1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ነፃነት 3ተኛ ዓመት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 2 2006

ደቡብ ሱዳን ሶስተኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን ዛሬ አከበረች ።ርዕሠ-ከተማ ጁባ ዉስጥ በከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ በተከበረው በዚሁ የነፃነት በዓል ላይ የደቡብ ሱዳን መሪ ሳልቫ ኪር ፣ተቀናቃናቸው የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር የሰላም ንግግሩን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል ።

https://p.dw.com/p/1CZ3a
Südsudan Feierlichkeiten Unabhängigkeit
ምስል CHARLES LOMODONG/AFP/Getty Images

ማቻርም ከአዲስ አበባ የሰላሙ ንግግር እንዲቀጥል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ። በጁባው በዓል ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ይገኙበታል ። 7 ወራት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት መፍትሄ ሳያገኝ በርካታ ዜጎችም ለረሃብ እንደተጋለጡ የተከበረው የደቡብ ሱዳን ሶስተኛ ዓመት የነፃነት በዓል የብዙ ዜጎችን ትኩረት አልሳበም ። በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ባሰሙት ንግግር አማፅያን ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል ። ሪክ ማቻር ደግሞ ከአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ለሃገሪቱ ችግር ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።ኪር በጁባው በዓል ላይ የተገኙትን የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒንም አመስግነዋል ። የደቡብ ሱዳን ሰላም አስተማማኝ እስኪሆን ድረስ የኡጋንዳ ወታደሮች ጥበቃ ለማድረግ እንደሚቆዩም ተናግረዋል ።

Südsudan Feierlichkeiten Unabhängigkeit
ምስል CHARLES LOMODONG/AFP/Getty Images

የዛሬ 3 ዓመት ዕውን ለሆነው ለደቡብ ሱዳን ነፃነት መንገዱን የጠረገው የሱዳን መንግሥትና የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ በምህፃሩ SPLM እጎአ በ2005 የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ነው ። ይሁንና መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ቻተም ሃውስ የተባለው የጥናት ተቋም ባልደረባ ጄሰን ሞስሊ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ሂደቱ ብዙ ጉዳዮችን ወደ ጎን ትቶ በማለፉ ሃገሪቱ አሁን የምትገኝበት ችግር ውስጥ ከቷታል ። በርሳቸው አስተያየት የሰላም ስምምነቱ ስያሜው የሚያመለክተውን ተግባር አለማከናወኑ ነው መሠረታዊው ችግር ።

« አጠቃላዩ የሰላም ስምምነት ስሙ እንደሚያመለክተው በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖችና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል የሚካሄዱ ግጭቶችን ሁሉ አይጨምርም ።የዳርፉር ግጭትም ሆነ በምሥራቅ ሱዳን ያለው ሁኔታ በሂደቱ አልተነሳም ።ስምምነቱም በደቡባዊ ሱዳን የሚገኙ ወገኖችን በሙሉ አላካተተም ።ከዚያ ይልቅ ያተኮረው በዋነኛውን የአማፂ ቡድን ላይ ብቻ ነው ።»

Riek Machar und Salva Kiir
ምስል Ashraf Shalzy/AFP/Getty Images

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን በማግባባት በሃገሪቱ ሰላም ለማውረድ አዲስ አበባ ውስጥ በኢጋድ ሸምጋይነት ሲካሄድ የቆየው የሰላም ንግግር እንደተቋረጠ ነው ።ሁለቱ ወገኖች ከዚህ ቀደም የተፈራረሟቸው የተኩስ አቁም ስምነቶችም አልፀኑም ። ለውጊያው አለመቆም ና ለሰላሙ ንግግር መደናቀፍ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸውን ቀጥሏል ። በበዓሉ ዋዜማ ተሰናባቿ በደቡብ ሱዳን የተመድ ተጠሪ ሂልደ ጆንሰን በሰጡት መግለጫ የሃገሪቱን ባለሥልጣናትና አማፅያንንም ራሳቸውን ብቻ የሚጠቅሙ በሙስናም የታመሙ ሲሉ ወቅሰዋቸው ነበር ። የደቡብ ሱዳን የሰላም ጥናት ተቋም ባልደረባ አብርሃም አቮሊች ደግሞ የህዝቡን አንድ አለመሆን ፖለቲከኞች ለሥልጣናቸው ማራዘሚያ እየተጠቀሙበት ነው ይላሉ ።

Südsudan Juba Essensverteilung
ምስል UNMISS/JC McIlwaine

« በመሠረቱ ህዝቡ ተለያይቷል ተከፋፍሏል ። ይህን ለመቋቋም መሞከር ያስፈልጋል ። ሁሉም መንግሥትን እንዲለይ መልሶ ለመገንባት መጣር ያስፈልጋል ። ለሁሉም ህዝብ የሚሰራ መንግሥት ቢኖር እርቀ ሰላም ቢወርድ እንኳን አንዳንዱ ህዝብ እንደደኽየ ነው የሚቀጥለው ። ፖለቲከኞች ሁል ጊዜም እነዚህን ልዩነቶች በመጠቀም ወደ ሥልጣን ለመውጣት ነው የሚሞክሩት ። »

ካለፈው ታህሳስ አንስቶ በሚካሄደው የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ወደ 10 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ህይወት እንዳለፈ ይገመታል ። የእርዳታ ድርጅቶች የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ነው ይላሉ ። ኦክስፋም የተባለው ድርጅት በቅርቡ እንዳስታወቀው ከህዝቡ አንድ ሶስተኛው ወይም ወደ 4 ሚሊዮን የሚሆነው ለአሳሳቢ የረሃብ አደጋ ተጋልጧል ።

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሃመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ