1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዮናታን ተስፋዬ ብይን

ሐሙስ፣ ግንቦት 17 2009

የፌደራል ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት በዛሬዉ ዕለት የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞዉ የሕዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ላይ የእስራት ቅጣት በየነ።

https://p.dw.com/p/2dZyG
Yonatan Tesfaye
ምስል DW/Y.Geberegziabehr

MMT / Q&A Yonatan'S lawyer - MP3-Stereo

የቀድሞዉ የሠማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ በተያዘባቸዉ የአሸባሪነት ወንጀል ሥድስት ዓመት ከመንፈቅ እስራት ተፈረደባቸዉ።ዛሬ አዲስ አበባ ያስቻለዉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በወጣቱ ፖለቲከኛ ላይ ቅጣቱን የወሰነዉ የተከሳሽ ጠበቆችን የቅጣት ማቅለያ በከፊል ከተቀበለ በኋላ ነዉ።ዩናታን፤ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚተች ፅሑፍ በፌስቡክ በማሰራጨታቸዉ ሰበብ ከታሕሳስ 2008 ጀምሮ እንደታሰሩ ነዉ።ፖለቲከኛዉ የሽብርተኝነትን ድርጊት ለመፈፀም ማቀድ፤ መዘጋጀትና ማነሳሳት በሚል ወንጀል ተከሰዉ ሲሟገቱ ነበር። ያስወነጀላቸዉ፤ መንግሥትን በመቃወም አደባባይ ለወጣዉ ሕዝብ  ተገቢዉን መልስ ከመስጠት ይልቅ መንግሥት የኃይል እርምጃ ወስዷል ብለዉ በመፃፋቸዉ ነዉ።የዩናታን ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ ዛሬ እንዳስታወቁት ተከሳሹ የተላለፈባቸዉን የ6 ወር ከመንፈቅ የእስራት ቅጣትን ሥላልተቀበሉት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ይጠይቃሉ።
                             
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሺዋስ አሰፋ ለፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደነገሩት ዩናታን ሐሳባቸዉን ከመግለፅ ሌላ ያደረጉት የለም።ፓርቲዉ ይግባኝ እንደሚጠይቅም አቶ የሺዋስ አስታዉቀዋል። እስካለፈዉ መስከረም ድረስ ለአንድ ዓመት ያክል የኢትዮጵያ መንግሥትን በመቃወም አደባባይ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ የመንግሥት ፀጥታ ኃይላት የወሰዱት  እርምጃ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እየጠየቁ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተፈፀመዉ የሠብአዊ መብት ጥሰት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ የኢትዮጵያ መንግሥት ይፈቅድ ዘንድ ምክር ቤቱ ግፊት እንዲያደርግ  13 የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ትናንት በደብዳቤ ጠይቀዋል።

ሸዋዬ ለገሰ

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ