1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ እጣ ፈንታ

ዓርብ፣ ግንቦት 5 2008

የአውሮጳ ህብረት በዓለም ግዙፉን የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለመዝጋት የኬንያ መንግስት በወሰነው ውሳኔ ላይ ዴፕሎማሲያዊ ድርድር እንዲደረግ ጥሪ አቅርቦ ነበር። የኬንያ መንግስት ግን እቅዱን እንደማያጥፍ አስታውቋል። የኬንያ አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በዳዳብ የሚገኙ ስደተኞችን ለማዘዋወር አንድ ቢሊዮን ሽልንግ ማዘጋጁቱን አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/1ImPx
Kenia Das Flüchtlingslager Dadaab
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

[No title]

ኬንያ በዳዳብ የሚገኙ ወደ 600,000 የሚጠጉ በአብዛኛው የሶማሊያ ስደተኞችን ወደ መጡበት የመመለስ እቅዷን ገፍታበታለች። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆሴፍ ንካይዜሪ በዕለተ ረቡዕ በናይሮቢ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መንግስታቸው እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የጊዜ ሰሌዳ እያወጣ መሆኑን እና የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ በመጪው ህዳር ይዘጋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

«ስደተኞቹን ወደ መጡበት ለመመለስ፤የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያን ለመዝጋት እና አስፈላጊ ቴክኒካዊ መሰረተ-ልማቶችን ለማዘጋጀት 10 ሚሊዮን ዶላር አዘጋጅቷል።»

የኬንያ መንግስት በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እዘጋለሁ የሚለውን ማስፈራሪያ አለዝቧል። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆሴፍ ንካይዜሪ መንግስታቸው ዒላማ ያደረገው የሶማሌያ ስደተኞችን በተለይ በዳዳብ የሚገኙትን መሆኑን ተናግረዋል። ንካይዜሪ ለጊዜው በዓለም ግዙፍ የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መሆኑን አረጋግጠዋል።

«የኬንያ ሪፐብሊክ መንግስት የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያን ለመዝጋት ዝግጅት ጀምሯል። ስደተኞቹ ወደ መጡበት የሚመለሱ አሊያም ወደ ሶስተኛ አገር የሚላኩ ይሆናል።»

በኬንያ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የህገ-ወጥ አደን፤የሰዎች እና የጦር መሳሪያ ዝውውር ማዕከል በመሆናቸው አገሪቱ በዓለም አቀፍ የደህንነት ምዘና እያሳጧት እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በዌስትጌት የገበያ ማዕከል እና ከ200 በላይ ሰዎች የተገደሉበት የጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ጥቃቶች የተጠነሰሱት በዳዳብ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ነው ብለዋል።

በግዳጅ ወደ አገራቸው የመመለስ ስጋት የተደቀነባቸው የሶማሌያ ስደተኞች አገራቸው ለደህንነታቸው አስጊ መሆኗን በስጋት በመግለጥ ላይ ናቸው። ስደተኞቹ አገራቸው ለመመለስ አመቺ ባለመሆኗ የኬንያ መንግስት በመጠለያ ጣቢያ እንዲቆዩ እንዲፈቅድላቸው መወትወት ይዘዋል። የ38 አመቷ ሐልጋን አኒሶ ወደ ሶማሊያ መመለስ ከማይፈልጉት መካከል አንዷ ናት።

«ህይወት በሶማሊያ እጅጉን ከባድ ነው። አሁን እዚህ በቆምኩበት ቅጽበት ባለቤቴ ወዴት እንዳለ እንኳ አላውቅም። አንድ ምሽት በቤታችን ሳለን ሁለት ሰዎች ወደ እኛ ቀርበው ይተኩሱብን ጀመር። ባለቤቴ አመለጠ። እኔ ደግሞ ከልጆቼ ጋር ለመቆየት ተገደድኩ። ሰዎቹ ባለቤቴ ወዴት እንዳለ ይጠይቁኝ ጀመር። በጠመንጃቸው ሰደፍም ደበደቡኝ። እጅግ አስፈሪ ነው። ወደ ሶማሊያ መመለስ አልሻም። በዚህ ምንም የለኝም። ብታመም እንኳ ህክምና አላገኝም። የምግብ እደላው ለእኔ እና ለልጆቼ በቂ አይደለም። ይሁንና መቼም ቢሆን ሰላም ወደ ሌለበት ሶማሊያ አልመለስም። እዚህ መቆየትን እመርጣለሁ።»

Konflikt im Südsudan Flüchtlinge 17.01.2014
ምስል Phil Moore/AFP/Getty Images


የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው እና የጸጥታ ተንታኙ ኤኖክ ማካንጋ የኬንያ መንግስት ውሳኔ ካስደሰታቸው መካከል ናቸው። ማካንጋ የኬንያ መንግስት የራሱን ዜጎች ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንደተጣለበት ይናገራሉ።

«ኬንያ ዜጎቿን የመጠበቅ ህገ-መንግስታዊ መብት አላት። ጉዳዩን በጥልቀት ከተመለከትንው እነዚህ ሁለት ካምፖች በደህንነት ጉዳይ አሉታዊ ሚና አላቸው። ሁለቱ ካምፖች ለወንጀለኞች መሸሸጊያ ሆነው አገልግለዋል።»


እሸቴ በቀለ/አንድሪው ዋሲኬ
አዜብ ታደሰ