናውያን 1,8 ቢልዮን ዶላር ርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ ካቀረበ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። በደቡብ ሱዳንን የሶስት ቀን ጉብኝታ አድርገው ሰሞኑን የተመለሱት የተመ የአስቸኳይ ርዳታ አስተባባሪ መስሪያ ቤት ወይዘሮ ቫለሪ ኤሞስ እንዳስታወቁት፣ 14 ወራት የሆነው የርስ በርስ ጦርነት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል፣ በሕዝቡም ላይ ስቃይ አስከትሏል። በቤንቲዩ ከተማ በሚገኘው የተመድ ጣቢያ ውስጥ ብቻ 53,000 ሰዎች ከለላ አግኝተዋል፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገር ተሰደዋል።

አርያም ተክሌ

ልደት አበበ