1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ትብብር ጉባዔ ፍፃሜ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13 2006

15 ቱ የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ትብብር ድርጅት፣ በምኅፃሩ የ«ሳዴክ» መሪዎች ያካባቢያቸውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማስፋፋት ተስማሙ። የኢንዱስትሪው ዘርፍ በ«ሳዴክ» የትብብር አጀንዳ ውስጥ ዓቢይ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ርዕሳነ ብሔራቱ ትናንት በዚምባብዌ የሁለት ቀናት ጉባያቸውን ባጠናቀቁበት ጊዜ አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/1Cx8m
Robert Mugabe
ምስል Getty Images/Afp/Jekesai Njikizana

በደቡባዊ አፍሪቃ የሚታየውን ድህነትን ለመታገል ይቻል ዘንድ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ወሳኝ ሚና ሊጫወት እንደሚችል የወቅቱ የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ትብብር ጉባዔ ሊቀ መንበር የሆኑት የዚምባብዌ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ በሞዚ ኦአ ቱንያ ከተማ ወይም በቀድሞ አጠራሩ በ«ቪክቶርያ ፎልስ» ባስተናገዱት የሁለት ቀናት ጉባዔ መዝጊያ ላይ አስታውቀዋል። የ«ሳዴክ» ስልት፣ ለኤኮኖሚያዊ ለውጥ በሚል ርዕስ የተካሄደው ጉባዔ ያካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ለዘላቂ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጥቅም ማዋል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መምከሩን ሙጋቤ አክለው አስረድተዋል።

በተለይ ባካባቢው ባለው በግዙፉ ሀብታችን በተሻለ መንገድ መጠቀም ስለምንችልበት ጉዳይ ለመምከር አጋጣሚውን አግኝተናል። ያካባቢያችን የኤኮኖሚ ሁኔታን፣ በተለይም፣ ትርፋማ እና እሴትን ማዳበር እና የአካባቢያዊ ስልታዊ ዕድገታችን አካል ማድረግ የምንችልበትን አሰራር ም መርምረናል። በዚህም መሠረት፣ የንግድ ሚንስትሮቻችን የኢንዱስትሪውን ዘርፍ እንዲያጠናክሩ እና በኢንዱስትሪያዊነት እና በነፃ ገበያ መካከል ግንኙነት እንዲፈጥሩ የቀረበውን ሀሳብ ደግፈናል። ይህን ማድረግ ከተሳነን፣ ማለትም፣ አስፈላጊውን ዕቃ ሳይቀርብ ገበያዎቻችንን በቻ ነፃ የምናደርግበት ሁኔታ የሚያስገኘው ፋይዳ አይኖርም ማለት ነው። »

Viktoria-Fälle in Sambia und Simbabwe
ምስል public domain/John Walker

የንግድ ሚንስትሮቹ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ማስፋፋት የሚቻልበትን መርሃግብር የሚነድፍ አንድ ኮሚቴ እንዲያቋቁምም ድርጅቱ ኃላፊነቱን ሰጥቶዋል። ሙጋቤ እንዳስረዱት፣ ይህ ዓይነቱ መርሃግብር አባል ሀገራት በዓለም አቀፍ አጋሮች ላይ ጥገኛ የሆኑበትን ድርጊት ለመቀነስ የሚረዳ ሲሆን፣ መርሃግብሩን የሚደግፍ ያካባቢ ፈንድ ለማቋቋም አበረታቺ ጥረት ተጀምሮዋል። የደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት ለኤኮኖሚያቸው ግዙፍ ጥቅም ለማስገኘት ከፈለጉ በጥሬ ምርት ፈንታ ያለቅ ውጤት በንግድ ወደ ውጭ እንዲልኩም ሙጋቤ አሳስበዋል።

አባል ሀገራት በምዕራብ አፍሪቃ ቢያንስ 1,145 ሰዎችን ሕይወት ያጠፋው የኤቦላ በሽታ ስርጭት እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጉባዔው አስጠንቅቋል።

Hifikepunye Lucas Pohamba
ምስል AP

ጉባዔው በተካሄደበት ጊዜ ፣ የዚምባብዌ ፖሊስ ፕሬዚደንት ሙጋቤ ሁለት ሚልዮን የስራ ቦታ ለመፍጠር በምርጫ ዘመቻ ጊዜ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ በመጠየቅ በመዲናይቱ ሀራሬ አደባባይ የወጡትን ከ700 የሚበልጡ የዚምባብዌ ዜጎችን በኃይሉ ተግባር መበተኑ እና የመብት ተሟጋቾችን እና አንድ ጋዜጠኛ ማሰሩ ተሰምቶዋል። «ሳዴክ» ጉባዔ ስለዴሞክራሲ፣ በአባል ሀገራቱ ውስጥ ይፈፀማል ስላሉት የሰብዓዊ መብት ረገጣ እና ስለሚታየው የእኩልነት መጓደል እንዲወያዩ በሀራሬ አደባባይ የወጡ የሲቪክ ድርጅቶች ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ሰሚ ሳያገኙ ነበር የቀረው። ሙጋቤ እነዚህን ጉዳዮች በመክፈቻው እና በመዝጊያው ንግግራቸው አላነሱም። ከነዚሁ ጉዳይ ጋ ተቀራራቢ ዲስኩር ያሰሙት ብቸኛው መሪ የናሚቢያ ፕሬዚደንት ሂፊኬፑንየ ፖሀምባ እንደነበሩ ቢነገርም፣ የሲቪክ ድርጅቶች አሳሳቢ ላሏቸው ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጡ ነበር ያለፉት።

« በአካባቢያችን ዴሞክራሲን እና መልከም አስተዳደርን ማጠናከራችንን ቀጥለናል። የሥልጣኑን ካባ ለቀጣዩ የናሚቢያ ፕሬዚደንት በማስረክብበት በአሁኑ ጊዜ፣ የ«ሳዴክ» አባል ሀገራት መሪዎችን እና ዜጎችን የማሳስበው ካሁን በፊት የነበሩ መሪዎች አጠቃላይ የሕዝቦቻችንን ውኅደት፣ አንድነት እና መጣጣምን እውን ለማድረግ የጀመሩትን ፈለግ እንዲከተሉ ነው። »

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ