1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ሁለተኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 5 2008

የደቡብ ሱዳን የርስ በር ጦርነት ከተጀመረ ዛሬ ሁለት ዓመት ደፈነ።ማቆምያ ባጣው በዚህ ጦርነት ሰበብ ፣ሃገሪቱ ከዛሬ አራት ዓመት ከሶስት ወር በፊት ነፃ ስትወጣ የተሰነቀው በጎ ተስፋ በሙሉ ፣ተስፋ ሆኖ የቀረ ይመስላል። መንግሥትና አማፅያን ከተደጋጋሚ ጥረትና ግፊት በኋላ ባለፈው ነሐሴ የሰላም ስምምነት ቢፈራረሙም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም ።

https://p.dw.com/p/1HNjh
Bildkombo Südsudan Riek Machar und Salva Kiir
ምስል Getty Images/Zacharias Abubeker/Ashraf Shazly/Montage

[No title]

ደቡብ ሱዳን ወደ ርስ በርስ ጦርነት የገባችው የዛሬ 2 ዓመት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳላቫ ኪር የቀድሞ ምክትላቸው ሪክ ማቻር የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ አቅደዋል ሲሉ ከወነጀሏቸው በኋላ ነበር ። ያኔ የፕሬዝዳንት ኪር ታማኞችና ከማቻር ጋር ያበሩ አማፅያን የጀመሩት ውጊያ፣ የኪር ጎሳ በሆኑት የዲንካ ህዝቦችና በማቻር ወገኖቹ ኔዌሮች መካከል እስከ ዛሬ የቀጠለውን የርስ በርስ ጦርነት አስነስቷል ።ጦርነቱን ለማስቆም በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ ሸምጋይነት መንግሥትና አማፅያን ቢያንስ 8 ጊዜ ያህል የተኩስ አቁም ና የሥልጣን መጋራት ስምምነቶች ላይ ቢደርሱም ስምመነቶቹ ተጋባራዊ አልሆኑም ። ባለፈው ነሐሴ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረትም ከብሔራዊ አንድነት የሽግግር መንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት ማቻርን ጨምሮ የአማፅያን ልዑካን እስከ ህዳር 19 2008 ዓም ድረስ ቀነ ገደብ ቢቀመጥላቸውም ይህም ተግባራዊ አልተደረገም ።ስምምነቱ ለማቻር የምክትል ፕሬዝዳንትነት ሥልጣን መስጠትን ያካትታል ።ሆኖም ማቻር በቀነ ገደቡ አልተገኙም ። የፕሬዝዳንት ኪር መንግሥት ቃል አቀባይ አተኔ ዌክ አተኔ ይህ ላለመሆኑ አማፅያንን ተጠያቂ ያደርጋሉ ።
«የሰላም ስምምነት መፈረም ብቻ በቂ አይደለም በሁለቱም ወገኖች ተግባራዊ ካልሆነ እውን ሊሆን አይችልም ።ተግባራዊነቱ ደግሞ በአንድ መስመር ብቻ የሚሄድ አይደለም ።መሆን ያለበት መንግሥትም የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄም ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል ።ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የተወሰነለት ቀን አለው ።እነዚን ቀኖች ካላከበርን በመዘግየታችን ችግር እየጋበዝን ነው ። »
ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት በዋና ከተማይቱ በጁባ ግድያና ዝርፊያው ሲጧጧፍ እዚያ ወደሚገኘው የተመድ ጦር ሰፈር ከተሸሸጉ ሰላማዊ ሰዎች አብዛኛዎቹ ፣አሁንም በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ናቸው ። ያኔ ወደ ጁባዎቹ መጠለያዎች ከመጡት ብዙዎቹ በዲንካቹዎቹ የኪር ታማኞች እንዳይገደሉ የሰጉ ኑዌሮች ነበሩ ። ከ2 ዓመት በኋላ ዛሬም በመላ ደቡብ ሱዳን በሚገኙ የተመድ መጠለያዎች ከ185 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተጠለሉ ነው ። ተፈናቃዮቹ አሁንም መጠለያ ካምፖቹን ጥለው መውጣት ይፈራሉ ።ባለፉት 2 ዓመታት የጎሳ ግጭቱ ተባብሶ 50 ሺህ ይደርሳል የተባለ ህዝብ ህይወት አጥፍቷል ፤2.2 ሚሊዮን ያህሉን ደግሞ ከቀያቸው አፈናቅሏል ። በርስ በርስ ጦርነቱ አስገድዶ መድፈር ና ህጻናቶችን በውትድርና ማሰለፍን የመሳሰሉ የመብት ጥሰቶች ደርሰዋል ። የጀርመን ዓለም ዓቀፍ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ተቋም ባልደረባ አኔተ ቬበር ለዚህ ሁሉ እልቂትና ምስቅልቅል ሁለቱንም ተዋጊ ኃይሎች ተጠያቂ ያደርጋሉ ። በርሳቸው አስተያየት ችግሩን መፍታት ያልተቻለው በሁለት ምክንያቶች ነው ።
« ከህዝቡ የተሰጣቸውን ሃላፊነትታቸውን በትክክል ባለመወጣታቸው ሁለቱንም ወገኖች ነው ተጠያቂ የማደርገው ።ሁለቱም ወገኖች ነገሮች ወደፊት እንዳይራመዱ ፣ለራሳቸው የሚጠቅመውን ለማግኘት ብቻ የሚሞክሩ ኒ,መሆናቸው ስሜት ነው ያለው ።እንደሚመስለኝ ችግሩ ላለመፈታቱ ሁለት ምክንያቶች ፣ በመካከላቸው መተማመን መጥፋቱና የፖለቲካ ፈቃደንነቱም አለመኖሩ ናቸው ። »
በሁለት ዓመቱ የደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት 7 ሚሊዮን ህዝብ በቂ ምግብ ማግኘት አልቻለም ።መንግሥት እንደሚለው ከ3 ሚሊዮን የሚልቅ ህዝብ ለረሃብ የመጋለጡ ስጋት አለ ። የእርዳታ ድርጅቶች አሁን 4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ደቡብ ሱዳናውያን የምግብ የውሐና የመጠለያ እርዳታ ሰጥተዋል ።ሆኖም የዓለም የምግብ ድርጅት በምህፃሩ የFAO የሰብዓዊ ጉዳዮች ተጠባባቂ አስተባባሪ ሱ ላውቴዝ ይህ ውቅያኖስ ላይ ጠብ ከተደረገ ውሐ ጋር የሚነፃፀር ብቻ ነው ብለዋል ።
«አሳዛኙ ነገር የሚሰጠው ድጋፍ በቂ አይደለም ። ለጋሾች በጣም ብዙ ሊባል የሚችል እርዳታ ሰጥተዋል ። 1.3 ቢሊዮን ዶላር ለግሰዋል ይህ ደግሞ ከሚያስፈልገው እርዳታ 70 በመቶው ነው ።»
FAO ለጎርጎሮሳዊው 2016 የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሰጠው ለመጠየቅ በዝግጅት ላይ ነው ። በዚሁ ዓመት ለሽግግር ጊዜ የሚሆን ሌላ የ600 ሚሊዮን ዶላር እርዳታም ይጠይቃል ።

Symbolbild - Soldaten Südsudan
ምስል Getty Images
Südsudan - Unterzeichnung des Friedensvertrags von Salva Kiir
ምስል Reuters/J. Solomun

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ