1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን የረሃብ አደጋ ስጋትና ኦክስፋም

ሐሙስ፣ ግንቦት 7 2006

ጦርነት በቀጠለባት ደቡብ ሱዳን ለረሃብ አደጋ ለተጋለጠው ህዝብ አስቸኳይ እርዳታ ለማቅረብ ለጋሽ ሃገራት ገንዘብ እንዲለግሱ ተጠየቁ ። ኦክስፋም የተባለው የብሪታኒያ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለችግሩ ከወዲሁ አፋጣኝ መልስ ካልተሰጠ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አስጠንቅቋል ።

https://p.dw.com/p/1C0q4
Flüchtlingslager Tomping in Juba Südsudan
ምስል DW/Scholz/Kriesch

የድርጅቱ የዓለም ዓቀፍ ፖሊሲ አውጭ ና የዘመቻ ክፍል ሃላፊ ማክስ ሎውሰን ለዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል በሰጡት ቃለ ምልልስ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን ረሃብ ያሰጋቸዋል ።

5 ኛ ወሩን የያዘው የደቡብ ሱዳን ግጭት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል ፤ 1.2 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችንም አፈናቅሏል ። ጦርነቱ ከገደለውና ካፈናቀለው ሌላ በርካታ ደቡብ ሱዳናውያንንም ለረሃብ ማጋለጡን በደቡብ ሱዳን እርዳታ የሚያቀብለው የኦክስፋም የዓለም ዓቀፍ ፖሊሲ አውጭ ና የዘመቻ ክፍል ሃላፊ ማክስ ሎውሰን ለዶቼቬለ ተናግረዋል ።

«ከደቡብ ሱዳን ህዝብ ከአንድ ሶስተኛው በላይ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጋው የረሃብ አደጋ ያሰጋዋል ። በመላው ሃገሪቱ እጅግ አሳሳቢ ና ከባድ የምግብ እጥረት አለ ። »

ሎውሰን እንደሚሉት በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙት ደቡብ ሱዳናውያን ይበልጥ ተጎጂዎቹ ደግሞ ህጻናት ናቸው ።

Südsudan Flüchtlingslager in Bor
ምስል Reuters

«በቅርቡ ደቡብ ሱዳን ነበርኩ በድህነት የተጠቁት እነዚህ ህዝቦች በጦርነቱ ምክንያት እህል መዝራት አልቻሉም ። ያማለት ሰብል አይሰበስቡም ። ይህ ማለት ደግሞ ልጆቻቸው በረሃብ ይጠቃሉ ማለት ነው ። ኦክስፋም እስካሁን 200 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች እርዳታ አቅርቧል ። በኛ ስሌት 200 ሺህ ህጻናት በምግብ እጥረት ምክንያት በተከሰቱ የጤና ችግሮች ሰበብ ህክምና ያስፈልጋቸዋል ።

ስለዚህ ይላሉ ሎውሰን ለጋሽና ሃብታም ሃገራት እነዚህን ሰዎች መመገብ የሚያስችል ገንዘብ መርዳት ይገባቸዋል ። ድርጅታቸው ኦክስፋም ለደቡብ ሱዳን እርዳታ ለማሰባሰብ በሚቀጥለው ሳምንት ኦስሎ ኖርዌይ ውስጥ በሚካሄደው የለጋሽ ሃገራት ጉባኤ ላይ ዓለም ዓቀፉ ማህብረሰብ እርዳታ ለመስጠት ቃል ይገባሉ ብሎ ይጠበቃል ።

«ለደቡብ ሱዳን ከተጠየቀው እርዳታ 40 ከመቶው ብቻ ነው የተገኘው ስለዚህ ለጋሽ ሃገራት ተጨማሪ 700 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰጡ እንፈልጋለን ገንዘቡ እንዳላቸው እናውቃለን ።ደቡብ ሱዳን ላይ እጅግ የከፈ ቀውስ እየመጣ መሆኑንም እናውቃለን ። እናም ይህን አስፈላጊ የሆነውን ገንዘብ በመጪው ሳምንት በኦስሎው ጉባኤ ላይ በአስቿኳይ እንዲሰጡ እንሻለን ። »

Südsudan Flüchtlingslager in Bor
ምስል Reuters

የደቡብ ሱዳኑን ግጭት ለማስቆም አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈረምም ተዋጊዎቹ ስምምነቱን ከቁብም የቆጠሩት አይመስልም ። ጦርነቱ ጋብ እንኳን አለማለቱ የእርዳታ ማቀበሉን ስራን አስቸጋሪ ቢያደርገውም ኦክስፋም ግን በደቡብ ሱዳን ግብረ ሰናይ ተግባሩን አላቋረጠም እንደ ሎውሰን ።

«ብዙዎች ሰዎች ጋ መድረስ አስቸጋሪ ነው ብለን እናስባለን ።ሆኖም አሁን ይህን እያደረግን ነው። ኦክስፋም በጣም አስቸጋሪና የተመሳቀሉ ሁኔታዎች ባለቡት ጊዜ ሁሉ ድሃው ህብረተሰብ ጋ የመድረስ ልምድ አለው ።»

ዘላቂው መፍትሄ ሰላም ቢሆንም ይላሉ ሎውሰን ረሃቡ ግን ጊዜ የሚሰጠው አይደለም ።

« በተቻለ ፍጥነት በሱዳን ሰላም መስፈን ይኖርበታል ሆኖም ረሃብ ለሚያሰጋቸው ደቡብ ሱዳናውያን እርዳታ ለመስጠት ሰላም እስኪመጣ መጠበቅ አንችልም »

ሂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ