1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ድርቁና ርዳታ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 21 2003

የድርቅና ረሐቡ ችግር በምግብ ርዳታ ብቻ የሚወገድ ባለመሆኑ ገበሬዉ እራሱን ለዘላቂዉ የሚችልበት ሥልት ሊቀየስ ይገባል።

https://p.dw.com/p/RcqC

ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረሐብ የተጋለጠዉ ሕዝብ የረጅም ጊዜ እርዳታ እንደሚያስፈልገዉ የኢትዮጵያና የጀርመን ቀይ መስቀል ማሕበራት አስታወቁ።ሁለቱ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ በተለይም ባሌ አካባቢ ለረሐብ የተጋለጠዉን ሕዝብ በጋራ እየረዱ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል።ይሁንና የሁለቱ ተቋማት ባለሥልጣናት እንዳሉት ለረሐብ የተጋለጠዉ ሕዝብ እራሱን መመገብ እስኪችል ድረስ የአስቸኳይና የልማት ርዳታ ሊደረግለት ይገባል።ነጋሽ መሐመድ የሁለቱን ማሕበራት ባለሥልጣናት በስልክ አነጋግሯቸዋል።


ድርቅ ረሐቡ ዳግም ማየሉ እንደተሰማ ወደ ምሥራቅ አፍሪቃ የተጓዘዉ የጀርመን ቀይ መስቀል ማሕበርየመልዕክተኞች ጓድ መሪ ክርስቶፍ ሙለር እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የመስክ ባለሙያ አቶ ካሳሁን ሐብተማሪያም ዛሬ ጠዋት ጎባ ነበሩ።ጎባ ከመድረሳቸዉ በፊት ከኢትዮጵያ ሞያሌ እስከ ባሌ ተራሮች ድረስ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል።

ገበሬዉ ሙለር እንደሚሉት ክፉኛ ተጎድቷል።

«በድርቁ ምክንያት አነስተኛ ገበሬዎች በጣም ተጎድተዋል።ይሕ ማለት አብዛኞቹ ከብቶቻቸዉ አልቀዉባቸዋል።ዝናብ በመዘግየቱ ምክንያትም ሠብል ስቷል።በዚሕም ምክንያት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርዳታ ማግኘት አለባቸዉ።እርግጥ ነዉ አሁን ዝናብ መጣል በመጀመሩ ሁኔታዉ ቀስ በቀስ መሻሻሉ አይቀርም።ይሁንና ተጎጂዎቹ እራሳቸዉን እስኪችሉ ድረስ ለረጅም ጊዜ ሰብአዊ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል።»በመላዉ ኢትጵያ ለረሐብ የተጋለጠዉ ሕዝብ ቁጥር ከ አራት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺሕ ይበልጣል።ግማሽ ያሕሉ ረሐብተኛ ሙለር እንደሚሉት ለወትሮዉ ለምነቱ የተመሠከረለት የኦሮሚያ መስተዳድ ነዋሪ ነዉ።

«እዚሕ (ጎባ) አካባቢ ወደ ሰወስት መቶ ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ለረሐብ ተጋልጠዋል።በመላዉ ኦሮሚያ አሰቸኳይ ርዳታ የሚያስፈልገዉ ሕዝብ ሁለት ሚሊዮን ግድም ነዉ።»

ከሙለር ጋር የተጓዙት አቶ ካሳሁን ሐብተማርያም አከሉበት።የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት መምሪያ ሐላፊ አቶ አፈወርቅ ተሾመ እንደሚሉት ደግሞ በመላዉ ኢትዮጵያ ለረሐብ የተጋለጠዉ ሕዝብ በጣም ቢያጥር እስከ ታሕሳስ ድረስ የርዳታ ጥገኛ ነዉ።በተራራማዎቹ የባሌ ቀበሌዎች ለሚኖረዉ ችግረኛ ሕዝብ አሁንም ርዳታ እየተከፋፈለ ነዉ።ሙለር።

«ቀይ መስቀል፥ ኦክስፋምና ሌሎችም ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች በተለይ ለሕፃናትና ለናቶች የርዳታ ምግብ እያከፋፈሉ ነዉ።»
ግን አቶ ካሳሁን እንደሚሉት ሁሉም እርዳታ አያገኝም።ምክንያት?ያም ሆኖ የጀርመን ቀይ መስቀል ማሕበር ከኢትዮጵያ አቻዉና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተጨማሪ እና የረጅም ጊዜ ርዳታ ለሚያስፈልገዉ የባሌ ሕዝብ ሁለት ዓይነት ርዳታ ለመስጠት አቅዷል።የአስችኳይ ጊዜና ምጣኔ ሐብታዊ ርዳታ።

«የጀርመን ቀይ መስቀል ማሕበር ከአዉሮጳ ሕብረት ፋርም ግሩፕ በሚደረግለት ድጋፍ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ አዝርዕት ያከፋፍላል።የመጠጥ ዉሐ ለማዳረስ ይጥራል።ገበሬዎች ምርታቸዉን የሚያከማቹና የሚሸጡበት አነስተኛ መጋዘንና መደብር ይሠራል።ይመክራልም።ይሕ ማለት እኛ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር አስቸኳይ ርዳታም፥ የልማት ርዳታም እንሰጣለን ማለት ነዉ።»

ሙለር እንደሚሉት የድርቅና ረሐቡ ችግር በምግብ ርዳታ ብቻ የሚወገድ ባለመሆኑ ገበሬዉ እራሱን ለዘላቂዉ የሚችልበት ሥልት ሊቀየስ ይገባል።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ