1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳቮስ የኤኮኖሚ መድረክና የጀርመን ቻንስለር ንግግር

ሐሙስ፣ ጥር 18 1998

እስከፊታችን ዕሑድ የሚዘልቀው ዓመታዊው የዳቮስ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ መድረክ ትናንት ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር በሰፈነበት ሁኔታ በስዊትዘርላንድ ተከፍቷል። መድረኩን በንግግር የከፈቱትም የጀርመን ቻንስለር አንጌላ ሜርከል ናቸው።

https://p.dw.com/p/E0e4
ቻንስለር አንጌላ ሜርከል
ቻንስለር አንጌላ ሜርከልምስል AP

በዘንድሮው ውይይት ከሁለት ሺህ የሚበልጡ የፖለቲካና የምጣኔ-ሐብት ዘርፍ ተጠሪዎች ይሳተፋሉ። ከአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት መሪዎች መካከል ወደ ስብሰባው ብቅ ያሉት የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርከል ብቻ ሲሆኑ መድረኩን በንግግር ለመክፈትም ዕድል አግኝተዋል። ሜርከል በዚሁ ንግግራቸው ጀርመን የምጣኔ-ሐብት ችግሯን ለመወጣት ማሕበራዊ የገበያ ኤኮኖሚ ሥርዓቷን መጠገንና መላ ሃይሏን ለዕድገት በሥራ ላይ ማዋል እንዳለባት አስረድተዋል።

የዶቼ ቬለ ባልደረባ ዮአሂም-ሹበርት-አንከንባወር ከስፍራው የላከው ዘገባ እንደሚከተለው አንጌላ ሜርከል በዳቮስ በይፋ የተገኙት ብቸኛዋ የአውሮፓ ሕብረት መራሄ-መንግሥት በመሆናቸው ተሰብሳቢዎቹ ለጀርመኗ ቻንስለር ንግግር ክብደት መስጠታቸው አልቀረም። ሜርከል የጉባዔውን የዘንድሮ መፈክር የፈጠራን ወይም የጽንሰ-ሐሳብ ማፍለቅን አስፈላጊነት መነሻ አድርገው ባሰሙት ንግግር “ፈጠራ የግድ አስፈላጊ ነው ለማለት ይቻላል። ከራሴ ሃላፊነት ተነስቼ ከተናገርሁ ፈጠራ ሁልጊዜም የጥሩ ፖለቲካ አንቀሳቃሽ ሃይል ሊሆን ይገባዋል። ዛሬ ደግሞ ይህ ከመቼውም የበለጠ ወቅታዊነት አለው። የሃሣብ ፉክክርን መቋቋም የቻለ የወደፊት ዕድሉንም ማቀናጀት አይገደውም” ብለዋል።

አንጌላ ሜርከል አያይዘው እንደተናገሩት ዛሬ ዓለም፤ አውሮፓም ብትሆን ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ከተካሄደው የኢንዱስትሪ ዓብዮት በሚመሳሰል መሠረታዊ የተሃድሶ፤ ወደ ዕውቀት ሕብረተሰብ በመለወጥ ሁኔታ ላይ ነው የምትገኘው። ለለውጥ አስፈላጊ የሆነውን የሃሣብ ፉክክር አንስተው ሲያስረዱም በሃላፊነት ላይ የተመሠረተ ነጻነት ያሉትን የአዲስ ማሕበራዊ የገበያ ኤኮኖሚ ሥርዓት ጽንሰ-ሃሣብ ጠቅሰዋል። አንጌላ ሜርክል እንዳሉት ይሁንና የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሉድቪግ ኤርሃርድ ያራመዱት ጽንሰ-ሃሣብ ከዛሬው ዘመን ተጨባች ሁኔታ መጣጣም ይኖርበታል።
ሜርከል ቀጠል በማድረግም “ስለ ጀርመን ልናገርና የበለጠ መፈናፈኛ፤ በትክክል ለመናገር ብዙ ነጻነት የምንፈልግ ይመስለኛል። ሥራ አጥነት፤ ዛሬ በጀርመን ትልቁ ችግር ነው። ግን ሥራ ዕድገትን፤ ዕድገትም ነጻነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ዓላማው በመጀመሪያ የዕድገትን ዕድል እንጂ የሚከተለውን ችግር ማተኮሪያ ማድረግ የለበትም። ይህ ደግሞ በሃላፊነት ላይ የቆመ ነጻነት ነው።”

ቻንስለር አንጌላ ሜርከል ዕድገትን፣ የሥራ አጦች ቅነሣንና ተሃድሶን በተመለከተ ጀርመንን በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት እንደገና በአውሮፓ ቀደምት ከሆኑት ሶሥት አገሮች ደረጃ ለማድረስ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚጥሩ ተናግረዋል። ቻንስለሯ እንዳስረዱት እርግጥ ባለፉት ዓመታት ሃሣብ በተግባር ሳይተረጎም ነው የቀረው። በመሆኑም ጀርመን እንደገና በራስ መተማመንን እንድታዳብርና በምታፈልቀው ሃሣብ መኖር እንድትችል ማድረጉ ግድ ነው። ሜርከል ተሃድሶ ለሁሉም ቁልፍ መሆኑን ጠቅሰው የአገሪቱ የበጀት፣ የጡረታና የሥራ ገበያ ፖሊሲ የግድ መጠገን እንደሚኖርበት ሳያስገነዝቡም አላለፉም።

ቻንስለሯ በንግራቸው በጀርመንና በአውሮፓ የወደፊት ዕጣ ብቻ አልተወሰኑም። አገራቸው የዓለም ንግድ ሥርዓትን ለማለዘብ በሚደረገው አስቸጋሪ ጥረት መፍትሄ ለማስገኘት የተቻላትን ሁሉ እንደምታደርግም ቃል ገብተዋል። ባለፈው ወር ሆንግ ኮንግ ላይ ተካሂዶ የነበረው የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ በአርሻ ድጎማና በኢንዱስትሪ ምርቶች አገልግሎት አኳያ ባለ ችግር መሠረታዊ ዕርምጃ ሳይታይ መቅረቱ አይዘነጋም። አንጌላ ሜርከል “ሆንግ ኮንግ ላይ ምን እንደደረሰ አይተናል፣ ይህ እንደገና እንዳይፈጸም፤ የዓለም ንግድ ድርጅትም ዓለምአቀፍ ውሎችን በቀደምትነት የሚያከብር አካል እንዲሆን እንጥራለን ብለዋል።