1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዴር- ሱልጣን ገዳም ጥሪ

ሐሙስ፣ ጥር 2 2005

በቅድስቲቱ አገር በእየሩሳሌም ክርስቶስ የተሰቀለበት የተቀበረበት፤ እንዲሁም የተነሳበት ስፍራ ተብሎ በሚታመንበት በጎልጎታ ተራራ ላይ የሚገኘዉ ዴር- ሱልታን ገዳም የሚገኘዉ የኢትዮጳያ ይዞታ፤ በመፈራስ ላይ ከመሆኑ የተነሳ፤ እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን መነኮሳቱ እየተናገሩ ነዉ።

https://p.dw.com/p/17HBF
ምስል X Verleih AG

ርግጥ ይህ መኖርያ ቤት በዓለም ዙርያ ከሚገኙት የጋራ በኖርያ ቤቶች ለየት ያለ ሁኔታ ይታይበታል ይላል ፊልሙ ሲጀምር። ከብዙ ምዕተ-ዐመት ጀምሮ እየሱስ በተቀበረበት በጎልጎታ በሚገኘዉ በዴር-ሱልጣን ገዳም፤ ስድስት የተለያዩ ሀገራት የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ ጠባብ በሆነ መተላለፍያ ጎን ለጎን ቦታን ከልለዉ ስርዓተ ሃይማኖታቸዉን ያካሂዳሉ። የግሪክ ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የሮማን ካቶሊካዉያን ቤተክርስትያን፤ የሶርያ ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የአርሜንያ ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እና የግብጽ ኮፕት ቤተክርስትያን ይገኙበታል። በዓለም እጅግ ትልቁ የተሰኘዉ የየተለያዩ ሀገራትን በአንድ ባቀፈዉ በዚህ ቤተክርስትያን ግን፤ ከሰላም ይልቅ ጠብ መጠንከሩን ይህ ጥናታዊ ፊልም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

Jerusalem Kirchen
ምስል DW/H. Melesse

ፊልሙን ይዘን በዱር ሱልጣን ገዳም ስለ ኢትዮጵያ ይዞታ ስለ ኢትዮጳያዉያን ምዕመናን እና አባቶች ጭንቀት ማብራርያ የሰጡትን አባ ገብረስላሴ ተስፋን ፈልገን አገኘናቸዉ። አባታችን በፊልሙ እንደሚታየዉ ችግሩ እንዲህ የጠነከረ ነዉ እንዴ ስንል ነበር መጀመርያ የጠየቅናቸዉ። እንደ አባ ገበረስላሴ፤ ግብፃዉያን ቦታዉን እንዳናድስ እየተከላከሉ ነዉ፤ በዚህም ምክንያት ቤቱ በላያችን ላይ እየፈረሰ ነዉ ባይ ናቸዉ። ገዳሙ ከሽህ አመት ግድም ጀምሮ በጭቃ እንደተሰራ የለበሰዉም ቆርቆሮ ተቀዳዶ እያፈሰሰ ነዉ። የመፀዳጃ ቤቱም እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ከሩቅ ጠረን እያመጣ ነዉ። ጀርመናዊዉ የፊልም ስራ አዋቂ Hajo Schmoerus በበኩላቸዉ ይህን ፊልም ስሰራ በጎልጎታ በቆየሁበት ግዝያት በጣም አሳዛኝ ሁኔታዎችን ተመልክቻለሁ ሲሉ የምስክርነት ቃላቸዉን ሰተዉናል፤

«ይህን ፊልም ስሰራ 4 ዓመት በቆየሁበት ግዜ ብዙ ነገሮችን አይቻለሁ። በርግጥ እዝያ ከሚታየዉ እጅግ ከባድ ዉጥረቶች እና ግጭቶች መካከል በኢትዮጵያዉያን አባቶች እና በቅብጣዉያን መነኮሳቶች መካከል ያለዉ ጥል አንዱ ነዉ። በሁለቱ ሀገራት ሃይማኖተኞች መካከል የሚታየዉ ዉጥረት እጅግ ከባድ ነዉ፤ በተቀሩትም አራቱ ሀገራት ሃይማኖተኞች መካከል ያለዉ ችግር ተመሳሳይ ነዉ። አስደናቂ ሆኖ ያገኘሁት ግን፤ የአንድ እናት አብያተ ክርስትያናት የሚባሉት የግብፅ እና የኢትዮጵያ ዓብያተ ክርስትያናት በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነዉ በማየቴ ነዉ» በቅድስት ሀገር እየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ገዳማት ሊቃነ-ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በዴር -ሱልጣን ገዳም የሚታየዉ ችግር መከሰት ከጀመረ ከ240 ዓመት በላይ ሆኖታል ብለዉናል። በዚህ ቦታ ላይ የኢትዮጵያዉያን ይዞታ ለማስጠበቅ በፍርድ ቤት ክርክር ከተጀመረ ወደ መቶ ሰባ አመት በላይ መሆኑን የነገሩን ደግሞ በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የእየሩሳሌም መታሰብያ ድርጅት የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ ተስፋዪ፤ የእየሩሳሌም መታሰብያ ድርጅት የተቋቋመዉ ለዚሁ ችግር መፍትሄ ለማስገኘት ነዉ ሲሉ ገልፀዉልናል። ቅድስት አገር እየሩሳሌምን በተመለከተ መፃህፍትን ለአንባብያን ያቀረቡት በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ዋና ተጠሪ ሊቀነ ካህናት ዶክተር መራዊ ተበጀ በጀርመን እና አካባቢዋ ባሉ ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያዉያን ምዕመናንን በማሰባሰብ በየዓመቱ ለትንሳኤ በዓል ወደ እየሩሳሌም ይጓዛሉ፤ ማህበራቸዉ ይህንን ችግር ለመፍታት ጥረቶችን ያደርጋል፤ ግን መነኮሳቱ የሚኖሩበት ቤትም እጅግ ከመዉደቁ የተነሳ በሃያ አንደኛዉ ክፍለ ዘመን እንኳን ሰዉ አዉሪ የማይኖርበት ሁኔታ ላይ ነዉ ብለዉናል።

Film Plakat Im Haus meines Vaters sind viele Wohnungen
ምስል X Verleih AG

በተመድ 28 ዓመታት ያገለገሉት እና በጡረታ ላይ የሚገኙት አቶ ኪዳኔ አለማየሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ዓለማቀፍ የምዕመናን ማህበር አባል ሲሆኑ ድርጅቱ ለችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ እና በመፈራረስ ላይ ያለዉ ገዳም ጥገና እንዲያገኝ አቤቱታዉን በማሰባሰብ ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ለማቅረብ ዝግጅት ላይ መሆናቸዉንም ገልጸዉልናል። የኢትዮጵያ ንግስት ሳባ እየሩሳሌም በሄደችበት ግዜ እስዋን የተከተሉ ሰዎች ያረፉበት ነበር በሚባለዉ በዚሁ በቅዱስ ጎልጎታ ስፍራ በሚገኘዉ በዴር-ሱልጣን ገዳም ስያሜዉ በጥንት ዘመን በአረቦች የተሰየመና የንጉስ ገዳም የሚል ትርጉም እንዳለዉ ስለገዳሙ ያነጋገርናቸዉ ገልጸዉልናል። በእየሩሳሌም የሚገኘዉ ይህ ታሪካዊ ገዳም የምዕመናኑ እና የሃይማኖቱ ተከታዮች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህዝብ አልፎም የመንግስት ጉዳይ መሆን እንዳለበት መነኮሳቱ ጥርያቸዉን ያሰማሉ። በአዲስ አበባ የሚገኘዉ የእየሩሳሌም መታሰብያ ድርጅት በበኩሉ መንግስት በጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ከሀገራቱ መንግስት ጋር በመወያየት መፍትሄን ማስገኘት እና ይዞታዉንም ለማስከበር ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ባል ነዉ። በእየሩሳሌም ከዴር- ሱልጣን ገዳም ባሻገር የንግስት ዘዉዲቱ፤ የእቴጌ ጣይቱ የደጃዝማች ባልቻ የአጼ-ምንሊክ ህንፃዎች ይገኛሉ። የዕለቱን ሙሉ ቅንብር ያድምጡ!

Jerusalem Kirchen
ምስል DW/H. Melesse

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ