1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን የስልጣን ትንንቅ

ማክሰኞ፣ ጥር 26 2007

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች ትናንት አዲስ አበባ ላይ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈራረሙ መባሉ ይታወሳል።ካሁን ቀደም ሶስት ተመሳሳይ ስምምነቶችን ፈርመው ተግባራዊ ማድረግ ያልቻሉት ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቻር ወደ ጦርነት ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ዛሬ ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1EV4o
Bildkombo Südsudan Riek Machar und Salva Kiir
ምስል Getty Images/Zacharias Abubeker/Ashraf Shazly/Montage

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለአራተኛ ጊዜ ተፈራረሙ በተባለ ማግስት በቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪየክ ማቻር የሚመራው አማጺ ቡድን ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል። በጄኔራል ዳኡ አቱርጆንግ ለሚመራው የአማጺ ጦር ቃል አቀባይ የሆኑትን አብደላ ኮት ጠቅሶ ሱዳን ትሪቢዩን እንደዘገበው የመንግስት ደጋፊ ሃይሎችን ቁልፍ ከሆኑ ከተሞች እና አካባቢዎች ለማስወጣት እና በማዕከላዊ መንግስቱ ላይ ጫና ለማሳደር በደቡብ ሱዳን ውስጥ እና ውጪ ወጣት ወታደሮች ሊመለምል አቅዷል። የሳልቫ ኪርና እና የሪየክ ማቻር ሃይሎች በ10 የጦር ግንባሮች ውጊያ ላይ መሆናቸውን እና በባህር ኤል-ጋዛል ግዛት ተጨማሪ ሶስት ግንባሮች በቅርቡ ጦርነት እንደሚጀመር አብደላ ኮት ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ላይ ለአራተኛ ጊዜ ተፈረመ በተባለው ስምምነት ሁለቱ ተቀናቃኞች ከአንድ አመት በፊት የተፈጸመውን የተኩስ አቁም ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሎ ነበር።በደቡብ ሱዳን የአንጀሊካን ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ-ጳጳስ ዳንኤል ዴንግ በሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ ውስጥ የተፈጠረው የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ አሁን የተፈረመውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ።

Südsudan Juba Essensverteilung
ምስል UNMISS/JC McIlwaine

«በደቡብ ሱዳን ያለው ጦርነት ለመላው የሃገሪቱ ዜጎችና ለሁላችንም ተቀባይነት የለውም። ይህ ስምምነት በተቻለ ፍጥነት እንዲፈረም እንፈልግ ነበር። ዋንኛው ፈተና የስልጣን ክፍፍል ጉዳይ ነው። ሌላ በግልጽ የሚታወቅ ልዩነት የላቸውም። በፓርቲው ውስጥ ማን ምን ያግኝ በሚለው ልዩነት የተፈጠረ ትንንቅ ነው። ከደቡብ ሱዳን ዜጎች ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም። »

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የቀድሞ ምክትላቸው እና የአሁኑ የአማጺ መሪ ሪየክ ማቻር ‘መፈንቅለ መንግስት ሊያደርጉ አሲረዋል’በማለት ከስልጣን ሲያባርሩ የተፈጠረው የደቡብ ሱዳን ቀውስ የጎሳ ግጭት ቀስቅሷል።የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄን ሶስት ቦታ የከፈለው መቃቃር በሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቻር መካከል የተፈጠረ ግለሰባዊ ልዩነት ይመስላል። ሁለቱ የቀድሞ የትግል አጋሮች ልዩነታቸውን አጥብበው ለሃገሪቱ ቀውስ መቋጫ ለማበጀት የተቸገሩ ይመስላል። ሊቀ-ጳጳስ ዳንኤል ዴንግ ሁለቱ መሪዎች ልዩነታቸውን እንዲፈቱ ይወተውታሉ።

«በፓርቲ ውስጥ የተፈጠረ የርስ በርስ ትግል በመሆኑ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ ሊዘገዩ አይገባም። እስካሁን የምናውቀው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ለሞት እና እንግልት የተዳረግንው በእነሱ የስልጣን ግብግብ ምክንያት መሆኑን ነው። በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው ይህ የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ መፍትሄ ካገኘ የሽግግር መንግስት በመመስረት ምርጫ ከተደረገ በኃላ ቀጣዩ ፕሬዝዳንት ማን ሊሆን እንደሚችል ይወሰናል። ከዚያ በኃላ ሌላ ልዩነት መኖሩን ደግሞ እንመለከታለን።»

ዳንኤል ዴንግም ሆኑ ደቡብ ሱዳናውያን በጉጉት የሚጠብቁት ሰላምና መረጋጋት እንዲህ በቀላሉ የሚገኝ አይመስልም። የሁለቱን ወገኖች መቃቃር በእርቅ ለመፍታት የሚደረገውን ድርድር በበላይነት የሚመራው የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለ ስልጣን- ኢጋድ እና የቀጣናው ሃገራት ባለፉት አስራ አምስት ወራት ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ መፍጠር አልቻሉም። ኢጋድ ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቻር በፊርማ የሚያጸድቋቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ካላደረጉ ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል ሲያስጠነቅቅ ከርሟል።ዳንኤል ዴንግ የኢጋድ ሃሳብ ፈጽሞ አይስማማቸውም።

Symbolbild - Soldaten Südsudan
ምስል Getty Images

«እነዚህ ሰዎች ሰላም እንዲያወርዱ ተጽዕኖ ማሳደሩ የተሻለ ነው። ማዕቀብ በባለስልጣኖች እና መሳሪያ ተሸክመው ጫካ በገቡት ላይ አንዳች ተጽዕኖ አያመጣም። እንዴት ማዕቀብ እንደሚጥሉ ሊያውቁ ይችላሉ ለእኔ ግን ማዕቀብ ሁልጊዜም የሚጎዳው ንጹሃንን ነው።»

ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ዘይት ሽያጭና ክፍፍል እና የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ከሰሜን ሱዳን ጋር የገባችበት እሰጥ አገባ መፍትሄ አላገኘም። በሃገሪቱ ባለው ሙስና ምክንያት ደቡብ ሱዳን ከዓለም አቀፍ ተቋማት የምታገኘው በቢሊየን ዶላር የሚቆጠር እርዳታ የት እንደሚገባ አይታወቅም ሲሉ የሃገሪቱን ፖለቲካ የሚታዘቡ ይተቻሉ።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ