1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች አዲስ ስምምነት

ሐሙስ፣ ጥር 14 2007

ጦርነት የገጠሙት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ትናንት አሩሻ ታንዛኒያ ላይ የእርስ በርስ ጦርነቱን ሊያስቆም የሚችል አዲስ ስምምነት መፈራረማቸዉ ተሰማ።

https://p.dw.com/p/1EPE4
Salva Kiir und Riek Machar unterzeichnen Abkommen
ምስል AFP/Getty Images

ስልጣን ላይ ሚገኙት ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸዉ የአማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቻር የተፈራረሙት ዉል የተከፋፈለዉን ገዢዉን የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አዉጭ ንቅናቄ (SPLM)ን ወደአንድነት ሊመስል ይችላል ተብሏል። በአዲሲቷ አፍሪቃዊት ሀገር በአንጋፋ ፖለቲከኞቿ መካከል አለመግባባቱ ንሮ ወደጦርነት ከተሸጋገረ ወዲህ ሁለቱ ወገኖች በተግባር ያልተገለፁ ተደጋጋሚ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።

በደቡብ ሱዳን አንጋፋ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረዉ አለመግባባት ነፍጥ ሲያማዝዛቸዉ ለዓመታት ለደቡቡ የሱዳን ሕዝብ ነፃነት ሲታገል እንደቆየ የሚነገርለት የአዲሲቱን ሀገር ገዢ ፓርቲ SPLMን በጎሳ አቧድኖ ነዉ የከፋፈለዉ። ይህም አንዱ በሌላኛዉ ጎሳ ላይ የአፀፋ ጥቃትና የጅምላ ጭፍጨፋ እስከመፈፀም አዳርሶ በሺና አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ነፍስ ሲያጠፋ መቶ ሺዎችን አሰድዶ በበርካቶች ላይ የረሃብ አደጋ እንዲያንዣብብ አድርጓል። ትናንት በታንዛኒያ መሪዎች ሸምጋይነት አሩሻ ከተማ በፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና በአማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቻር መካከል ሁለቱ ተፋላሚዎች የፈረሙት ስምምነት የተከፋፈለዉን ገዢዉን ፓርቲ ወደአንድነት ሊመልሰዉ እንደሚችል ነዉ በሸምጋዮቹ የተነገረዉ። የዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት የሪፖርት ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን ደርሶ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ አንጃዎች የሚያሳዩት ባህሪ ካልተለወጠ የስምምነቱ ዘላቂነት አጠራጣሪ እንደሆነ ያመለክታሉ።

Salva Kiir Südsudan Abkommen
ምስል picture-alliance/dpa/Dhil

የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ምክትላቸዉ የነበሩትን ሪየክ ማቻርን ከስልጣን ሊገለብጡኝ አሲረዋል ሲሉ ከከሰሱበት ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2013ዓ,ም ታኅሳስ ወር ጀምሮ ወደጦርነት ከገቡ ወዲህ በተካሄዱ የሽምግልና መድረኮች የተፈረሙት አምስት የተኩስ አቁም ስምምነቶች አንዳቸዉም በተግባር አልተገለፁም። ከምን በላይ የራሳቸዉን የስልጣን ሕልዉና በማስቀደም የሚወቀሱት የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች አዲስ አበባ ላይ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት IGAD አማካኝነት በተካሄዱ ድርድሮች መስመር የያዙ ጉዳዮች ሕይወት እንዳይኖራቸዉ ቢያደርጉም የትናንቱ ስምምነታቸዉ እንዲሁ ከንቱ ተደርጎ መታየት አይኖርበትምም ይላሉ ዶክተር ሰሎሞን፤

Salva Kiir mit Jakaya Kikwete und Riek Machar
አደራዳሪዉ የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ጃካያ ኪክዌቴ እና ሳልቫ ኪርና ሪየክ ማቻር ከስምምነቱ በኋላምስል AFP/Getty Images

ዘገባዎች እንደሚሉት የአሩሻዉ የደቡብ ሱዳን የሰላም ዉይይትና ስምምነት አዲስ አበባ ላይ በያዝነዉ ወር ማለቂያ ላይ ከሚካሄደዉ የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ጎን ለጎን በIGAD አማካኝነት ለሚኖረዉ የሁለቱ ወገኖች ድርድር ተጓዳኝ ነዉ። አደራዳሪዎቹ የታንዛኒያ ባለስልጣናትም ተቀናቃኞቹን ያደራደሩት SPLMን የከፈለዉን ልዩነት ለማስታረቅ እንጂ የተኩስ ማቆሙና መሰሉ ድርድር አዲስ አበባ ላይ በኢጋድ እንደሚከናወን አመልክተዋል። ዶክተር ሰሎሞን በኢጋዱ ድርድር ወቅት ደም የተቃቡት ፖለቲከኞች በሽግግር መንግሥቱ አብረዉ ለመሥራት የሚወያዩበት አጋጣሚ ስለሆነ በደቡብ ሱዳን ለቀጠለዉ የእርስ በርስ ጦርነት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ