1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ቀዉስና የለጋሾች ጉባኤ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 12 2006

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ከአራት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አስቸኳይ ሠብአዊ ርዳታ ያስፈልገዋል

https://p.dw.com/p/1C34h
Südsudan-Konferenz in Oslo
ምስል DW/L. Schadomsky

በደቡብ ሱዳኑ የርስ በርስ ጦርነት ለተጎዳዉ የሐገሪቱ ሕዝብ ርዳታ ለማሰባሰብ ያለመ ዓለም አቀፍ የለጋሽ ሐገራት ጉባኤ ኦስሎ-ኖርዌ ዉስጥ ተከፍቷል።በጉባኤዉ ላይ ከሐምሳ የሚበልጡ ለጋሽ መንግሥታት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።የጉባኤዉ አስተናጋጅ ኖርዌ ዛሬ ሥልሳ ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች።ሌሎች ሐገራትም የተለያየ መጠን ያለዉ ገንዘብ ለመስጠት ቃል እየገቡ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ከአራት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አስቸኳይ ሠብአዊ ርዳታ ያስፈልገዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፤ በዕርስ በርስ ጦርነት በምታመሰዉ ደቡብ ሱዳን ለሚኖረዉ ህዝብ ከፍተኛ እርዳታዉን እንዲለግስ የተመድ ጠየቀ። በደቡብ ሱዳን በሚልዮን የሚቆጠሩ ህፃናት፤ ሴቶችና ወንዶች፤ ለከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል ሲሉ በተመድ የሰብዓዊ ርዳታ ጉዳይ ምክትል ዋና ፀሃፊ ቫለሪ ኤሞስ ዛሬ ኖርዊ መዲና ኦስሎ ላይ በተሰየመዉ የደቡብ ሱዳን ሰብዓዊ ርዳታ አሰባሳቢ ዓለም አቀፍ የለጋሾች ጉባኤ ላይ ተናግረዋል። ኤሞስ በደቡብ ሱዳን የሚታየዉ የሰብዓዊ ጉዳይ በጣም አስደንጋጭ እደሆነም ገልፀዋል። ዛሬ በኦስሎ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የተለያዩ አገሮች ለደቡብ ሱዳን ርዳታ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል ። የጀርመን ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰብዓዊ ጉዳዮች ተጠሪ ኢና ሌፔል ጀርመን ለደቡብ ሱዳን ስለምታቀርበዉ ርዳታ ሲገልጹ፣
«ልክ እንደሌላ ጊዜ ሁሉ ጀርመን በደቡብ ሱዳን የተከሰተዉ ሰብዓዊ ጉዳይ ቀዉስ አሳስቦአታል። በደቡብ ሱዳን ያሉት ተቀናቃኝ ኃይሎች ሁሉ ፤ ስልታዊ ዉይይት እንዲያካሂዱ፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እና የሰብዓዊ ጉዳይ ሕግጋትን እንዲያከብሩ፣ እንዲሁም፣ በአፋጣኝ ዘላቂ የፖለቲካዊ መፍትሄ ላይ እንዲደርሱ እንጠይቃለን። ሁኔታው ይህን የመሰለበትን ምክንያት በማድረግ የሰብዓዊ ርዳታችንን በስድስት ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን። ይህ ዛሬ የተገባዉ ቃል በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ባፋጣኝ ተግባራዊ ይሆናል። በዚህም ጀርመን እአአ በ 2014 ዓም የምትሰጠውን የሰብዓዊ ርዳታ ድርሻ ወደ 12 ሚሊዮን ዩሮ ያደርሰዋል።»
በጉባኤዉ ላይ የአዉሮጳዉ ህብረት ኮሚሽን ዓለም አቀፍ ትብብር እና የሰብዓዊ ርዳታ አስተባባሪ ኮሚሽነር ክርስቲና ጌዮርጌቫ በበኩላቸዉ ከደቡብ ሱዳኑ ቀዉስ ባሻገር በጎረቤት ሃገራት የሚታየዉንም ቀዉስ ጠቅሰዋል ።
« የደቡብ ሱዳን ጎረቤት የሆኑት ቀዉስ ያመሰቃቀላት የመካከለኛዉ አፍሪቃ ሬፐብሊክ ፤ ቦኮ ሀራም የሚንቀሳቀስባት ናይጀርያ፣ እንዲሁም፣ በራሳቸው ችግር በተወጠሩት የሳህል አካባቢ ሀገራት ፣ በማሊ የሚታየዉ ቀዉስም ገና አላበቃም፣ ሶማልያም እጅግ ብዙ ስደተኞች የሚፈልቁባቸዉ ሀገሮች ናቸዉ። እና በዚህ የችግር መቀነት ውስጥ የምትገኘው ደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ከማንኛዉ ቀዉስ የከፋ ነዉ፤ ቀዉሱ ደግሞ ድንበር እንደሚሻገር እናውቃለን። እናም የኔ መልዕክት ለሕዝቧ ስንል በመጀመርያ ደቡብ ሱዳንን ህዝብን መርዳት ያስፈልገናል። በዚሁ የችግር መቀነት ውስጥ የሚታየው የፀጥታ ሁኔታ ሊያሳስበንም ይገባል።» በጉባኤዉ ላይ እስካሁን 500 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ እንደሚሰጥ ቃል ተገብቷል። በደቡብ ሱዳን የሚታየዉን ሰብዓዊ ቀዉስ እጅግ ያከበደዉ፤ በአካባቢዉ ላይ የተከሰተዉ የኮሌራ ወረርሽኝ እንደሆነም ተመልክቶአል። የደቡብ የሱዳን ሰብዓዊ ርዳታ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ያዘጋጀችው ኖርዌይ ለደቡብ ሱዳን የ 81 ሚሊዮን ዶላር ርዳታ ለመስጠት ቃል ገብታለች።
በተያያዘ ዜና የጀርመን መንግሥት ዜጎቹን ከደቡብ ሱዳን ማዉጣት መጀመሩ ተነግሮአል። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር መንግሥት በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ዜጎቹን ለማዉጣት አዉሮፕላን ወደ ጁባ መላኩን እና ዜጎቹን የማዉጣቱ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። የስቶክሆልሙ ወኪላችን ቴዎድሮስ ምሕረቱ የጉባኤዉን አዘጋጆች አነጋግሮ የሚከተለዉን ዘገባ ልኮልናል።

ቴዎድሮስ ምሕረቱ
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ

Oslo Geberkonferenz für Südsudan Brende und Amos 20.05.2014
ምስል picture-alliance/dpa
Oslo Geberkonferenz für Südsudan Brende und Benjamin20.05.2014
ምስል picture-alliance/dpa
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ