1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የድላሚኒ ዙማ ሥንብት እና ተተኪ ፍለጋ

ሐሙስ፣ ሰኔ 23 2008

ተሰናባቿን የአፍሪቃ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን ለመተካት የፊታችን ሐምሌ ይደረጋል የተባለዉ ምርጫ ወደ ሌላ ጊዜ ሳይራዘም እንደማይቀር እየተነገረ ነዉ።ተሰናባቿ ፕሬዝደንት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ በደቡብ አፍሪቃ ሊደረግ በታቀደዉ ምርጫ ፕሬዝዳንት አሊያም ምክትል ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጭምጭምታ እየተሰማ ነው።

https://p.dw.com/p/1JGtw
Nkosazana Dlamini-Zuma
ምስል Reuters

[No title]

የአፍሪቃ ኅብረት 54 አባል አገራት ለ27ኛ ጉባዔያቸው በኪጋሊ ሲሰበሰቡ የኮሚሽኑን አዲስ ፕሬዝደንት ይመርጣሉ።በጎርጎሮሳዊው 2012 ዓ.ም. ከረጅም ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ በኋላ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት እና አራት አመት ለማይሞላ ጊዜ በኃላፊነት የቆዩት ደቡብ አፍሪቃዊቷ ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ይሰናበታሉ። የጸረ-አፓርታይድ ታጋይ እና የፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ የቀድሞ ባለቤት ዙማ ጋቦናዊውን ዲፕሎማት ዤን ፒንግን ያሸነፉት በቀላሉ አልነበረም። በጸጥታ ጥናት ተቋም የደቡብ አፍሪቃ ቢሮ ተመራማሪ የሆኑት ሊይስል ሎው የዙማ ዘመነ-ሥልጣን ቅሬታ የተሞላበት ቢሆንም ስኬታማ እቅዶችም ነበሯቸው ሲሉ ይናገራሉ።

«በአዎንታዊው ጎን በሴቶች መብት፤ እንደ ያለ ዕድሜ ጋብቻ፤ የጾታ እኩልነት ሰላም እና ጸጥታን በመሳሰሉ የአፍሪቃ ሴቶች ጉዳዮች ላይ ጠንክረው ለመስራት ሞክረዋል። በዚህ በአንዳንድ የአፍሪቃ አገሮች ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት አዳዲስ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል። ሌላው አጀንዳ 2063 የተሰኘ እቅድ ጀምረዋል። ሌሎች ኔፓድን የመሰሉ በርካታ ተመሳሳይ እቅዶች በመኖራቸው እና የጀመራቸው ሰው ሲቀየር የሚዘነጉ በመሆኑ ይኸኛው ከእርሳቸው ዘመን መሻገር መቻል አለመቻሉን ወደ ፊት የምናየው ይሆናል። አጀንዳ 2063 በአፍሪቃ ሰላም እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ያለመ የረጅም ጊዜ እቅድ ነው።»

Afrikanische Union Gebäude Außenansicht Äthiopien Addis Ababa
ምስል Imago

የድላሚኒ ዙማ ተቺዎች አጀንዳ 2063 ያተኮረበት ኢኮኖሚያዊ እድገት ከአፍሪቃ ኅብረት ይልቅ የአፍሪቃ ልማት ባንክ እና የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ጉዳይ ነው ሲሉ ይደመጣል። የጸጥታ ጥናት ተቋም ተንታኟ ሊይስል ሎው ዙማ የደቡብ አፍሪቃ የአሰራር ልምድን ወደ አፍሪቃ ኅብረት ማምጣታቸውን በአህጉራዊው ድርጅት ጉዳዮች ውስጥ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ መሞከራቸውን በበጎ ጎን ያነሱላቸዋል።በአፍሪቃ ኅብረት በነበራቸው ጊዜ ሁሉም እንደታቀደው ስኬታማ ባይሆኑም በተቋሙ ውስጥ የግል አማካሪዎችን ቀጥረዋል። ሊቀ-መንበሯ የሚወቀሱባቸውም ጉዳዮች አልጠፉም።

«አዲስ አበባ አይገኙም። ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በደቡብ አፍሪቃ ነው እያሉ ሰዎች ይወቅሷቸዋል። በፈረንሳይኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለመፍታትም አልቻሉም። ከደቡብ አፍሪቃ እና አካባቢው አገራት በመጡ አማካሪዎች ራሳቸውን ከበዋል ብለው የሚተቿቸውም አሉ።»

ድላሚኒ ዙማ በደቡብ አፍሪቃ የቀድሞ ባለቤታቸውን ጃኮብ ዙማን መንበር አሊያም የምክትል ፕሬዝዳንትነቱን ቦታ ይረከባሉ የሚለው መላምት ከአፍሪቃ ኅብረት ሐላፊነታቸዉ የሚለቁበት ቀዳሚ ምክንያት ተደርጎ ተጠቅሷል። ሊይስል ሎው ግን «ዳግም ላልመረጥ እችላለሁ» የሚል ስጋት ሊኖራቸው እንደሚችልም ይገምታሉ። ተንታኟ በተወሰኑ የአፍሪቃ ፖለቲከኞች ዘንድ ያን ያክል ታዋቂ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።

Tanzania Dar es Sallam Jakaya Kikwete ehemaliger Präsident von Tanzania
የቀድሞው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጃካያ ኪክዌቴምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

የኢኳቶሪያል ጊኒው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አጋፒቶ ምባ ሞኩይ ለኮሚሽኑ ፕሬዝደትነት ራሳቸውን በእጩነት ያቀረቡ የመጀመሪያው ሰው ናቸው። የቦትስዋናው ፔሎኖሚ ቬንሶን ሞይቶይ የደቡብ አፍሪቃ አገራት የልማት ማሕበረሰብን፤ የዩጋንዳው ስፔሲዮዛ ናይጋግ ዋንዲራ ደግሞ የምስራቅ አፍሪቃ አገራትን ወክለው በእጩነት ቀርበዋል። የአፍሪቃ ኅብረት ከሶስቱ ይልቅ የቀድሞውን የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጃካያ ኪክዌቴን አሊያም የአልጄሪያን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራን ማማተር ይዟል። እናም የመራዘሙ ነገር እውነት ይመስላል።

«ምርጫው በሐምሌ ወር በኪጋሊ ይካሄዳል። ከሁለት ወራት በፊት ቀነ-ገቡ ከማብቃቱ በፊት ሶስት እጩዎች ተመዝግበዋል። ምርጫው ይራዘማል የሚሉ ጭምጭምታዎች ከወደ አዲስ አበባ እየተሰሙ ነው። ሶስቱ እጩዎች ተቀባይነት የሚያገኙ አይመስልም። አንዳንድ የአገራት መሪዎች እና የቀድሞ ባለስልጣናት እጩዎች እንደገና እንዲመዘገቡ እና ምርጫው ጥር 2017 እንዲካሄድ ግፊት እያደረጉ ነው። ስለዚህ ቀጣዩን ሊቀ-መንበር መሾም በጣም አስቸጋሪ ነው። አህጉሩም በዚህ ጉዳይ እጅጉን ተከፋፍሏል።»

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ