1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ስምምነት

ሐሙስ፣ ሰኔ 5 2006

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳል ቫ ኪርና ተቀናቃኛቸው የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር በኢጋድ ሸምጋይነት ብሄራዊ የጋራ ሽግግር መንግስት ለመመስረት የደረሱበትን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ፈተናዎች ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ።

https://p.dw.com/p/1CHVh
Südsudan - Abkommen
ምስል Reuters

ሁለቱ ወገኖች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ የሽግግር መንግሥት መመስረት ሊያስቸግራቸው እንደሚችል ደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ የሚገኘው ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። በሌላ በኩል ሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ካላቆሙ ኢጋድ ማዕቀብ እንደሚጥላባቸው ማስጠንቀቁ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል ተንታኙ ጠቁመዋል። የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለማስቆም በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ ሸምጋይነት ተፋላሚዎቹ ኃይሎች ሁለት ጊዜ የተኩስ ቀቁም ስምምነት ቢፈራረሙም ተግባራዊ አልሆኑም። ሁለቱ ወገኖች ከትናንት በስተያ ማክሰኞ አሁንም በኢጋድ ሸምጋይነት 6 ወራት የዘለቀውን ግጭት ያስቆማል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ኢጋድ አስታውቋል። በዚሁ መሠረት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳል ኪርና ተቀናቃኛቸው የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር 60 ቀናት ውስጥ ብሄራዊ የአንድነት የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ተስማምተዋል። ብዙዎች ካለፉት ጊዜያት ልምድ በመነሳት የስምምነቱን ተግባራዊነት ይጠራጠራሉ። ደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያ የሚገኘው ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ ኢጋድ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ግፊት ማድረጉ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው ይላሉ። ሆኖም በርሳቸው አስተያየት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ሁለቱ ወገኖች የሚጠብቋቸውን ፈተናዎች ማለፍ ይኖርባቸዋል።

Südsudan Friedensverhandlung in Addis Abeba
ምስል DW

«አንደኛው በሁለቱ ወገኖች ዙሪያ የሚገኙት አሰቸጋሪ ጉዳዮች ናቸው። ሪክ ማቻር በሥራቸው ያሉትን የተለያዩ አንጃዎች እንደማይቆጣጠሩ አሁን ግልፅ ሆኗል። ፕሬዝዳንት ኪርም በርሳቸው ካምፕ ውስጥ የተለያየ ፍላጎት ያላቸውን ቡድኖች የማሰባሰብ ችግር አለባቸው። እንደሚመስለኝ ዋነኛው ፈተና የሚመነጨው በአዲስ አበባ ቃል የገቡትን የፖለቲካ ስምምነት መተግበሩና በፖለቲካው ግንባርም የተለያዩ ወገኖችን ማሳተፉ ነው። ምክንያቱም የስምምነቱ ሂደት ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆን ይጠይቃልና። ፈታኙ ጉዳይ ይህን ሁሉ 2 ወር ወይም 60 ቀናት ማሳካቱ ነው።»

እንደ አሳሞዋ ሁለቱ ወገኖች የአሁኑ ስምምነት ላይ ለመድረስ እስካሁን የዘገዩት በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው በመካከላቸው ከፍተኛ አለመተማመን በመኖሩ በጠላትነት ስሜት መተያየታቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ የወታደሮቻቸውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አለመቻላቸው ነው። በኢጋድ ጫና ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የሚመሠርቱት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ይዘት ምን ሊሆን እንደሚችል ለተጠየቁት ሲመልሱ።

«የተለቀቁት እስረኞች በአንድ በኩል አሁን ሥልጣን ላይ ያለው የፕሬዝዳንት ኪር መንግስት እና የሪክ ማቻር ቡድን በአንድ ላይ መጣመር አለባቸው። ኢጋድ ሌሎች የሀገሪቱ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላትም እዲካተቱ አበክሮ ባሳሰበው መሠረት የሲቪሉ ማህበረሰብ የተከፋፈለ ቢሆንም ከሲቪሉ ማህበረሰብም ገለልተኛ ወገኖች መካተት ይኖርባቸዋል »

Südsudan Flüchtlingslager in Bor
ምስል Reuters

ሸምጋዮች እንዳስታወቁት የደቡብ ሱዳን ተፈላሚ ኃይሎችን ለማግባባት ለተካሄዱት ንግግሮች እስካሁን የወጣው ገንዘብ 17 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው። ይህ ሁለ ገንዘብ የፈሰሰባቸው ንግግሮች መና እንዳይቀሩ ኢጋድ የሰላሙን ጥረት ለማደናቀፍ የሚወሰዱ እርምጃዎች ማዕቀቦችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል። ዘግይቶም ቢሆን ኦጋድ የሰጠው ማስጠንቀቂያ ጠቃሚ ነው ይላሉ አሳማዋ።

«አካባቢያዊ ማዕቀብ ከዓለም ዓቀፍ ማዕቀብ በላይ ጉዳት ያደርሳል። ምክንያቱም ሁለቱን መሪዎች ብንመለከት ሪክ ማቻርና ሳልባ ኪር በርካታ የኤኮኖሚ ፍላጎቶች አሏቸው ከአካባቢው ሃገራት ጋር የጠበቀ ግንኑነትም አላቸው። በተለይ ከኬንያ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከዩጋንዳ እንዲሁም ከሱዳን እነዚህ ጎረቤት ሃገራት ባለፉት ዓመታት እንደ ወላጅ ተንከባክበዋቸዋል፤ በነዚህ ሃገራት ኤኮኖሚያዊ ጥቅሞች አሏቸው። ከነዚህ ሃገራት የሚሰነዘረው ማስጠንቀቂያ ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ወይም የጉዞ እገዳም ቢሆን በጣም ከባድ ጉዳት ያስከትልባቸዋል። ይህ ደግሞ ለሰላም ተገዥ እንዲሆኑ ለሚደረግባቸው ጫና መሠረት ይሆናል።»

ሂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ