1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቅጥ ያጣው የደቡብ ሱዳን ድርድር

ሰኞ፣ ጥር 25 2007

ከአፍሪቃ ህብረት አመታዊ ጉባኤ ጎን ለጎን ሲካሄድ በነበረው የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር የስልጣን ክፍፍል አለመካተቱን የአማጺ መሪው አሳወቁ። ትናንት ተፈረመ በተባለው ስምምነት የሳልቫ ኪር የስልጣን ዘመን በሐምሌ ወር ሲጠናቀቅ የሽግግር መንግስት ለመመስረት መስማታቸው ተዘግቦ ነበር።

https://p.dw.com/p/1EUe2
Riek Machar und Salva Kiir
ምስል Ashraf Shalzy/AFP/Getty Images

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት በአዲስ አበባ መፈራረማቸው ተሰምቷል። የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቻር የተፈራረሙት ይህ ተጨማሪ ስምምነት የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ (Sudan People's Liberation Movement) እና በመንግስታዊ መዋቅሩ የተፈጠረውንና ለ15 ወራት የዘለቀውን የርስ በርስ ጦርነት ማብቂያ ሊያበጅ ይችላል የሚል አዲስ ተስፋ ተሰንቋል።ሁለቱ ወገኖች በተፈራረሙት ስምምነት የስልጣን ክፍፍልን ይጨምራል የሚል ዘገባ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘንድ ተሰምቶ የነበረ ቢሆንም የአማጺ ቡድኑ መሪ ሪየክ ማቻር ማስተባበላቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት ሱዳን ትሪቢዩንን ጠቅሶ ዘግቧል። የሪየክ ማቻር ቃል አቀባይ የሆኑትን ጄምስ ጋጀት ዳክ በስምምነቱ ምንም አይነት የመንግስት አወቃቀር እና የስልጣን ክፍፍል ጉዳዮች አልተካተተም ሲሉ መናገራቸውን የዜና አገልግሎቱ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም ዓቀፍ ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ አቤል አባተ አሁን በሁለቱ ተፈረመ በተባለው ስምምነት ሪየክ ማቻርን ምክትል ፕሬዝዳንት የማድረግ ሃሳብ የነበረ መሆኑን ይናገራሉ።

Rebellen ethnische Massaker in Südsudan
ምስል AFP/Getty Images

«መጀመሪያ ዶ/ር ሪየክ ማቻርን ጠቅላይ ሚኒስቴር አድርጎ ሌሎች ምክትል ፕሬዝዳንቶች የመሾም የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳለ ስንሰማ ነበር። አንዳንድ ይፋዊ ያልሆኑ ምንጮች እንደጠቀሱት የትናንቱ ስምምነት አንዱ አካል ዶ/ር ሪየክ ማቻርን ምክትል ፕሬዝዳንት የማድረግ ነው። ይኸ ስምምነት ምን አይነት ፋይዳ ይኖረዋል?ከሌሎቹ ስምምነቶችስ በምን ይለያል የሚለውን ለማየት ገና ይመስለኛል።»

ሙሉ በሙሉ ይፋ አልተደረገም በተባለው እና ሁለቱ ተቀናቃኞች ለአራተኛ ጊዜ በተፈራረሙት ስምምነት የሳልቫ ኪር የስልጣን ዘመን በበጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ሐምሌ 9 ቀን ሲጠናቀቅ የሽግግር መንግስት መመስረት ይኖርባቸዋል። አቶ አቤል አባተ ከስምምነቱ ይልቅ የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ቁርጠኝነት ለደቡብ ሱዳን ሰላም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራሉ።

«ትናንትና በደቡብ ሱዳን ውስጥ ያሉ አንድ ሺ አለቃ ማመጻቸውና የራሳቸውን ጦር ይዘው ጫካ መግባታቸው እየተዘገበ ይገኛል።ይህ ራሱ ስምምነቱ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ መጠናት አለበት። ትልቁ ስምምነት ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋ አለ በብዙዎች። ግን አሁንም ቁርጠኝነታቸው የሚፈተንበት ወሳኝ ምዕራፍ ይመስለኛል።»

Symbolbild - Soldaten Südsudan
ምስል Getty Images

የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ ክፍፍልን ለመፍታት የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለ ስልጣን- ኢጋድ፤የታንዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት ስኬታማ መሆን አልቻለም። ለሶስት ቦታ የተሰነጠቀው የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ የርስ በርስ ሽኩቻ በሃገሪቱ አስከፊ ረሐብ እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል። አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሃገሪቱ ለተፈጠረው የጎሳ ግጭት፤ስደት እና ሞት ሳልቫ ኪር፤ሪየክ ማቻርና ተከታዮቻቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ