1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ምስረታ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 16 2008

የደቡብ ሱዳን የሠላም ሥምምነት ተቆጣጣሪ ኮሚሽን ሊቀመንበር የቀድሞው የቦትስዋና ፕሬዝዳንት ፌስቱስ ሞጋዔ፤ የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት፤ በሪየክ ማቻር የሚመራው አማፂ ቡድንና በእስር ላይ የነበሩ ፖለቲከኞች ጁባ ላይ ከትመዋል።

https://p.dw.com/p/1HU58
Bildkombo Südsudan Riek Machar und Salva Kiir
ምስል Getty Images/Zacharias Abubeker/Ashraf Shazly/Montage

[No title]

እንደ ደቡብ ሱዳን የዜና አገልግሎት (SSNA) ከሆነ የቀድሞዎቹ ባላንጣ ፖለቲከኞችና አደራዳሪዎቻቸው በደቡብ ሱዳን ሊመሰረት ለታቀደው የሽግግር መንግስት ሚኒስትሮችን በመምረጥ ላይ ናቸው።

በስምምነቱ መሰረት አዲሱ የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት 30 ሚኒስትሮች የሚኖሩት ሲሆን 16ቱ አሁን በስልጣን ላይ ከሚገኘው መንግስት፤ አስሩ ደግሞ በሪየክ ማቻር ከሚመራው ቡድን የሚሾሙ ናቸው። ቀሪዎቹ ሁለት የሚኒስቴር ቦታዎች በእስር ላይ ለነበሩ ፖለቲከኞች ሁለቱ ደግሞ ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መታቀዳቸውን የዜና ምንጩ ጨምሮ ዘግቧል።

Südsudan Soldaten Rückeroberung Blue Nile Raffinerie
ምስል picture-alliance/AA

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ለሁለት ዓመት የዘለቀውን የርስ በርስ ጦርነት በማብቃት ከዚህ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለማስቻል የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እልህ አስጨራሽ ሂደት ውስጥ አልፏል። የደቡብ ሱዳን የሠላም ዉል ተቆጣጣሪና አጣሪ ቡድን ዋና ኀላፊ የሆኑት አምባሳደር ተፈራ ሻውል አሁን በደቡብ ሱዳን ለተደረሰበት የሽግግር ምስረታ የቀጣናው አገራት መሪዎችና ክፍለ አህጉራዊው ድርጅት ከፍ ያለ ሚና መጫወታቸውን ይናገራሉ።አምባሳደሩ የክፍለ አህጉራዊው ተቋም ልፋት መና እንደማይቀር ተስፋም አድርገዋል።

የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት ከብሪታኒያ፤ኖርዌይ እና ዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመሆን የሽግግር ምስረታ ሂደቱን እና የስልጣን ክፍፍሉን የመከታተል ሃላፊነት ተጥሎበታል። በስምምነቱ መሰረት የሽግግር መንግስቱ ለ ዘጠና ቀናት የሚቆይ ይሆናል። በሽግግር መንግስቱ ውስጥ በደቡብ ሱዳን ቀውስ ግጭት ውስጥ ሚና የነበራቸው መንግስት፤በሪየክ ማቻር የሚመራው አማፂ እና በእስር ላይ የከረሙት ፖለቲከኞች ሊወከሉ ይገባል። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ የሰላም ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት ዋና አደራዳሪው አምባሳደር ስዩም መስፍን ሰነዱን «አስተማማኝ» የሆነ ስምምነት ብለውት ነበር።

ለደቡብ ሱዳን ጦርነት አዲስ አይደለም። አዲሲቱ አገር እንደ አዲስ ከመፈጠሯ በፊት ከጎርጎሮሳዊው 1962 ዓ.ም. መገንጠልን የሚያቀነቅነው የአንያ ንያ ታጣቂ ቡድን ከሱዳን ጋር የለየለት ጦርነት ውስጥ ገብቶ ነበር። በጎርጎሮሳዊው 1972 ዓ.ም. የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ጃፋር አል ኑሜሪ አዲስ አበባ ላይ ከአማጽያኑ ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረም ለደቡብ ሱዳን የራስ ገዝ አስተዳደር ሲፈቅዱ የርስ በርስ ጦርነቱ ጋብ አለ።

Südsudan - Unterzeichnung des Friedensvertrags von Salva Kiir
ምስል Reuters/J. Solomun

በጎርጎሮሳዊው 1983-2005ዓ.ም. የዘለቀው ሁለተኛው የርስ በርስ ጦርነት ሲፈጠር የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ንቅናቄን የሚመሩት ጆን ጋራንግ ነበሩ። ጋራንግ አልፈው ደቡብ ሱዳንም ነጻ ወጥታ ግን አገሪቱ ከቀውስና ብጥብጥ አልጸዳችም። አሁን የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት እና ከሽግግር መንግስቱ ምስረታ በኋላ የሚካሄደው ምርጫም ተመሳሳይ ስጋት አጥልቶበታል። አምባሳደር ተፈራ ሻውል ግን የውጭ ጣልቃ ገብነት ካልኖረ በቀር ደቡብ ሱዳን ዳግመኛ ወደ ቀውስ አትገባም የሚል ክርክር ያቀርባሉ።

በአገራት ግንኙነት፤የርስ በርስ ጦርነት፣ግጭትና ጣልቃ ገብነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው የአሜሪካኑ ፎሬን አፌርስ የተሰኘ መጽሔት ለደቡብ ሱዳን ቀውስ ከፖለቲከኞቹ በተጨማሪ የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ምክንያት መሆኑን ያትታል። እንደ መፅሔቱ ከሆነ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሺር ታማኞች በደቡብ ሱዳን የመንግስት መዋቅር ውስጥ ስልጣን ማግኘታቸው ሌላው ምክንያት ነው። ባለስልጣናቱ ከሳልቫ ኪር ጎሳ ወገን ይሁኑ እንጂ የፕሬዝዳንት ኦማር አል በሺር ፓርቲ አባል እና በጦርነቱም ወቅት ለሰሜናውያኑ ያደሉ ነበር ሲል በስም ያልጠቀሳቸውን ግለሰቦች ፎሬን አፌርስ ይኮንናል።

በደቡብ ሱዳን ቀውስ እና በተደጋጋሚ ወድቆ ሲነሳ በከረመው የሰላም ድርድር የአካባቢው አገራት የጥቅም ግጭት አንዱ ምክንያት ለመሆኑ የጸጥታ ተንታኞችም ይስማማሉ። ይህ ደግሞ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት አባል አገራትን እንደሚጨምር በኢትዮጵያ ሠላምና ልማት ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበበ አይነቴ ይናገራሉ።

Konflikt im Südsudan Regierungssoldat 30.12.2013
ምስል Reuters

እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሒውማን ራይትስ ዎች ከሆነ በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን በዘራቸው አሊያም በፖለቲካ አቋማቸው ተለይተው ተገድለዋል። ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል። ሌሎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኛ ጣቢያዎች ለመጠለል ተገደዋል። ትላልቅ የሚባሉ የደቡብ ሱዳን ከተሞች፤ ለሕዝብ ሊያገለግሉ የጤና ማዕከላት፤ሆስፒታሎች እና ትምህርት ቤቶች በቀውሱ ተዘርፈዋል፤ፈራርሰዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ዘንድ የተጠያቂነት መጥፋት ለቀውሱ መባባስ ሁነኛ አስተዋጽዖ ማበርከቱን ይናገራሉ። በሁሉም ተቀናቃኝ ኃይሎች ዘንድ የሚገኙ የጦር እና ፖለቲካዊ መሪዎች በወታደሮቻቸው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፤ግድያና ወንጀሎችን ለመከላከልም ሆነ ለማስቆም ቸልተኛ ናቸው ሲሉ ይተቻሉ።

ተቀናቃኝ ኃይሎቹ ማዕቀብን ጨምሮ ከአደራዳሪዎቻቸውና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጧቸውን ቀነ-ገደቦችም ይሁን ማስጠንቀቂያዎች ችላል በማለት በተደጋጋሚ ስምምነቶችን ጥሰዋል። አምባሳደር ተፈራ ሻውል የሪየክ ማቻር ኃይል ወደ ጁባ ገብቶ ድርድር መጀመሩ ለደቡብ ሱዳን ቀውስ ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነ ያምናሉ።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ