1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ንግግር በአዲስ አበባ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 24 2006

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ተደራዳሪዎች ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የሰላም ንግግር ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል ። አደራዳሪዎቹና ተደራዳሪዎቹ ግን ድርድር የሚጀምሩበትን ትክክለኛ ቀን እስካሁን በይፋ አላሳወቁም ።

https://p.dw.com/p/1AkYW
ምስል Reuters

የሰላም ንግግሩ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው የተኩስ አቁም እንደሚሆን ይጠበቃል ። በንግግሩ የተኩስ አቁም ተግባራዊ መሆኑን መቆጣጠሪያ መንገድም ይቀይሳል የሚል ተስፋ አለ ። ከሁለት ሳምንት በፊት የተቀሰቀሰው የደቡብ ሱዳን ውጊያ ዛሬም እንደቀጠለ ነው ። ውጊያው የመቆሙ ተስፋ በማይታይበት በዛሬው እለት ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በተስማሙት መሠረት በወቅቱ የአፍሪቃ ህብረትና የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን በምህፃሩ IGAD ሊቀመንበር በሆነችው በኢትዮጵያ ሸምጋይነት አዲስ አበባ ውስጥ የሰላም ንግግር ይጀምራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው ። ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ የሚገኘው የዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ሃላፊ ዶክተር ያኪ ሲልየር በሽምግልናው የኢትዮጵያ ሚና ምን ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።

Südsudan Kämpfe 28.12.2013
ምስል Reuters

« ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ህብረትና የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት በእንግሊዘኛው ምህፃር IGAD ሊቀ መንበር ናት ። በርግጥ አዲስ አበባ የአፍሪቃ ህብረትም መቀመጫ ነው ። አሁን የአፍሪቃ ህብረት ፣ IGAD ድርድሩን እንዲመራ የጠየቀ ይመስላል ። የኢትዮጵያ ሚና ሁለቱ ወገኖች ሊነጋገሩ የሚችሉበትን ገለልተኛ ስፍራ መስጠት ነው ። »

ከሁለት ሳምንት በላይ ባስቆጠረው በደቡብ ሱዳኑ ውጊያ ከ 1 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ብዙዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል ። የውጭ ዜጎችን ጨምሮ ሃብት ንብረታቸውን ተዘርፈው የተሰደዱም በርካታ ናቸው ። የሃገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴም ተስተጓጉሏል ። ይህን ሁሉ ወደ ነበረበት መመለሱ ቀላል ይሆናል ተብሎ አይታሰብም ። የሰላም ንግግሩ የዚህ አንድ ተስፋ ሊሆን እንደሚችል ግን ይገመታል ። በዚህ የሰላም ሰላም ድርድርም ዶክተር ያኪ ሲልየ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ዋነኛው ጉዳይ የተኩስ አቁም ሊሆን ይችላል ይላሉ ።

Südsudan Militär Soldaten ARCHIVBILD 2012
ምስል Getty Images

« መጀመሪያ የሚነጋገሩበት ጉዳይ የተኩስ አቁም እንዲፀና ማድረግ ና ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆኑን የሚቆጣጠሩበት መንገድ ላይ የሚሆን ይመስለኛል ። አሁን በምንነጋገርበት ሰዓት ውጊያው አልቆመም ። ቅድሚያ የሚሰጠው ውጊያውን ማስቆምና ከዚያ በኋላ የተኩስ አቁሙን መከበር መከታተል የሚቻልበትን መንገድና ስርዓት መዘርጋት ነው የሚሆነው ።»

ምንም እንኳን የተኩስ አቁም ዋነኛው ትኩረት ሊሰጠው የሚችል ጉዳይ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ግን ማጠያየቁ አይቀርም ። ሲልየ እንደሚሉት ግን ደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ኃይል በመጠናከሩ ለዚህ እገዛ ያደርጋል የሚል ትልቅ ተስፋ አለ ።

Südsudan Flüchtlinge Flüchtlingslager Juba
ምስል picture-alliance/dpa

«ቁጥራቸው በእጥፍ ጨምሮ ወደ 12500 እንዲያድግ የተወሰነላቸው የተባበሩት መንግስታት ማለትም የUNMISS ኃይሎች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ። እንደሚገባን ውጊያው አሁን በ2ት ግዛቶች ማለትም በዩኒቲና በጆንግሌ ክፍለ ግዛቶች ነው የሚካሄደው ። የጆንግሌ ክፍለ ግዛት ዋና ከተማ ቦር እንደገና በአማፅያኑ እጅ ገብታለች ። ስለዚህ ዋነኛው እንቅስቃሴ የሚደረገው በዚሁ አካባቢ መሆኑን መገመት ይቻላል ። እንደ እድል ሆኖ ዓለም ዓቀፉ ማህብረሰብ በደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ተግባራዊ መሆኑን በመከታተል ሊያግዝ የሚችል የተባበሩት መንግሥታት ኃይል UNMISS አለው ።»

የሰላም ንግግር ይጀመራል በተባለበት በዛሬው እለት ከትናንት በስተያ ቦር የተባለችውን የጆንግሌ ክፍለ ግዛት ዋና ከተማ መልሰው የያዙት አማፅያን ወደ ደቡብ በመግፋት ላይ ሲሆኑ የመንግሥት ወታደሮች ደግሞ ወደ ቦር እየገሰገሱ ነው ። ዶክተር ስሊየ እንደሚሉት የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች አዲስ አበባ መግባታቸው ቢነገርም የልዑካን ቡድኑ ይዘት ግልፅ አይደለም ። ቀጥተኛ ድርድር ከመጀመሩ በፊትም አንድ ሁለት ቀን ሊወስድ ይችላል የሚል ግምት አላቸው

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ