1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግብፅ ዕቅድ በኢትዮጵያ ዘንድ እንደማይወደድ ታዛቢዎች ይገልጻሉ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 12 2009

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አል-ሲሲ ባለፈው ሳምንት ወደ ዩጋንዳ ጎራ ብለው ከኡጋንዳው አቻቸው ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር በተለያዩ ጉዳዩች ላይ መክረዋል፡፡ በደቡብ ሱዳን እንዲሰፍር ለተቃደው የአካባቢው ሀገራት የጥበቃ ኃይል ግብጽ ጦር ብታዘምት እንደሚደግፉ ሙሴቪኒ አሳውቀዋል፡፡ ታዛቢዎች እንደሚሉት የግብፅ ዕቅድ በኢትዮጵያ ዘንድ ብዙም አይወደድም።

https://p.dw.com/p/2UgAs
Berlin Pressekonferenz Merkel al-Sisi
ምስል picture-alliance/dpa/von Jutrczenka

Why Egypt want to send troops to South Sudan -FINAL - MP3-Stereo

የደቡብ ሱዳን የእስር በእርስ ጦርነት ዙሪያ ገባውን ያሳስብ፤ያሻኩት ይዟል፡፡ የአካባቢው ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ  «መፍትሄ» የሚሉትን ከማፈላለግ አልቦዘኑም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በሀገሪቱ እየተፈጸሙ ናቸው የሚባሉት አሰቃቂ ግድያዎች የሩዋንዳ አይነት የዘር ፍጅት ሊያስከትል እንደሚችል  ከማስጠንቀቅ  ቸል አላሉም፡፡ በሀገሪቱ የተሰማራውን የሰላም አስከባሪ ኃይል ይበልጥ ያጠናክራል የተባለለት ከአካባቢው ሀገራት የተውጣጣ የጥበቃ ኃይል ዕጣ ፈንታ ገና አለመለየቱ ደግሞ ሌላ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል፡፡ 

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት 4000 የአካባቢዉ ሐገራት ኃይል ደቡብ ሱዳን እንዲሰፍር ውሳኔ ያሳለፈው ባለፈው ነሐሴ ነበር፡፡ ይህ  ኃይል በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ እና አካባቢዋ ያለውን ጸጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ተቋማት ቅጽር ግቢ የተጠለሉ ሰላማዊ ዜጎችን፣ የጁባን ዓየር ማረፊያ እና ሌሎችም ቁልፍ ተቋማት የመጠበቅ ተግባርም ያከናውናል፡፡ 

ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ኬንያ ለዚህ ኃይል ወታደሮቻቸውን ለማዋጣት ፍላጎታቸውን ወዲያውኑ ቢገልጹም እስካሁን አንድም አባላቸው ወደ ቦታው አልተንቀሳቀሰም፡፡ ግብጽ በበኩሏ ዘግየት ብላ ለጥበቃ ኃይሉ ወታደር የማዋጣት ፍላጎቷን አስታዉቃለች፡፡ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የጥበቃ ኃይሉን ለመላክ ሲወሰን ድምጽ ተዐቅቦ ካደረጉ አራት ሀገራት መካከል ግብጽ አንዷ እንደነበረች የሚያስታውሱ “አሁን ምን ተገኘ?” ማለታቸው አልቀረም፡፡ 

 የፖለቲካ ተንታኝ ዶ/ር ጆን ያንግ ግን ጉዳዩ የደቡብ ሱዳን ሳይሆን የኢትዮጵያ ነው ይላሉ፡፡

Yoweri Museveni
ምስል picture alliance/empics

“ግብጽ ከዚህ ቀደም በእዚህ የቀጠናው ጥበቃ ኃይል ላይ ለመሳተፍ በተባበሩት መንግስታት [ስብሰባ] ጊዜ ሞክራለች፡፡ በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ በጉዳዩ በጣም ተበሳጭታ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግብጽ በእርግጠኝነት የሩቅ አጋር ሳትሆን በደቡብ ሱዳን ሁኔታ ላይ ሚና እንዲኖራት እና ወታደሮቿ በቦታው እንዲኖሩ የምትሻ ነች፡፡ ነገር ግን ይህ ኢትዮጵያን በጣም በጣም የሚያበሳጭ ነው፡፡ ይህ የሚሆን ከሆነ ደግሞ በደቡብ ሱዳን ዕውቅና የሚደረግ ነው የሚሆነው፡፡ ያ ደግሞ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ትልቅ ውጥረት የሚፈጥር ነው» ይላሉ፡፡

እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የግብጹ ፕሬዝዳንት በኡጋንዳ ባደረጉት የአንድ ቀን ጉብኝት ከዩጋንዳ አቻቸዉ  ሞቅ ያለ ድጋፍ ተችሯቸዋል፡፡ ሙሴቬኒ የግብጽን ውሳኔ የደገፉበትን ምክንያት “ግብጽ ከደቡብ ሱዳን ጋር ድንበር የምትጋራ ባለመሆኗ ለእንድ ወገን ታዳላለች የሚለው ስሞታ አይቀርብባትም” በማለት ነበር-የገለፁት፡፡ ሙሴቬኒ የሳልቫ ኪር ጠንካራ ደጋፊ ናቸዉ።

የፖለቲካ ተንታኙ ፕሬዝዳንት ሙሲቬኒ የግብጽን ዕቅድ የደገፉት ይሳካል ብለው አምነው ሳይሆን “የፖለቲካ ጨዋታ” ለመጫወት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡

“እየተመለከትን ያለነው ሰፋ ያለ ጨዋታ ነው፡፡ ጨዋታው ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ በደቡብ ሱዳን ሰፋ ሲልም በአፍሪካ ቀንድ ያላቸውን የየራሳቸውን የበላይነት ማጠናከራቸው ነው፡፡ ሙሲቬኒ በግልጽ እንዳሳየው ግብፆችን በማምጣት በሆነ መልኩ ኢትዮጵያውያንን ለመቆጣጠር ነው፡፡ በድጋሚ ያ ሚሆን አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን እዚህ እየተጫወቱት ያለውን ጨዋታ መመልከት ትችላለህ» ይላሉ፡፡

 በደቡብ ሱዳን  ከተሰማሩት 16‚000 ሰላም አስከባሪዎች በተጨማሪ ይሰማራል የተባለው የጥበቃ ኃይል መጓተት  በሀገሪቱ ያለውን ደም መፋሰስ  ያባብሰዋል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ የጥበቃ ኃይሉን ለማሰማራት በሚመለከታቸው ዘንድ ሁሉ “እግር መጎትት ይታያል” የሚሉ ፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡

ይሁንና  ከጥያቄዎቹ ሁሉ አነጋጋሪዉ «በአስር ሺህዎች የሚቆጠረው የሰላም አስከባሪ ኃይል ማድረግ ያልቻለውን አራት ሺህዉ  የአካባቢው ኃይል እንዴት አድርጎ ሰላም ያመጣዋል? የሚለዉ ነዉ። ዶክተር ጆን ያንግን  የሚያሳስባቸው ሌላም ነገር አለ።

“እኔን የሚሳስበኝ ይህ የጥበቃ ኃይል የሚሰራው መንግስትን ከጥቃት መከላከል መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የተቃዋሚዎቹ አባላት ጁባን ጥለው ወጥተዋል አሊያም በሰላመዊ ሰዎች ካምፖች ውስጥ ተጠልለዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ ሰዎች እዚያ ምንድነው የሚሰሩት? እዚያ የሚሄዱት በጁባ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ኃይሎች ጥቃት ከፈጸሙ መንግስትን ለመከላከል ነው” 
ሲሉ አወዛጋቢ የሚሉትን የራሳቸውን ግምት ይሰነዝራሉ፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ