1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደ/አፍሪቃ ፕሬዚደንት እና የኢሜይል ቅሌቶች

ቅዳሜ፣ ግንቦት 26 2009

ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ የሚያጋጥሟቸውን ጠንካራ የፖለቲካ ቅሌቶች በሙሉ እንደሚቋቋሙ በተደጋጋሚ አሳይተዋል።  የሀገሪቱ ገዢው ፓርቲ ፣ የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ፣ በምህፃሩ «ኤኤንሲ» ባለፈው የሳምንት መጨረሻ ለሶስት ቀናት ባካሄደው ስብሰባው  ላይ አንዳንድ የፓርቲው  አባላት በዙማ ላይ የመታመኛ ድምፅ እንዲካሄድ ማመልከቻ አቅርበው ነበር።

https://p.dw.com/p/2e3dn
Südafrika | Präsident Jacob Zuma
ምስል REUTERS/S. Hisham

Fokus Afrika A _ 03.06.2017 - MP3-Stereo

ይሁንና፣ ፕሬዚደንት ዙማ ምንም እንኳን በምግባረ ብልሹነት የሚያስጠይቋቸው በሀገሪቱ ከታወቁት ባለተቋም ከሆኑት ከጉፕታ ቤተሰብ አባላት ጋር የተለዋወጡዋቸው የኢሜይል መልዕክቶች ሰሞኑን ሾልከው መውጣታቸው ቢሰማም፣ በአንፃራቸው የቀረበው ማመልከቻ በታማኞቻቸው ድጋፍ አማካኝነት ውድቅ ሆኗል። ሁለት የደቡብ አፍሪቃ ዕለታዊ ጋዜጦች ፕሬዚደንት ዙማ ያን ያህል ጥሩ ስም ከሌላቸው የጉፕታ ቤተሰብ ጋር በኢሜይል ከተለዋወጡዋቸው መልዕክቶችን አንዳንዱን በይፋ ያወጡበት ድርጊት በመላይቱ ሀገር ትልቅ ቁጣ  ቀስቅሷል። በኢንተርኔት የዜና ገጽ ያለው «ደይሊ ማቨሪክ»ም ከ100,000 እስከ 200,000 የሚጠጉ ሌሎች ተጨማሪ ኢሜይል መልዕክቶችን በቅርቡ ለንባብ እንደሚያቀርብ ማስታወቁም የህዝቡን ቁጣ ይበልጡን አባብሷል። ይኸው የኢንተርኔት ድረ ገጽ «ስኮርፒዮ» የተባለ አዲስ መርማሪ ቡድን ያቋቋመ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ከጉፕታ ቤተሰብ ጋር ያለውን የፕሬዚደንቱን ግንኙነት በሚመለከት በእጁ ያሉ እና   የሾለኩ የኢሜይል መልዕክቶች እንዳይሰረዙበት በመስጋት በአሁኑ ጊዜ  ከደቡብ አፍሪቃ ውጭ በሚገኝ  የመረጃ ማጠራቀሚያ ቋት ውስጥ ማስቀመጥ ጀምሯል።  
ከጄኮብ ዙማ ጋር ወዳጅ የሆነው የጉፕታ ቤተሰብ በፕሬዚደንቱ አመራር ላይ ተፅዕኖ ማሳረፋቸው ከብዡ ጊዜ ወዲህ የሚታወቅ  ነው።  አሁን ሾልከው የወጡት የኢሜይል መልዕክቶች የህንድ ዝርያ ያለባቸው የባለተቋሙ ቤተሰብ በመንግሥቱ ስራ ውስጥ ያሳረፈው ተፅዕኖ ምን ያህል ስር የሰደደ መሆኑን እና የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንትን እና አንዳንድ ሚንስትሮቻቸውን እንዴት እንደተቆጣጠራቸው  በግልጽ አሳይተዋል።  ሰፊ ተነባቢነት ያላቸው የታወቁት የሀገሪቱ ዕለታዊ ጋዜጦች «ሲቲ ፕሬስ» እና «ሳንደይ ታይምስ»  ፕሬዚደንቱ የስልጣን ዘመናቸውን ሲያበቁ ኑሯቸውን በዱባይ ለመምራት እቅድ እንዳላቸው አጋልጠዋል። ከዚሁ የፕሬዚደንቱ እቅድ በስተጀርባ የጉብታ ቤተሰብ እጅ እንደሚገኝበት ይገመታል።  
«ሳንደይ ታይምስ» በአምዱ ባሰፈረው አንድ ደብዳቤ ፣ ፕሬዚደንት ዙማ የተባበሩት የዐረብ ኤሚሮችን ሁለተኛ የመኖሪያ ቦታቸው ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ለአቡ ዳቢ አልጋወራሽ  እንደሚከተለው ገልጸዋል፣ « እኔ እና ቤተሰቤ በቀረበልን ሀሳብ መሰረት መኖሪያችንን በተባበሩት የዐረብ ኤሚሮች በምናደርግበት ጊዜ የርስዎን ከለላ ማግኘት እንፈልጋለን፣ ይህ ለኛ ክብር ነው። » ይላል፣ ይፋ የወጣው ደብዳቤ እንደሚጠቁመው ፣ ደብዳቤውን ያረቀቀው የጉፕታ ቤተሰብ ነው።
ፕሬዚደንት ዙማ ወደ ዱባይ ለመሄድ ማሰባቸው  ስልጣናቸውን ሲያበቁ ያለመከሰስ ዲፕሎማሲያዊ መብታቸውንም ስለሚያጡ፣ ሊነሳባቸው ከሚችል የሕግ ጥያቄ ለማምለጥ መሆኑን ተንታኞች ይገምታሉ።  ከስልጣን ዘመናቸው በኋላ በንካንድላ የሚገኘው እና በትውልድ አካባቢያቸው ንካንድላ የሚገኘው የናጠጠ መኖሪያ ቤታቸው ብቸኛው መኖሪያቸው እንደሚሆን ዙማ አመልክተዋል።  ዙማ ይህንኑ ቤታቸውን በመንግሥት ገንዘብ አሳድሰው በማሰራታቸው ወጪውን እንዲከፍሉ ፍርድ ቤት መበየኑ ይታወቃል። የፖለቲካ ተንታኙ ዳንየል ሲልከ የዙማን ወደ ዱባይ የመሄድ እቅድ እውን ሊሆን የማይችል ሆኖ አግኝተውታል። «  ዙማ ከስልጣን ዘመናቸው ፍፃሜ በኋላ ለመከተል የወጠኑት ስልት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ብዬ አላስብም።  የኢሜይል መልዕክቶቹ ትክክለኛ ባይሆኑም እንኳን፣  እቅዳቸው ተጋልጦባቸዋል፣  ጉዳዩ አንዴ  ይፋ በመውጣቱም  የመገናኛ ብዙኃን ጉዳዩን  በቅርብ መከታተላቸው አይቀርም።  ኢሜይሉ ትክክለኛ ሆነም  አልሆነ ጉዳዩ  በቀረው የፕሬዚደንቱ የስልጣን ዘመን ላይ ጥላ መጣሉ አይቀርም።  »
አሁን እንደሚታየው፣ ፕሬዚደንት ዙማ በፕሪቶርያ የሚገኘውን የመንግሥቱን ጽሕፈት ቤት ለቀው የሚወጡ አይመስልም። አንድ ከፍተኛ የገዢው  የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ ፣ በምህፃሩ የ«ኤኤንሲ» አመራር አባል ዦኤል ኔትስሂቴንሴ በዙማ ላይ የመታመኛ ድምፅ እንዲካሄድ ያቀረቡትን ሀሳብ የፓርቲው ማዕከላይ ኮሚቴ ባለፈው የሳምንት መጨረሻ ውድቅ አድርጎታል። 
ባለፉት ስድስት ወራት ይህ ዓይነት መመልከቻ ሲቀርብ የሳምንቱ መጨረሻ ሁለተኛ ነበር። ማዕከላዩ ኮሚቴ በብዛት በዙማ ታማኞች የተያዘ ሲሆን፣ ዙማን ከማንኛውም ቅሌት ከመከላከል ወደኋላ እንደማይሉ ተንታኙ ሲልከ ገልጸዋል።
« «ኤኤንሲ»  ፕሬዚደንት ዙማን  የስልጣን ዘመናቸው ሳያበቃ በፊት ልቀቁ  ለማለት  በጣም ስጋት ያደረበት ይመስላል።   ፓርቲው ፣  የቀድሞ ፕሬዚደንት ታቦ ምቤኪን የአመራር ዘመናቸው ሳያበቃ በፊት ከስልጣን ባወረደበት ጊዜ ያጋጠመውን ችግር በሚገባ ነው የሚያስታውሰው።  እና ይህን ተሞክሮ  ለመድገም ይፈልጋል  ብዬ አላስብም። »
ያም ቢሆን ግን በፕሬዚደንት ዙማ አንፃር ስልጣናቸውን አስቀድመው እንዲለቁ ግፊቱ መጠናከሩ እንደማይቀር የፖለቲካ ተንታኙ ዳንየል ሲልከ ገምተዋል።
« «ኤኤንሲ»  ከሁለት ዓመት በኋላ  በሀገሪቱ የሚካሄደውን ምርጫ የሚመለከት ጉባዔ የተያዘው 2017 ዓም ከማብቃቱ በፊት  ያካሂዳል።  ይህ  አንዱ የፓርቲው  ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ነው።  እና ፓርቲው፣   ይህ መደረግ ያለበትን መደበኛ ሂደት  ለመዝለል ወይም ለማቃወስ  አስቧል የሚል ወቀሳ እንዲቀርብበት  አይፈልግም። በዚያም ሆነ በዙህ ፣ «ኤኤንሲ»  በስድስት ወር ውስጥ አዲስ የፓርቲ መሪ ለመምረጥ ጉባዔ ያካሂዳል።  »
ፕሬዚደንት ዙማ ባለፈው ሚያዝያ ወር የካቢኔ ሹም ሽር ያካሄዱበት ርምጃቸው ቅሬታ ፈጥሮ እንደነበር አይዘነጋም። ያኔ ሳይታሰብ በአንጻራቸው ትችት የሰነዘሩትን የገንዘብ ሚንስትር ፕራቪን ጎርደንን አባረው ታማኝ ባሏቸው ማሉዚ ጊጋባ ተክተዋቸዋል።  ጎርደን ገዢው ፓርቲ  70 ቢልዮን ዩሮ አውጥቶ ለመገንባት የያዘውን  እና የጉፕታ ቤተሰብ ተቋም ትልቅ ጥቅም ሊያገኝበት ይችል ነበር የተባለውን የአቶም ኃይል ማመንጫ ተቋም እቅድ በጥብቅ ነበር የተቃወሙት።  
ሰሞኑን ሾልከው የወጡት የዙማ የኢሜይል መልዕክቶች የደቡብ አፍሪቃ የማዕድን ሚንስትር ሞሴቤንዚ ዝዋኔ በጎርጎሪዮሳዊው 2015 ዓም እንዴት ወደ ስልጣን እንደመጡ አሳይተዋል።  ዝዋኔ የሚንስትርነቱን ቦታ ሊይዙ ሁለት ወራት ሲቀራቸው የግል የትምህርት እና የስራ ታሪካቸው ወይም  ካሪክለም ቪቴ ለእይታ ወደ ጉፕታ ተቋም ተልኮ ነበር።  የጉፕታ ቤተሰብ የካቢኔ አባላት እና የባለተቋማት ኃላፊዎች ለስራ ወደሌላ ቦታ በሚሄዱበት ጊዜ  በተደጋጋሚ የጉዟቸውን እና የሆቴል ወጪዎቻቸውን እንደሚሸፍኑ የኢሜይል መረጃዎች አረጋግጠዋል። የጉብታ መረብ በመንግሥቱ ስራ ውስጥ በጣም ስር መስደዱን ሌላው የፖለቲካ ተንታኝ ሲትሄምቢሌ ምቤቴ ገልጸዋል። 
« አሁን እያየን ያለነው  ፕሬዚደንቱን ከስልጣን ለማውረድ የሚያስችሉ ማስረጃዎች እየተሰበሰቡ መሆናቸውን ነው።  ይሁንና፣  ይህ ርምጃ በቀጥታ ፕሬዚደንቱን ስልጣናቸውን እንዲለቁ ወደ መጠየቁ ወይም ከርዕሰ ብሔርነት ስልጣናቸው ወደማውረዱ ውሳኔ ያደርሳል ብዬ አላስብም። »  
የ«ኤኤንሲ»  ማዕከላይ ኮሚቴ  ፕሬዚደንቱን ሙሉ ለሙሉ እንደሚደግፍ እንግዲህ ከጥቂት ቀናት በፊት ድጋሚ አሳይቷል። ያጋጠሟቸውን ቀውሶች ሁሉ እስካሁን የተቋቋሙት የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ሾልከው ወጡ በተባሉ  የኢሜይል መልዕክቶች ሰሞኑንን የተጋረጠባቸውንም ችግር ወደኋላ ለማድረግ ቆርጠው ተነስተዋል። የሀገሪቱ መንግሥት የኢሜይል መልዕክቶቹን የሀሰት መረጃዎች ሲል አጣጥሏቸዋል። 

Südafrika Atomkraftwerk Koeberg nahe Kapstadt
ምስል picture-alliance/dpa/EPA/N. Bothma
Südafrika Privatvilla von Präsident Jacob Zuma
የዙማ የንካንድላ መኖሪያ ቤታቸውምስል Getty Images/AFP/M. Longari
Architektur VAE Dubai Gebäude im Stadteil Marina
ምስል picture-alliance/Geisler-Fotopress
Afrika Johannesburg Ajay und Atul Gupta bei Interview
ምስል imago/Gallo Images


አርያም ተክሌ/ማርቲና ሺቪኮቭስኪ
ማንተጋፍቶት ስለሺ