1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ አፍሪቃው ዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ አዲስ መሪ

ሰኞ፣ ግንቦት 3 2007

ዴሞክራሲያዊ ትብብር (Democratic Alliance (DA) በመባል የሚታወቀው የደቡብ አፍሪቃ ዋንኛ ተቃዋሚ ፓርቲ ጥቁሩን ፖለቲከኛ ምሙሴ ማይማኔ መሪ አድርጎ መረጠ። የፓርቲው የመጀመሪያ ጥቁር መሪ ለመሆን የበቁት ማይማኔ ፓርቲው በሐገሪቱ ጥቁር ሕዝብ ዘንድ ያለዉን ተቀባይነት ያሳድጋሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

https://p.dw.com/p/1FOID
Südafrika Mmusi Maimane
ምስል imago/Gallo Images

የደቡብ አፍሪቃውን ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን አጥብቀው በመተቸት የሚያታወቁት ምሙሴ ማይማኔ የዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲን ከጎርጎሮሳዊው 2011 ዓ.ም. በቃል አቀባይነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። የ34 አመቱ ወጣት ፓርቲያቸው ፖርት ኤልዛቤት ከተማ ባደረገዉ ጉባኤ የቀድሞዋን መሪ ሄለን ዚልን ለመተካት ከምክትል ሊቀ መንበሩ ዊልሞት ጄምስ ጋር ተፎካከረዋል።አሸነፉ።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ በታሪኩ ከፍተኛ ወንበር ያሸነፈው የዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ ውክልናው በቀዳሚነት ለነጮች ብቻ ነው የሚል ነቀፋ ይሰነዘርበታል። ማይማኔን የዚህ ፓርቲ የመጀመሪያው ጥቁር መሪ ሆነዋል። ማይማኔን ፓርቲያቸው ባለፈው ምርጫ ባገኘው ውጤት ላይ ተመስርተው ተቀባይነታቸውን የማሳደግ ስራ እንደሚጠብቃቸው ለዶይቼ ቨለ ተናግረዋል።

Wahlen in Südafrika ANC Anhängerin
ምስል AP

«አጀማመራችን ጥሩ ነው። የነጻነት፤ፍትሃዊነትና የእኩል እድልን ዋጋ በኮንግረስ ለማስተዋወቅ ሞክረናል። ትልቁና ከባዱ ስራ እነዚህን ዋጋዎች የሚጋሩን ደቡብ አፍሪቃውያንን ለእኛ ድምጽ እንዲሰጡ ማድረጉ ነው። እናም ፓርቲውን ማሳደግ እንዳለብን እናምናለን።»

ማይማኔ በሙያቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሰባኪ ናቸው። ከነውጠኛው የኢኮኖሚ ነጻነት አርበኞች (Economic Freedom Fighters) መሪ ጁሊየስ ማሌማ ጋር መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ይነገርላቸው። ማይማኔ የዴሞክራሲያዊ ትብር ፓርቲን ስልጣን ሲቆናጠጡ በእድሜያቸውና ባላቸው አነስተኛ ልምድ ስልጣኑ አይገባቸውም የሚል ጥያቄ ተነስቶባቸዋል። የፖለቲካ ተንታኞች የቀድሞዋ የፓርቲው መሪ ሄለን ዚል የጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የዘየዱት መላ ነው ሲሉም ይደመጣሉ። ማይማኔም ቢሆኑ ለነጮች ብቻ ቅድሚያ ይሰጣል የሚባለውን የዴሞክራሲያዊ ትብብር ፓርቲ እንደ አዲስ ለመገንባት ተስፋ አላቸዉ።

«ለማንኛውም ዘር ያልቆመ የሁሉም ደቡብ አፍሪቃውያን ፓርቲ የመገንባት መርህ አለን። ይህን ለማሳካት እሴቶቻችንን ለደቡብ አፍሪቃውያን ማስተዋወቅ እና መነጋገር ይኖርብናል። እናም በሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች በርካታ ተወካዮች ያሉት ፓርቲ ለመገንባት እቅድ አለን። የእኛ ፓርቲ ባልደረሰባቸው አካባቢዎች በጥቁሮች የመኖሪያ አካባቢዎች ሁኔታዎች እና ሙስናን በመሳሰሉ ጉዳዮች ከፍተኛ ቁጣ አለ። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በመስራት ፓርቲውን ለመገንባት እና ተፎካካሪ ለመመሆን እቅድ አለኝ።»

ማይማኔ አሁን ሊመሩት የተረከቡትን ፓርቲ በአባልነት የተቀላቀሉት በጎርጎሮሳዊው 2009 ነው። ከቃል-አቀባይነት ወደ መሪነት በፍጥነት የተሻገሩት ሰው በሚቀጥለው አመት ከአፓርታይድ መውደቅ ጀምሮ በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኘውን የአፍሪቃ ብሄራዊ ኮንግረስን(ANC) የሚገጥሙበት አካባቢያዊ ምርጫ የመጀመሪያ ፈተናቸው ይሆናል።

Wahlen in Südafrika ANC Anhängerin
ምስል AP

በፖርት ኤልዛቤጥ ከተማው ጉባኤ ለደጋፊዎቻቸው «እናሸንፋለን» ሲሉ ቃል የገቡት ማይኔማ ገና ካሁኑ በፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል።የዴሞክራያዊ ትብብር ፓርቲ ሊቀ-መንበርነታቸው በታወጀበት ጉባኤ ላይ «ፕሬዝዳንት እንዳይሳሳቱ እርሶም በፍርድ ቤት የሚቆሙበት ቀን ይመጣል።» ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞዋ መሪ ሄለን ዚሌ ለስምንት አመታት ፓርቲውን በሊቀ-መንበርነት ያገለገሉ ሲሆን የጎርጎሮሳዊውን 2014 ዓ.ም. ምርጫ 22 በመቶ ወንበር ካሸነፉ በኋላ በቃኝ ያሉት በድንገት ባለፈው ወር ነበር። ‘የስዌቶው ኦባማ’ የሚል ቅጽል ስም የወጣላቸው ማይማኔ ፓርቲያቸው ተስፋ እንዳደረገው የስራ አጥ ወጣቶችን ቀልብ ለመሳብ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው የፖለቲካ ተንታኞች እየተናገሩ ነው። ፓርቲዉ እንደ ካሁን ቀደሙ ተመሳሳይ አቋም ተመሳሳይ ፖሊሲ ይዞ ከዘለቀ ‘በጥቁር የሚመራ የነጮች ፓርቲ’ተብሎ ሊብጠለጠል ይችላል ተብሏል።

ክሪስፒ ምዋኬዲዩ /እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሀመድ