1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ ሱዳን ጦርነት፤ ድርድርና እና የተመድ

ረቡዕ፣ ግንቦት 26 2007

የቀድሞ አማፂ ቡድናት ደቡብ ሱዳንን ከሱዳን እንዲገነጥሉ ሁለንተናዉ ድጋፍ ትሰጥ የነበረችዉ ዩናይትድ ስቴትስም የጁባ መንግሥት በብሪታኒያዊዉ ዲፕሎማት ላይ ሲዞርባቸዉ አልታገሰችም።የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ትናንት እንዳሉት የላንሰር መባረር «በደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን የሚያደርግዉን ጥረት የሚያጨናጎል ነዉ»

https://p.dw.com/p/1FbOH
ምስል DW

[No title]

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሐይላት ከዚሕ ቀደም የተፈራረሙትን የሠላም ዉል ተግባራዊ ባለማድረጋቸዉ ሲወቀሱ የፕሬዝደንት ሲልቫ ኪር መንግሥት ከሥልጣን አስወግዶ፤ አስሮ፤ ካገር አባርሯቸዉ የነበሩ የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣት ወደ ጁባ እንዲመለሱ ፈቅዷል። ጦርነቱ ለችግር የዳረገዉ ሕዝብ ተጨማሪ ርዳታ እንደሚያስፈልገዉ በሚነገርበት ወቅት፤ የሐገሪቱ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የርዳታ አስተባባሪ ማባረሩ ሌላ ዲፕሎማሲያዊ ዉዝግብ አስከትሏል። የርስ በርሱ ዉጊያ፤ የሕዝቡ ሥደት እንግልትም እንደቀጠለ ነዉ።

ባንድ አብረዉ በመዋጋት-ማዋጋታቸዉ ሠፊዋን አፍሪቃዊት ሐገር ለሁለት ለመግመሥ ልዩነት፤ ጠብ ሽኩቻቸዉን ለዓመታት ማቻቻሉ በርግጥ አልገደዳቸዉም። እንዲቻቻሉ መካሪ፤ ረዳት፤ አስተባባሪ አላጡምም።ዛሬ በርግጥ ነበር ነዉ። ጁባ ላይ አዲስ ባንዲራ በሰቀሉ ባመቱ «ነፃ አወጣንሕ» ያሉትን መከረኛ ሕዝብ ለሌላ መከራ መዳረጋቸዉ ለሩቁ ታዛቢ አይደለም ለቀድሞ አስታራቂ፤ አስታጣቂ፤ ደጋፊ ረጂዎቻቸዉም ግራ እንዳጋባ ዓመት ከመንፈቅ ደፈነ።

እሰወስት ከተገመሱት የቀድሞ ነፃ አዉጪ ቡድን መሪዎች መሐል አንዱ መንግሥት ሁለተኛዉ አማፂ ሆነዉ ሲዋጉ፤ ሲደራደሩ፤ ሰወስተኛዉ መጀመሪያ እስረኛ፤ ቀጥሎ ስደተኛ፤ አሰልሶ የተደራዳሪዎች ታዛቢ ነበር። አምስት የቀድሞ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተቧደኑበት ሰወስተኛዉ ወገን የዓመት ከመንፈቅ፤ እስራት፤ ግዞት፤ ታዛቢነትን ጨርሶ ባለፈዉ ሰኞ ጁባ ገብቷል። ቡድኑ ጁባ እንዲገባ ያግባቡ፤ የፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርን ይሁንታ ያስገኙት የአፍሪቃ መንግሥታት ባለሥልጣናት ናቸዉ።

Toby Lanzer
ምስል UN Photo/Martine Perret

አምስቱን ሰዎች አጅበዉ ጁባ ያስገቡትን የአፍሪቃ ባለሥልጣናት የመሩት የደቡብ አፍሪቃ ምክትል ፕሬዝደንት ሲሪያል ራማፎዛ «የደቡብ ሱዳን ጎበዝ ልጆች» ያሏቸዉ ፖለቲከኞች ስደት ማብቃቱ ለደቡብ ሱዳን ሠላም የመጀመሪያዉ ተጨባጭ ዉጤት ነዉ።

ጁባ፤ የቀድሞ ባለሥልጣኖችዋንና የአፍሪቃ አጃቢዎቻቸዉን ለማስተናገድ ሽር ጉድ ስትል፤ ላጭር ጊዜ የሥራ ጉብኝት ጁባን የለቀቁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣን ቶቢ ላንሰር ጁባን ዳግም እንዳይረግጡ የሐገሪቱ መንግሥት አዘዘ። ቃል አቀባይ አቴንይ ዌክ አቴንይ እንደሚሉት ላንሰር የተባረሩት ለአፋቸዉ «ለከት» በማጣታቸዉ ነዉ።

«ቶቢ ላንሰር የተባረሩት ጄኔቭ ዉስጥ ሥለ መንግሥት በሰጡት ሐላፊነት በጎደለዉ መግለጫቸዉ ምክንያት ነዉ። በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተልዕኮ የመንግሥትን ሥራ ማገዝ፤ ማሟላትና ማጠናከር እንጂ አፍራሹ አይደለም። ድርጅቱ የደቡብ ሱዳን ሸሪክ ነዉና።»

ብሪታኒያዊዉ ዲፕሎማት፤ በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የርዳታ ድርጅቶች አስተባባሪነትን ሥልጣን ከድርጅቱ ምትክል ልዩ መልዕክተኛነት ሐላፊነት ጋር ደርበዉ የያዙ ናቸዉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ፓን ጊ ሙን የደቡብ ሱዳንን እርምጃ አዉግዘዋል። ደቡብ ሱዳን ዉሳኔዋን እንድትሽርም ጠይቀዋል።

ዛሬ ጎራ ለይተዉ የሚፋለሙት የቀድሞ አማፂ ቡድን መሪዎች ደቡብ ሱዳንን ከሱዳን እንዲገነጥሉ ሁለንተናዉ ድጋፍ ትሰጥ የነበረችዉ ዩናይትድ ስቴትስም የጁባ መንግሥት በብሪታኒያዊዉ ዲፕሎማት ላይ ሲዞርባቸዉ አልታገሰችም። የዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ትናንት እንዳሉት የላንሰር መባረር «በደቡብ ሱዳን ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሚያደርግዉን ጥረት የሚጨናጎል ነዉ»

ቃል አቀባይ አቴንይ ግን ላንሰር ሥለ ደቡብ ሱዳን ያሉትን ሌላ ሐገር ላይ ብለዉት ቢሆን ኖሮ ሌላ አይጠብቃቸዉም ነበር።«አዎ የደቡብ ሱዳንን ዉሳኔ ለመቀበል የሚቸገሩ እንዳሉ ይገበኛል። ይሕ ተገቢ ነዉ። ግን ማንም ሉዑላዊ ሐገር የሚያደርገዉን ነዉ ያደረግነዉ።ቶቢ ላንሰር ሥለየትኛዉም ሐገር ተመሳሳይ ነገር ቢናገሩ ተመሳሳይ እርምጃ ይግጥማቸዉ ነበር።»

Südsudan Zivilisten auf der Flucht in Bentiu
ምስል picture-alliance/AP Photo

ሰዉዬዉ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎችን በመዉቀስ የታወቁ ናቸዉ። ጦርነቱ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያደረሰዉን ጥፋት አጥብቀዉ ሲተቹ ነበር። ቃል አቀባይ አቴንይ እንደሚሉት ግን ላንሰር ከትችት አልፈዉ ሊያበጣብጡም ቃጥቷቸዋል።

«በቅርቡ ለሲ ኤን ኤን በሰጡት መግለጫ የደቡብ ሱዳን አመራር (ሕዝብ ማስተዳደር) እያቃተዉ ነዉ፤ ሐገሪቱም ከመጥፋት አፋፋ ላይ ናት ብለዋል። ሥለዚሕ ለሕዝቡ ተስፋ ከመስጠት ይልቅ ሥጋት እየለቀቁበት ነዉ። እዚሕ የሚገኙት መንግሥትን ለመደገፍ እንጂ ዉድቀቱን ለመተንበይ አይደለም።»

ላንሰር ባይባበረሩም የደቡብ ሱዳን ተልዕኳቸዉን ጨርሰዉ ሌላ ሥፍራ ለመቀየር ሳምንት ነበር የቀራቸዉ።የጁባ መንግሥት ዉሳኔ- ያለቀ ሠዓትም ቢሆን በላንሰር የወደፊት ዲፕሎማሲያዉ ተልዕኮ ላይ ተፅኖ ማሳረፉ አይቀርም።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ